1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኦሮሞ ልሂቃን ጥሪ እና የኦነግ መግለጫ

ሥዩም ጌቱ
ሰኞ፣ ሐምሌ 28 2017

የኦሮሞ ምሁራንና የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በሚል እራሱን የሰየመ የልሂቃን ቡድን ባሳለፍነው ሰሞን በዩናይትድ ስቴትስ ተሰብስቦ በኦሮሚያ ክልል፣ በኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የፖለቲካ ግቡን አስቀምጠዋል፡፡ሆኖም ኦነግ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በስብስቡ ውስጥ የወከለው አካል አለመኖሩንና አለመሳተፉን አስታዉቋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) - አርማ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) - አርማምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኦሮሞ ልሂቃን ጥሪ እና የኦነግ መግለጫ

This browser does not support the audio element.

የኦሮሞ ልሂቃን ጥሪ እና የኦነግ መግለጫ

የኦሮሞ ምሁራን እና የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በሚል እራሱን የሰየመ የልሂቃን ቡድን ባሳለፍነው ሰሞን በዩናይትድ ስቴትስ ተሰባስቦ በኦሮሚያ ክልል፣ በኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ እንሄድበታለን ያለዉን የፖለቲካ ግብ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡

ስብሰባ ተቀምጦ የነበረዉ ይኸዉ የልሂቃን ስብስብ ውስጥ በአገር ቤት በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የሚገኙ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መሳተፋቸውን ስብስቡ አስታውቋል፡፡ ሆኖም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በስብስቡ ውስጥ የወከለው አካል አለመኖሩንና ተሳትፎም አለማድረጉን ነው ያስታወቀው፡፡እራሱን የኦሮሞ ልሂቃን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ብሎ የጠራው የልሂቃን ስብስብ በወቅታዊ የኦሮሚያ ክልል፣ የኢትዮጵያ እና አፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች በጥልቀት መክሮ ደረስኩበት ባለው ስምምነት በርካታ እንሄድበታለን ባለው የፖለቲካ አቅጣጫ ነጥቦችን ማስቀመጡን አመልክቷል፡፡

የኦሮሞን ህዝብ ከዚህ በፊት ታይቶ ለማይታወቅ ሰቆቃ እና ጭቆና መጋለጡን ገልጾ አቋሙን የገለጸው ስብስቡ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ መንግስት በጨቋንነት ከሶ ለህዝቦች የጋራ ትግል ጥሪ እንደሚቀርብ አስታውቋል፡፡ የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች (ኦነግ-ኦነሰ፣ ኦፌኮ እና ኦነግ) አስፈላጊውን ለውጥ ለማምጣትና መጪውን ሽግግር ስኬታማ ለማድረግ በተደራጀ መንገድ የሚደረግ ያለውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመደገፍ መስማማታቸውንም በመግለጽ፤ ለተለያዩ አካላት አብሮ የመስራት ጥሪ አሰምቷል፡፡ በውጪ አገራት የሚገኙ የኦሮሞ ልኂቃን የበይነ መረብ ምክክር እና ትችቱ

በዚህ ውስጥ ስማቸው ከተጠቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ግባር (ኦነግ) ግን በዚህ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተደርጓል በተባለው የውይይት መድረክ ላይ ተሳትፎ አለማድረጉንና ሰውም አለመወከሉን ጠቅሶ ስሙ ያለአግባብ ባልነበረበት ስፍራ መጠቀሱን ተቃውሟል፡፡ ፓርቲው ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፤ ኦነግ የሲያትል ውሳኔ በሚል ከተላለፈው የፖለቲካ አቅጣጫ ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደሌለውና ስሙም በዚያ መጠቀሱ ስህተት ነው ብሏል፡፡

የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ድሮ በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየት፤ “ኦነግ በዚህ ስብሰባ ላይ፣ አልተጋበዘም፣ አልተሳተፈም እንዲሁም የወጣው የአቋም መግለጫ እኛን የሚመለከተን አይደለም” ሲል ነው የገለጸው፡፡ ፓርቲያቸው ጉዳዩን ከማህበራዊ ሚዲያ መስማቱን የገለጸው ኦነግ አቋሙንም ለሚከተለው ህዝቡ ይፋ ማድረጉንም አቶ ዓለማየሁ አስታውቀዋል፡፡

ለኦሮሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የአንድነት ጥሪ ያቀረበው የአቋም መግለጫ ያወጣው የፖለቲካ ልሂቃን ስብስቡ ግን ፤ በኦሮሞ የፓለቲካ ኃይሎች መካከል የተጀመረው ውይይት እንዲቀጥልና ከሌሎች የአገሪቱ  ሕዝቦችና ዜጎች ጋር ምክክር ለማድረግ ከስምምነት እንደተደረሰበት አሳውቋል። በዚህም ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ዓለማየሁ ድሮ፤ “እኛ በመሪህ ደረጃ የኦሮሞ ህዝብ እና የፖለቲካ መሪዎች አንደነት የምንደግፈው ቢሆንም ይሄን መድረክ በተመለከተ ግን ምንም ተሳትፎ ያላደረገበት በመሆኑ ውሳኔውንም እንደማይቀበለው” ነው የገለጸው፡፡ ስለመጭዉ የኢትዮጵያ 2018 ምርጫ ኦፌኮ የሰጠዉ ገለጻ

በዚህ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ አልተሰማም፡፡ ዶይቼ ቬለ በበኩሉ ለመንግስት ኮሚዩኒኬሽን የስራ ኃላፊ በመደወል አስተያየታቸውን ለማካተት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ በውጪ አገር የሚገኙ የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን እና የሌሎችም ብሔሮች ተወካይ ምሁራን ከዚህ በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት አስተዳደር ላይ ሰፊ ቅሬታ በማቅረብ መንግስታቸውን ለመጣል እንደምተባበሩ መግለጻቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር እንቅስቃሴውን መንቀፋቸው ግን አይዘነጋም፡፡


ሥዩም ጌቱ 
አዜብ ታደሰ 
ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW