የኦባማ ዳግም መመረጥ እና የአፍሪቃ ተስፋ
ዓርብ፣ ጥቅምት 30 2005የዮናይትድ እስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዳግም በፕሬዚዳንትነት ተመርጠዋል። የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የምርጫ ዘመቻውን እና የምርጫውን ውጤት በሀገራቸው ምርጫ እንደተካሄደ ማለት ይቻላል በቀጥታ ሲያሰራጩ ተስተውሏል። ኦባማ ከአራት አመት በፊት ሲመረጡ በተለይ ለአፍሪቃውያን ትልቅ ተስፋ ጥለውባቸው ነበር። በአሁንስ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ያደረባቸው ስሜት ምን ይመስላል? ሶስት ወጣቶችን አነጋግረናል።
ሌሎች ወጣቶችም በኦባማ ዳግም መመረጥ ያላቸው አስተያየት በፊስ ቡክ አካፍለውናል። ደስ አለኝ የተባለ አንናቢያችን፤ «ኦባማ የ300 ሚሊዮን ተስፈኞች እንጂ የአፍሪቃ አይደሉም» ይላል። ሰለሞን ተክሌ ደግሞ የኦባማ ዳግም መመረጥ ለUSA ህዝብ ጥሩ ጊዜ እና አጋጣሚ ይፈጥራል ነው ያለው። ይሄውም ጀምረውት ለነበረው ውጥን ስራ ብሩህ ወቅት ነው፤ አፍሪቃም የሆነ ቁምነገር ከሳቸው ትጠብቃለች ሲል አስተያየቱን ገልጿል። ደመቀ ፍሰሀ ደግሞ «ኦባማ ለአፍሪቃ ጥሩ ነገር ያደርጋሉ ብሎ ማሰብ ከንቱ ተስፋ ስለሆነ ባንለፋ ጥሩ ነው። የአፍሪቃ ችግር የሚፈታው በልጆቿ ብቻ ነው» ብሏል።አዳነ ሳሙኤል ፤«የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ማንም ይሁን ማን ለአፍሪቃ የተለየ ነገር አይፈጥሩም። ለዕርዳታ ከሆነ ከአፍሪቃ የሚጠበቀው ፀባይ ማሳመር ብቻ ነው፤ ነው ያለው። በርካታ አስተያየት የሰጡን የኦባማ መመረጥ ለአፍሪቃ ምንም አይነት ለውጥ አያመጣም ነው ያሉት። ሁሉንም አስተያየቶች ከፌስ ቡክ ገፃችን dw amharic ላይ ማንበብ ይቻላል። የድምፁን ዘገባ ወደታች ሲመለከቱ ያገኙታል።
ልደት አበበ
ተክሌ የኋላ