የኦብነግ ጉባኤ በጎዴ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 27 2012ድርጅቱ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ጉባዔውን ዛሬ በጎዴ ከተማ ሲጀምር ከ700 በላይ ተሳታፊዎች በጉባዔው ላይ ተሳታፊ ተሳታፊ ስለመሆናቸውም አስታውቋል። የኦጋዴን ነጻነት ግንባር በምህጻሩ ኦብነግ ለረዥም አመታት መሪውን ድርጅቱን ሲመሩ የነበሩትን አንጋፋ ፖሎቲከኞቹን በአዳዲስ ሊቀይር መሆኑን አስታውቋል። በአገሪቱ በቀጣይ ለሚኖረው የፖሎቲካ ተሳትፎ የፕሮግራም ለውጥ እንደሚያደርግ የድርጅቱ ቃል አቃባይ አቶ ሀሰን ሙዓሊን ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል።
ድርጅቱ አራተኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ በጎዴ ከተማ ጀምሯል። በጉባዔው ነባርና አንጋፋ የድርጅቱ መሪዎች በራሳቸው ጥያቄ ከሃላፊነታቸው ተነስተው በአዳዲስ ሰዎች እንደሚተኩ አቶ ሃሰን ተናግረዋል። ኦብነግን ላለፉት 21 ዓመታት ሲመሩ የነበሩት አድሚራል መሀመድ ዑመር ዑስማን በራሳቸው ጥያቄ ከሃላፊነታቸው እንደሚነሱ አቶ ሃሰን ገልጸዋል። በተጨማሪም ሌሎች ለጊዜው ስማቸው ያልተገለጸ የድርጅቱ አመራሮችም አድሚራል መሃመድን ተከትለው ከሃላፊነት እንደሚነሱ እና በምትካቸው ጉባዔው ሌሎች አዳዲስ አመራሮችን እንደሚመርጥ አቶ ሃሰን አብራርተዋል። ኦብነግ አሁን ወደ ሰላማዊ የትግል መንገድ መጥቷል ያሉት የድርጅቱ ቃል አቃባይ አቶ ሀሰን በሀገሪቱ በቀጣይ በሚካሄድ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ መዘጋጀቱን እና በዚህ ጉባዔ የፕሮግራም ለውጥ ማድረጉን እንደሚያሳውቅ አስረድተዋል። ኦብነግ ነፍጥ አንግበው ዱር የነበሩት ታጣቂዎቹን ወደ መደበኛ የክልሉ የፖሊስ አገልግሎት መቀላቀሉን ተከትሎ ድርጅቱ ከፕሮግራም ለውጥ ባሻገር የአርማ ለውጥ እንዳደረገም አቶ ሃሰን ተናግረዋል። የኦጋዴን ነጻነት ግንባር ኦብነግ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ተቃዋሚ የፖሎቲካ ሃይሎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ጥሪ መደረጉን ተከትሎ አመራሮቹ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ይታወሳል።
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ