የኦሮሚያ ጸጥታ ይዞታ፤ የንጹሃን ጥቃት
ሐሙስ፣ ኅዳር 5 2017የኦሮሚያ ጸጥታ ይዞታ፤ የንጹሃን ጥቃት እና የሰላም ፍላጎት ጩኸት
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ድሮንን ጨምሮ በሚጣሉ ከባባድ መሳሪያዎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአከባቢው ነዋሪዎች በተለይም ሰኞ እለት በተጣለው ጥቃት ንጹሃን መጎዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ዛሬ ኦሮሚያ ውስጥ በተለያዩ ዞኖች እና ከተሞች ስለሰላም የሚጣሩ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የሰሜን ሸዋ ዞን ሂደቡ አቦቴ ወረዳ ነዋሪ ተደጋግሞና በስፋት የሚስተዋለው የስልክ ግንኙነት ኔትዎርት መቆራረጥ በግጭቱ በብርቱ የፈተናቸው አንዱ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው ባለፈው ሰኞ በወረዳው ተከሰተ ባሉት የድሮን ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች መጎዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ “በዚህ አቦቴ ሀሪሮ ጠሬ በሚባል ስፍራ በድሮንም የታገዘ እርምጃ ተወስዶ በአጨዳ ላይ የነበሩ አርሶ አደሮች ተጎድተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከታለመለት ዓለማ ውጪ ንጹሃንን ስገድል እየተመለከትን ነው፡፡ ሲቪሎች በሁሉም አቅጣጫ ነው የሚጠቁት፡፡ ተፋላሚዎች ስፋለሙ ሰላማዊውም ዜጋ ጭምር ይጎዳል፡፡ አሁን ሰኞ እለት በነበረው የድሮን ጥቃት እና ከዋና ዋና ከተሞች ወደ ታች በሚወረወሩ ከባባድ መሳሪያዎችሰላማዊ ዜጎች ተጠቅተዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ህብረተሰቡ አይቶት የማያውቅ ስጋት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ ንብረትም ይጎዳል፡፡ በሰኞ ጠዋትና ከሰዓት ስምንት ሰዓት አከባቢ የድሮን ጥቃቱ እስካሁን ቁጥሩን ባንለይም የሰላማዊ ሰዎች መጎዳት እናውቃለን” ብለዋል፡፡
ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም በዚያው ዞን ወጫሌ ወረዳ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ በርካቶች ከተገደሉ ወዲህ በዞኑ ተባብሶ ቀጥሏል በተባለው ጫና ሰላሙ እጅጉን መደፍረሱም በአስተያየት ሰጪው ተነግሯል፡፡
በከባባድ መሳሪያዎች የደረሰው ጉዳት
ሌላም አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ነዋሪ ሃሳባቸውን ቀጠሉ፡፡ “መንግስትም ፊቼና አቦቴ ላይ ሆኖ ከባባድ ተኩስ ይለቃል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን አጠፋለሁ በሚል ሰበብ ጸጥታውም ትንሽ ከብዷል፡፡ ከሩቅ በሚለቀቁ ከባባድ ማሳሪያዎች የሚጎዳው ሰላማዊው ሰው ነው፡፡ በዚያ ላይ ድሮንም በስፋት ስጣል እንመለከታለን፡፡ አሁን ከሰሞኑ እዚሁ የአቦቴ አጎራባች የደራ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ከዚሁ በተጣሉ ከባባድ መሳሪያዎች ሰው ተጎድቷል፡፡ አሁን በደራ ባቡድሬ በተባለ ቀበሌ በአርሶአደር መሳ ላይ ወድቆ በሬዎችን ጎድቶባቸዋል፡፡ ሁለት ሰውም እንዲሁ ተጎድቷል እንጂ ከዚያ ባለፈ የከፋ አደጋ መከሰቱን አልሰማንም” ነው ያሉት፡፡
ከደራ ወረዳ ጉንዶመስቀል ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪም በወረዳው ሌላኛው ቀበሌ ተመሳሳይ አደጋ ማጋጠሙን በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡ “ዙ-23ን ጨምሮ ከባባድ መሳሪያዎች ተጥለው ከሰላማዊ ሰው አንድ ሁለት ሰው ላይ ጉዳት መድረሱን እናውቃለን፡፡ ሁለቱን ሰዎች ግን እህል በሚሰበስቡበት ስፍራ ነው የገደላቸው፡፡ አንድ ሴትና አንድ ወንድ ናቸው፡፡ ይህ የሆነው በደራ ወረዳ ራቾ ቀበሌ ነው” ብለዋል፡፡
የሰላም መታወኩ የፈጠረው ስጋት
አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን ላይ የሰላም እጦቱ የሚያስከትለው መዘዝ ሰፊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ “ህዝቡ በጣም ተቸግሯል፡፡ ይህ ወቅት አዝመራ የሚሰበሰብበት ወቅት ብሆንም በከባባድ መሳሪያዎች ጭምር የታጀበው ግጭት ስጋትን ፈጥሯል፡፡ አሁን ከጅሩዳዳ እና ባቡድሬ ከሚባሉ ቀበሌያት የተፈናቀሉ በጀማወንዝ አከባቢ ተፈናቅለው ሁለት ወላድ አሁን ከሰሞኑ ሜዳ ላይ ወልደዋል፡፡ የእኔም ቤተሰብ በዚህ ፈተና ላይ ከወደቁ መካከል ናቸው፡፡ ህብረተሰቡ ከሶስት ተፋላሚዎች በኩል በሚመጡበት ፈተና ነው የሚፈተነው” ብለዋል፡፡ ዶይቼ ቬለ በዚህ ላይ አስተያየቶችን ከመንግስት አካላት በተለይም ከዞኑ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር፣ ከኦሮሚያ እና ፌዴራል መንግስት የኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ግን ለዛሬ አልሰመረም፡፡
በአገር መከላከያ እና ኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ይፋዊ ማህበራዊ ገጽ በሚሰራጩ መረጃዎች መሰረት ግን መንግስት መጠነሰፊ ወታደራዊ እርምጃዎች በታጣቂዎች ላይ እንደሚወስድ እና በዚህም በተለያዩ አከባቢዎች ትጥቃቸውን አውርደው ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚመለሱ ታጣቂዎች መኖራቸውን ከነምስላቸው አሳይቷል፡፡
የሰላም ጥሪ በሰላማዊ ሰልፍ
በሌላ በኩል ኦሮሚያ ውስጥ በሚካሄደው የሰላም እጦት የተማረሩ የክልሉ ነዋሪዎች በተለያዩ ዞኖች ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ ስለሰላም አስፈላጊነት ተጣርተዋል፡፡ ከምዕራብ ሸዋ ዞን ባኮ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ነዋሪ በዛሬው ሰልፍ ተላለፈ ያሉትን መልእክት እንዲህ አጋሩን፡ “ህዝቡ በዛሬው ሰልፍ የሰላም ጥሪ ነው ያቀረበው፡፡ ሰው በነቂስ ነው የወጣው፡፡ ማንም ቤት አልቀረም ማለት ትችላለህ፡፡ ተጎድተናል፣ ተፈናቅለናል ሰላምና ልማቱ ይሻላል የሚል መልእክትም በህዝቡ ተላልፏል” ነው ያሉት፡፡ በክልሉ በርካታ ዞኖችና ከተሞች ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ ተካህዶ መዋሉን የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮም አረጋግጧል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ