1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ መገደላቸዉን የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር አስታወቀ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 30 2017

የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሰራዊት ሾዴ በሚባል ስሙ የሚታወቀውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) አመራር መግደሉን ያስታወቀው ከትናንት በስቲያ መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ነው፡፡ መከላከያ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ዋና አዛዥ “የጃል መሮ ወይም ኩምሳ ድሪባ የቀኝ እጅ” ያለው ግለሰቡ---

የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ሠራዊት ከፍተኛ ባለሥልጣኑ «ተገደሉ» ሥለመባሉ እስከ ዛሬ አመሻሽ ድረስ ማረጋገጪያም፣ ማስተባባያም አልሰጠም
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባልደረቦች በከፊል።የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የኦሮሞ ነፃ አጪ ሠራዊት (ኦነሠ) ከፍተኛ አዛዥን መግደሉን አስታዉቋልምስል፦ Solomon Muche/DW

የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ መገደላቸዉን የኢትዮጵያ መከላከያ ጮር አስታወቀ

This browser does not support the audio element.

 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በታንዛንያው የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) የድርድር መድረክ ላይ ከተሳተፉት የኦነሰ ከፍተኛ አመራሮች አንዱን ገድያለሁ አለ፡፡የአገር መካላከያ ሰራዊት ሾዴ ያለው የኦነሰ ከፍተኛ አመራር በሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ሀሮ ሊሙ ወረዳ ውስጥ መግደሉን ነው ያሳወቀው፡፡ከፍተኛ አመራሩ እንደተገደለበት የተነገረው ታጣቂው ቡድነ (ኦነግ-ኦነሰ) ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠበትም፡፡

የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሰራዊት ሾዴ በሚባል ስሙ የሚታወቀውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) አመራር መግደሉን ያስታወቀው ከትናንት በስቲያ መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ነው፡፡ መከላከያ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ዋና አዛዥ “የጃል መሮ ወይም ኩምሳ ድሪባ የቀኝ እጅ” ያለው ግለሰቡ ከዚህ በፊት ታንዛንያ ዳሬሰላም ውስጥ በተዘጋጀው የኦነሰ እና ኢትዮጵያ መንግስት የድርድር መድረክ ላይ መሳተፉንም ነው ያመለከተው፡፡

መከላከያ በመግለጫው በትግል ስሙ “ጃል ሾዴ” ተብሎ የሚታወቀውን የታጣቂ ቡድኑን አመራር የገደለው በሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ሀሮሊሙ ወረዳ ገንጂ ለጋኮርማ ተብሎ በሚታወቅ ስፍራ መሆኑን ነው ያስታወቀው፡፡

እንደ የአገር መከላከያ ማብራሪያ ጃል ሾዴ የተገደሉት ከተጠቀሰው ስፍራ ተነስተው ሱጊ ወደተባለ አከባቢ በሞተር ሳይክል በመንቀሳቀስ ላይ ሳለ እንደነበር ነው ያስታወቀው፡፡

መከላከያ አክሎ እንዳስታወቀው ሾዴ ከዚህ ቀደም በታንዛንያ በተሞከረው የሰላም ውይይት መድረክ ላይ ከታጣቂ ቡድኑ ዋና አዛዥ ጃል መሮ (ኩምሳ ድሪባ) ጋር በመሆን ወደ ታንዛንያ ማቅናቱንም አስታውቋል፡፡ አክሎም “ሾዴ ከታንዛንያው የሰላም ድርድር መልስ የመላው የወለጋ ዞኖች ዋና አዛዥ ሆኖ በጃል መሮ ተሹሞ ነበር” በማለት ነው መከላከያ ያስታወቀው፡፡

ጃል ሾዴ የኦነሰ ተወካይ ሆነው በታንዛንያው ዳሬሰላም ድርድር ላይ ስሳተፉ “የጃል መሮ ደህንነት ጉዳዮች ኃላፊ ነበርም” ነው የተባለው፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሐኑ ጁላ።የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም።ማርሻል ብርሃኑ የሚያዙት ጦር የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ሠራዊት (ኦነሠ) አንድ ከፍተኛ አዛዥን መግደሉን አስታዉቋል።ምስል፦ Fana Broadcasting Corporate

ዶይቼ ቬለ ይህንኑን መረጃ በመያዝ  በተለይም ከፍተኛ ባለስልጣናኑ ተገድሎበታል በተባለው በኦነግ-ኦነሰ በኩል ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልሰመረም፡፡ የመከላከያን መግለጫ ተከትሎ በተለይም ለታጣቂ ቡድኑ ከፍተኛ አዛዥ አማካሪ አቶ ጅሬኛ ጉደታ በተደጋጋሚ ያደረግነው የስልክ ጥሪ ምላሽ አላገኘም፡፡

በኦሮሚያ ክልል አላቧራ ባለው የፀጥታ ችግር እለት በእለት በሰላማዊ ዜጎች ላይ በሚደርሰው የሰላም እጦት ተጽእኖ በርካቶች ከሃብት ቀዬያቸው ተፈናቅለዋል በዚሁ በተራዘመው ግጭትም ህይወታቸው የተቀጠፈው ዜጋ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታዎች በቅርበት የሚከታተሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ እንደሚሉት “ብዙም ጊዜ እንደተነገረው በመገዳደል የሚመጣ ነገር የለም” ያሉት ሙላቱ ለችግሮች እልባት የሚመጣው በመነጋገር ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና መንግስት በታንዛንያ በሁለት ዙር ከዚህ በፊት ያደረጉት የሰላም ድርድር ተደጋግሞ ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ለሰላማዊ ድርድሩ አለመሳካትም ሁለቱም ወገኖች አንዱ ሌላኛውን ጥፋተኛ በማድረግ ተወቃቅሰዋል፡፡ በተለይም ጃል መሮ እና ጃል ገመቹ አቦየን ጨምሮ የታጣቂ ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች በተሳተፉበት ሁለተኛው የታንዛንያ የሰላም ድርድር “ቁልፍ” በተባሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ መግባባት ባለመደረሱ በልዩነት እንደተለያዩ እስካሁንም በግጭት ላይ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ በሰሜን ሸዋ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖችም በርካታ “የሸነ” ታጣቂዎችን ገደልኩ ያለው መከላከያ በሆሮጉዱሩ ወለጋው የሀሮ ወረዳ ጥቃት ከጃል ሾዴ ጋርም በርካታ ታጣቂዎች ተድለው የጦር መሳሪዎች መማረካቸውን ነው የገለጸው፡፡

ፖለቲከኛ ሙላቱ እንዳሉት ደግሞ በአገሪቱ ያለው ልፈታ የሚገባው ቁልፉ ችግር ይህ ነው፡፡ “አገሪቷ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ኤደለም፡፡ ትልቁ ችግር የፖለቲካ ችግር በመሆኑ ያንን በመፍታት ዘላቂ መፍትሄ ማስፈን ይቻላል” በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW