1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኦነግና ኦፌኮ የአገራዊ መድረኮች ተሳትፎ ለምን ቀዝቅዞ ተስተዋለ?

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ሰኔ 12 2017

የፓርቲዎቹ የአገራዊ ንግግሮች መድረኮች ተሳትፎ መቀዛቀዝን በማስመልከት ዶይቼ ቬሌ በመጀመሪያ ጥያቄውን ያቀረበላቸው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ዋና ጸሃፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ “ጥሪውን ያስተላለፉ አካላት” ያሏቸው የመድረኩን መዘጋጀትና ዓላማውን በተመለከተ ግልጽ ጥሪ አልተደረገልንም ነው ያሉት፡፡

Äthiopien Addis Abeba Oromo Federalist Congress (OFC)
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኦነግና ኦፌኮ የአገራዊ መድረኮች ተሳትፎ ለምን ቀዝቅዞ ተስተዋለ?

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በኦሮሚያ በስፋት ተቀባይነት አላቸው ተብለው የሚታመኑት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በአገራዊ ምክክርም ሆነ በተለያዩ ጊዜያት መንግስት በሚያዘጋጃቸው መድረኮች ሲሳተፉ አይታይም፡፡
ፓርቲዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ መስራትና የፖለቲካ ምህዳርን ማስፋት ዓላማው ያደረገ በተባለው በሰሞነኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ደድርጅቶች ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይትም ተሳትፎ አላደረጉም፡፡
ባለፈው ስድስተኛ አገራዊ ምርጫም የተለያዩ ምክንያቶቻቸውን አስቀምጠው በምርጫው ተሳትፎ ያላደረጉት ሁለቱ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ከአገራዊ መድረኮች ተሳትፎ ያራቃቸው ምን ይሆን?
የፓርቲዎቹ የአገራዊ ንግግሮች መድረኮች ተሳትፎ መቀዛቀዝን በማስመልከት ዶይቼ ቬሌ በመጀመሪያ ጥያቄውን ያቀረበላቸውየኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ዋና ጸሃፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ “ጥሪውን ያስተላለፉ አካላት” ያሏቸው የመድረኩን መዘጋጀትና ዓላማውን በተመለከተ ግልጽ ጥሪ  አልተደረገልንም ነው ያሉት፡፡ “በተለያየ መንገድ እንደ ፖለቲካ ድርጅት በደል ይፈጸምብናል” ያሉት ፖለቲከኛው አጋጣሚውን በመጠቀም ጥያቄዎቻቸውን ለሚመለከተው የመንግስት አካላት ለማድረስም መሰል መድረኮች አስፈላጊ ነበሩም ነው ያሉት፡፡ ፓርቲያቸውም ከየትኛውም አገራዊ መድረክም ሆነ የውይይት አጋጣሚዎች የመሸሽ ፍላጎት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ በፊናቸው፤ “ኦነግ ከመሰረቱ በውይይት ያምናል” በማለት በተለያዩ መድረኮች ላይ ለመሳተፍ ግን ድርጅታዊ ዓላመውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለመሳተፍና ላለመሳተፍ ግምገማዎች እንደሚደረጉ ነው የገለጹት፡፡ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በዚህ ላይ ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበላቸውየኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ በፊናቸው፤ “ኦነግ ከመሰረቱ በውይይት ያምናል” በማለት በተለያዩ መድረኮች ላይ ለመሳተፍ ግን ድርጅታዊ ዓላመውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለመሳተፍና ላለመሳተፍ ግምገማዎች እንደሚደረጉ ነው የገለጹት፡፡ አቶ ለሚ ሰሞነኛው የተፎካካሪ የፖለቲካ ድረጅቶች ተወካዮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በተወያዩበት መድረኩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ግን ለፓርቲው ጥሪ ዶርሶት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
ሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች በ2013 ዓ.ም. በተደረገው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ከተሳትፎ እራሳቸውን በማግለል የሚታወቁም ናቸው፡፡ “ከዚያ ምርጫ በኃይል ተገፍተኝ ወጣን የሚሉት” ሁለቱም የፖለቲካ ድርጅቶች የአመራሮችና አባላቶቻቸው እስራት እንዲሁም የጽህፈት ቤቶቻቸው መዘጋትን በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ለመካሄድ እቅድ በተያዘለት በቀጣዩ ሰባተኛ ብሔራዊ ምርጫ ስለመሳተፍ አለመሳተፍም የተጠየቁት ፖለቲከኞቹ፤ ፍላጎታቸው በምርጫው መሳተፍ ቢሆንም አሁን ያሉ ተግዳሮቶች ግን መፈታት ይኖርባቸዋል በሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “አሁንም ያ ፓርቲያችን ላይ ያለው ውጥረት አልተቃለለም” የሚል አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ጥሩነህ የፖለቲካ ድርጅታቸው ግብ ምርጫን በማሸነፍ መንግስታዊ ስልጣን መያዝ ነው በማለት በግልጽ ተናግረው፤ በተለያዩ አከባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን ጨምሮ ለምርጫው “ግልጽነት የጎደላቸው” ያሏቸው ተግዳሮቶች ካልተቀረፉ የመርጫ ተሳትፎአቸውን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ዝርዝር ጉዳዮቹ አሁን ባይገለጹም በሚመጣው ምርጫ ለመሳተፍ ከወዲሁ ዝግጅት ለማድረግ እንደ ፖለቲካ ድርጅት ማቀዳቸውን ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ምርጫ አስቻይ ሁኔታ ስላልነበር ከምርጫው ተገፍተን ወጥተናል ያሉት የኦነግ ቃልአቀባይ አቶ ለሚ በፊናቸው በቀጣዩ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ለተሳትፎ እንደሚዘጋጁ አስረድተዋል፡፡ “እኛ በተቻለን መጠን በምርጫ ህዝባችን ለመምራት ዝግጁ ነን” ያሉት አቶ ለሚ በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ ፈተናም ሆነ የተስፋ ጭላንጭሎች ከፊትለፊታቸው እንደሚታዩም ገልጸዋል፡፡ 
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ ከተባሉ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዓላማውም ፓርቲዎቹን ህጋዊ ተፎካካሪዎች አድርጎ በማስተናገድ ዴሞክራሲያዊ ከባቢን መፍጠር እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW