1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ ስለ ኦሮሚያው ግጭት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 9 2014

አባ ገዳ ጂሎ ማንኦ የአገር ሽማግሌ አልቀረ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሃዳ ሲንቄዎችም ብሌን ሴቶች ሰብስበን ሳር ይዘን ወጥተን ሁሉንም የሰላም አማራጮች ሞክረናል፡፡ ሲታረቁ ግን አላየንም፡፡ ምናልባት ወደ ፊት ያለቀ አልቆ ያሸነፈም አሸንፎ የቀረ እድለኛ ይኖር ይሆናል” ብለዋል፡፡

Äthiopien | Oromo | Abageda Jilo Man'o
ምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ ስለ ኦሮሚያው ግጭት

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ላለፉት አራት ኣመታት በታጣቂዎች እና መንግስት መሃል በሚካሄው ጦርነት ትልቁን ዋጋ እየከፈለ ያለው የኦሮሞ ህዝብ በመሆኑ ሰላምን ለህዝብ ሚያመጣ አማራጭ እንዲፈለግ የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ ጠየቀ፡፡
የጉጂ አባገዳ እና የኦሮሞ አባገዳዎች ሰብሳቢ አባገዳ ጂሎ ማንኦ ለዶቼ ቬለ እንደገለጹት በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች የሚካሄደው ግጭት ሳይወሳሰብ ጀምሮ ህበረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ለማስቆም ያቀረብነው ጥሪም ሆነ ጥረት ሳይሰምር ቀርቷል፡፡ አባገዳ ጂሎ ማንኦ የአባገዳዎች ህብረት በርካታ ጊዜ እርቅ ወርዶ ሰላም የሚመጣበት መንገድ ቢፈልግም ተደማጭነት አጥተናል ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል መንግስት “ሸነ” ሲል በሚጠራውና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በአሸባሪነት ከተፈረጀው እራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” በሚል ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር መንግስት ላለፉት ዓመታት በሚያደርጋቸው ውጊያና አለመግባባቶች በርካቶች  ሕይወታቸው አጥተዋል፡፡ ንብረት ወድሟል፣ ሰላማዊ ዜጎች ተፈናቅለዋል።  የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ለችግሩ የፖለቲካ መፍትሄ ተፈልጎለት ህብረተሰቡ ሰላሙን እንዲያገኝ እየወተወቱ ነው፡፡ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው የኦሮሞ አባገዳዎች ከዚህ አንጻር ምን ሰርተው ይሆን ብለን የኦሮሞ አባገዳዎች ሰብሳቢ አባገዳ ጂሎ ማንኦን አነጋግረናል፡፡ አባገዳ ጂሎ ማንኦ “በእርግጥ የፖለቲካ ኃይሎች፤ መንግስትም ይሁን ‘ሸነ’ ተብሎ በጫካ ያለው ኃይል ለምን እንደሚፈላለጉ፤ አንዱ ሌላውን ለምን እንደሚያድን እነሱ ያውቃሉ፡፡ የኛ ህዝብ ምንም የማያውቅ አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ነጋደው ግን በማያውቀውና ባልገባው ጉዳይ ነው እያለቀና መከራ እየተቀበለ ያለው። ሁላችንም እየተሰቃየን ነው ‘ሸነ’ በተባለውና እነሱ ላይ ይወሰዳል በተባለው እርምጃ ምክንያት፡፡  አየህ እነሱ ጋ ማንም ማንንም ማጥፋት አልቻለም፡፡ ችግሩ ሁሉ በዋናነት እያረፈ ያለው ህዝቡ ላይ ነው፡፡ ሸነ የተባሉትም ካምፕ የላቸውም፡፡ ካምፓቸው ህዝብ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ እዛው በማህበረሰቡ ውስጥ እያሉ ነው ከመንግስት ጋር የሚታኮሱት፡፡ ይህም ያም በሚያደርጉት ነገር ተጎጂው ንጹህ ማህበረሰቡ ነው” ብለዋል።

ምስል Seyoum Getu/DW

አባ ገዳ ጂሎ ማንኦ እሳቸው ከሚኖሩበት ጉጂ አከባቢ እንኳ ተነስተው ሲያብራሩ “እኛ አሁን ስለ ልማት ማሰብ አይደለም የነበረንም ልማት አጥተናል፡፡ ተማሪ ቤት በለው ከጤና ጣቢያ እስከ ሆስፒታል ተቃጥሏል፣ ወድሟል፡፡   የልጆቻችን ትምህርት ተቋርጦ ጨለማ ውስጥ ነን፡፡ መንገድ የለንም፣ ውሃ የለም፡፡ ምን የቀረልን ነገር አለ? የቱን ተናግረን እንዘልቃለን ብለህ ነው፡፡ እንደው የዚህ የቡሌ ሆራው ምእራብ ጉጂም ሆነ አጠቃላይ እንደ ጉጂም ይሄ ነው የሚልህ ሰላማዊ ቦታ ልጠቅስልህ አልችልም፡፡ ይኸው እስከ ዛሬ እንኳ ጥፋት ነው ሚሰማው” ሲሉ አማረዋል፡፡
አባ ገዳ ጂሎ ማንኦን ስለመፍትሄ በተለይም ሰላማዊ ማህበረሰብን መታደግ ስለሚቻልበት መንገድ እና ህብረታቸው በዚህ ላይ ስለሚያስበው ውጥንም ጠይቀናቸው፤ “እኛ አሁን ግራ የገባን እንዴት ከዚህ እንውጣ ነው፡፡ ታረቁ እኛ በመሃል አልቀናል ብለን ሁሉንም ወገን ተማጽነናል፡፡ እንደው ጉጂ ዋጋ እየከፈለ እያለቀ ነው፡፡ የአገር ሽማግሌ አልቀረ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሃዳ ሲንቄዎችም ብሌን ሴቶች ሰብስበን ሳር ይዘን ወጥተን ሁሉንም የሰላም አማራጮች ሞክረናል፡፡ ሲታረቁ ግን አላየንም፡፡ ምናልባት ወደ ፊት ያለቀ አልቆ ያሸነፈም አሸንፎ የቀረ እድለኛ ይኖር ይሆናል” ብለዋል፡፡ 
በኦሮሞ ባህላዊ  የገዳ ስርዓት መሰረት የገዳ አባቶች ካላቸው ተሰሚነት አንፃር የአባገዳዎቹ ተቀባይነት ምን ያህል ይሆን የተባሉት አባገዳ ጂሎ ማንኦ፤  ስንደመጥ ስንሰማ አላየንም ብለዋል፡፡
“የአባገዳዎች ህብረት ከተቻለ የሚዋጉት እንዲታረቁ፡፡ ካልተቻለም ህብረተሰቡ ሰላሙን እንዲያገኝ ብለን ያልገባንበት የለም፡፡ በጫካ ሆነው የሚዋጉትና ሸነ የተባሉት ጋም ገና ከጅምሩ ሳር ይዘን ሄደን ተወካዮቻችን ያሉንም አነጋግረን፤ ከዚያን መንግስትንም አነጋግረን ነበር፡፡ እኛ አልቀናል፡፡ በተለይም የጉጂ ህዝብ በእጅጉ ተጎድቷል አልናቸው፡፡ እንደ አባገዳዎች ማን ያልተማጸነው አካል አለ? አሁን መፍትሄ የሚመስለኝ እነዚህ ሸነ የተባሉት አሊያም መንግስት አሸንፎ አንዱ አልጋ ከያዘ ያኔ ሰላም እናገኝ ይሆናል፡፡ አባገዳዎች ይሁኑ የአገር ሽማግሌዎች አሊያም የሃይማኖት አባቶች ማንም ያስታርቃቸው ማን እርቅ ቢወርድ እፎይ እንል ይሆናል፡፡ አሁን ለሁለት ጌቶች የምናጎነብስ ነው የሆነው፡፡ እንዴት ከዚህ እንደምንወጣ አናውቅም” ብሏል።
 ሥዩም ጌቱ 

ምስል Seyoum Getu/DW

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
  

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW