የኦነግ ዋና ቢሮ መከፈት
ረቡዕ፣ ሰኔ 4 2017
በ2012 ዓ.ም. የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ አገሪቱ ውስጥ ከተነሳው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የተዘጋው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ዋና ቢሮ ከአራት ዓመት ከ11 ወራት ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መከፈቱ ነው።
የቢሮው መከፈት ፋይዳ
ይህንኑን ለዶቼ ቬለ ያረጋገጡት የፓርቲው ስነስርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ዓለማየሁ ድሮ የዚህ ዋና ቢሮ ከአምስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መከፈቱ ለፖለቲካ እንቅስቃሴዎቻቸው አዎንታዊ ሚና ያለው ብለውታል። «እውነት ነው ተረክበናል አሁን ወደ ሥራ ለመግባት ቢሯችንን እያጸዳን ነው» ያሉት አቶ ዓለማየሁ፤ ለቢሮው ዳግም መከፈት አጋር የፖለቲካ ድርጅቶች ላሏቸው እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርዶ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በቀጣይ እንዲከፈቱ ስለሚጠበቀው የተዘጉ ሌሎች ጽ/ቤቶች
ኦነግ ባለፈው በ2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው አምስተኛ ብሔራዊ ምርጫ ላይ የአመራርቹና አባላቱን እስራት እንዲሁም የቢሮዎቹን መዘጋት እንደምክንያት ጠቅሶ ሳይሳተፍ ቀርቷል። አሁን ዋና ቢሮው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚቀጥለው ዓመት ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድ ማቀዱን ባሳወቀበት ወቅት መከፈቱ ፓርቲው ስለቀጣይ ስድስተኛ ብሔራዊ ምርጫ ተሳትፎ እንዲያደርግ ምን ያህል ይረዳው ይሆን? በሚል የተጠየቁት የፓርቲው ስነስርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ዓለማየሁ ድሮ፤ ጅማሮውን በመልካም ጎኑ እንደሚመለከቱት በመግለጽ «ጽሕፈት ቤቶች የነበሩን በየዞኖችና ወረዳዎች በመሆኑ ሁሉም ተከፍተው ነጻ እንቅስቃሴ መኖር አለበት» በማለት ለዚያ መሟላት አለባቸው ያሏቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠዋል።
ላለፉት አምስት ዓመታት በቢሮው መዘጋት ምክንያት ምንም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከማድረግ ተገቶ መቆየቱንም ያመለከተው ኦነግ፤ አሁን የዋናው ቢሮው መከፈት ለሌሎችም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መከፈት መንገድ ሊከፍት እንደሚችል አሳውቋል። አቶ ዓለማየሁ በ2012 ዓ.ም. ዋናው ቢሮው ሲከፈት በፓርቲው አመራሮች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባትና ክፍፍል ምክንያት ሆኖ ቆይቶ እንደሆነም ተጠይቀው፤ «ያ አንድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል» ጠቁመው ቢሮው ግን ከዚያም በፊት ተዘግቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
ለዓመታትም ተዘግቶ የቆየው አዲስ አበባ ጉሌሌአካባቢ የሚገኘው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)ዋና ቢሮ ፓርቲው ኢትዮጵያ ውስጥ በ2010 ዓ.ም. የመጣውን መንግሥታዊ ለውጥ ተከትሎ ከትጥቅ ትግል ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መመለሱን ተከትሎ ከረጅም ጊዜ በኋላ ተከፍቶ ሥራ ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ