1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አቤቱታ

ሐሙስ፣ ግንቦት 7 2017

የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉና የኦፌኮ የጅማ ዞን ኮሚቴ አቶ ቶኩማ ኡርጌ “ሕገ-ወጥ” ባለው መንገድ ተይዘው መታሰራቸውን አስታውቋል።ኦፌኮ ከ2010 ለውጥ በኋላ በመላው ኦሮሚያ 206 ቢሮዎች መክፈት መቻሉን ያመለከቱት የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና አሁን ሶስቱ ብቻ በንቃት የምንቀሳቀሱ መሆኑን ልጸዋል።

የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናምስል፦ Seyoum Getu/DW

“ካሉኝ 206 ጽ/ቤቶች በስራ ላይ ያሉ ሶስቱ ብቻ ናቸው” ኦፌኮ

This browser does not support the audio element.

የኦፌኮ አመራር አባል እስር

የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉና የኦፌኮ የጅማ ዞን ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ቶኩማ ኡርጌ “ሕገ-ወጥ” ባለው መንገድ ተይዘው መታሰራቸውን በገለጸበት መግለጫው፤ አቶ ቶኩማ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት ግድም በጅማ ከተማ ከሚገኙበት የሥራ ቦታቸው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መወሰዳቸውን ነው ያመለከተው። እኚህ የድርጅቱ አባልና አመራር እስካሁን ድረስ ፍርድቤት ያልቀረቡ መሆኑን ያመለከተው የፓርቲው ይፋዊ መግለጫ፣ በጅማ ከተማ በሚገኘው 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ ከሕግ ሥርዓት ውጪ በእስር ላይ ይገኛሉም ነው ያለው።

በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም.ኦፌኮ ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የአመራሩን መታሰር አስመልክቶ ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ ማብራሪያ እንዲሰጠው ቢጠይቅም የተሰጠው ተጨባጭ ምላሽ አለመኖሩንም ጠቁመዋል። “ሕገወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ትሳተፋለህ በሚል መያዙንና ቤቱ ተፈትሾ ምንም እንዳልተገኘበት እናውቃለን” ያሉን መረራ እስካሁን ለፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንም ገልጸዋል፡፡

“የጽህፈት ቤቶቹ መዘጋት”

ኦፌኮ በኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም. የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በመላው ኦሮሚያ ወደ 206 ቢሮዎች መክፈት መቻሉን ያመለከቱት ፕሮፌሰር መረራ አሁን ላይ ሶስቱ ብቻ በንቃት የምንቀሳቀሱ መሆኑን ገልፀው የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ፈትኖናል ብለዋል፡፡ “በስራ ላይ የሚገኙ ከሞላ ጎደል በአዲስ አበባ፣ አምቦ እና አሰላ የሚገኙ ሶስት ቢሮ ናቸው” ያሉት ፕሮፈሰር መረራ “በደጉ ጊዜ በለውጡ ሰሞን እስከ 206 ቢሮ ከፍተን ነበር” በማለት አሁን ላይ ከ200 በላይ የፓርቲው ጽህፈት ቤቶች ከስራ ውጪ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ የቢሮዎቻቸው መዘጋት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የሚፈጸም መሆኑን ለዶቼ ቬለ የገለጹት ፕሮፌሰር መረራ፤ በአንዳንድ ቦታ አመራሮችን ማስፈራራትና መሳድ እንዲሁም አንዳንድ ቦታ ደግሞ “የቢሮዎች መዘረፍ” እንደገጠማቸውም ገልጸው ምእራብ ወለጋ ጊምቢ፣ ምስራቅ ወለጋ ነቀምት እና ምዕራብ ሀራርጌን በማሳያነት ጠቃቅሰውአቸዋል፡፡

ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የፖለቲካ ምህዳር ጥያቄ

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ለማከናወን የአንድ ዓመት እድሜ ብቻ ቀርቶታል ተብሎ በሚታሰብበት ባሁን ወቅት፤ ኦፌኮ ከወዲሁ ስለሚያደርገው ዝግጅት ምንነትም የተጠየቁት ፕሮፌሰር መረራ፤ “ከምርጫ 97 ሌላ እንኳን ምርጫ ቅርጫም አልሆኑም” በማለት በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ምርጫዎች ሰላምና መረጋጋት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የተረጋጋ ብልጽግና ማምጣት እንዳለባቸው ሞግተዋል፡፡ ባለፈው የ2013 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ገዢው ፓርቲን በብቸኝነት በመወዳደር የከሰሱት መረራ፤ ቀጣዩ የ2018 ምርጫም ቢሆን ከመካሄዱ በፊት ዜጎች በነጻነት መምረጥ የሚያስችላቸው የፖለቲካ ስምምነት መደረግ እንደሚኖርበት ግልጸዋል፡፡ ምርጫው ላይ ለመሳተፍ የአጭር ጊዜ ዝግጅት ብቻ በቂያቸው መሆኑንም በመጠቆም የፖለቲካ ውይይቶች ከዚያ አስቀድሞ እንደሚያስፈልጉም ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡

በኦፌኮ ክስ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ የእጅ ስልክ ላይ በመደወል አስተያየታቸውን ለማካተት ጥረት ብናደርግም ለዛሬ አልተሳካም፡፡ ኦፌኮ ከሰላማዊ የፖለቲካ አማራጭ ውጪ ምንም ተሳትፎ እንደሌለው የገለጹት ፕሮፌሰር መረራ በቅርቡ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ጀምረውት የነበረው እንቅስቃሴ እስካሁን ፍሬ አለማፍራቱን ገልጸዋል፡፡ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የሰሞኑን የአመራር አባሉን እስራት ሃገራዊና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት የፍትሕ፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ ክብር መርሆዎችን እንዲያስከብሩ ሲል ጠይቋልም፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW