የኦነግ ዋና ቢሮ መከፈትና የፖለቲካ ምህዳሩ ተስፋ
ሰኞ፣ ሰኔ 16 2017
የኦነግ ዋና ቢሮ መከፈትና የፖለቲካ ምህዳሩ ተስፋ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አዲስ አበባ ጉሌሌ የሚገኘውን ዋና ቢሮውን በትናንትናው እለት በተከናወነ ስርዓት በይፋ መክፈቱን አመልክቷል፡፡
የፓርቲው ዋና ቢሮ ከተዘጋ ከአምስት ዓመታት ግድም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መከፈቱ በይፋ በተበሰረበት በትናንትናው እለት ቤጽህፈት ቤቱ በተዘጋጀ ስርዓት ንግግር ያደረጉት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከቢሮው መዘጋት ጀምሮ ያለፉትን አምስት ዓመታት ፓርቲው ያለፈበት የፖለቲካ አጣብቂኝ እጅጉን ከባድ ነበር ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባ ጉሌሌ የሚገኘውየኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ቢሮ በ2012 ዓ.ም. ሃምሌ ወር ተዘግቶ ከአምስት ዓመታት ግድም በኋላ ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሮው በይፋ ሲከፈት በፓርቲው በተዘጋጀ ስነስርዓት ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እና ተጋባዥ እንግዶች ታድመው ነበር፡፡
በስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ ያለፉትን ዓመታት መራር ያሉትን አጣብቂኝ የተሞላበት የፖለቲካ ሁኔታ ማሳለፉን በመግለጽ “ኦነግ የሚቆም ትግል ግን አልጀመረም” ሲሉ የፓርቲያቸው ዓላማ ከግብ እንደሚደርስ ተናግረዋል፡፡ አቶ ዳውድ ፓርቲያቸው በ2011 ዓ.ም. ወደ አገር ቤት መመለሱን ተከትሎ ቢሮውን ከፍቶ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደጀመረ የተለያዩ ፈተናዎች እንደገጠሙትም ለታዳሚያኑ አስረድተዋል፡፡ “ከዚህ ቢሮ የስራ አስፈጻሚ አባሎቻችን ለስራ መንቀሳቀስ ላይ ሳሉ እነ ጀቤሳ ገቢሳ እና የፖለቲካ አመራር የነቡት ዶ/ር ቡሊ ኤጄታ መንገድ ላይ ተይዘው ነው ወደ እስር ቤት የተወሰዱት” ብለዋል፡፡ አቶ ዳውድ አክለውም መሰል ሁኔታዎችን እያስተናገድን ወደ ምርጫ ማምራት ከባድ መሆኑን ብንረዳም በትዕግስት እና በጥብቅ ስነምግባር እንቅስቃሴያችንን ብንቀጥልም የካቲት 2012 ዓ.ም. ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የፓርቲያችን ስራ አስፈጻሚ አባል ጃል አብዲ ረጋሳ፣ የጽህፈት ቤታችን አማካሪ ዶ/ር ሽጉጥ ገለታ፣ እንዱሁም ጃል ኬኔሳ አያና፣ ጃል ሚካኤል ቦረን ጠዋት ማለዳ በተኙበት ገብተውባቸው ነው የያዙዋቸው፡፡ በተለይ ጃል አብዲ ተተኩሶባቸውም ነበር፡፡ በኋላ ሌሎቹ በመሃል ሲፈቱ ጃል አብዲ በዚያው በእስር ቀጥለው አሁን ባለፈው ጥቅምት ከሌሎች አመራሮቻችን ጋር ነው ከአምስት ወይም ስድስት ዓመታት በኋላ የተፈቱት ብለዋል፡፡
በዚያው ዓመት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎም በተፈጠረው አለመረጋጋት ሌሎች የፓርቲው አመራሮች በተለይም አቶ ዳዊት አብዴታ እና ለሚ ቤኛ ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው መታሰራቸውን የገለጹት አቶ ዳውድ ፓርቲው የታሰሩት አመራሮቹ እንዲፈቱለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታውን እያስገባ ስራውን በትዕግስት ለመቀጠል ጥረት አድርጎም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህን ወቅት ኦነግ በጎርጎሳውያኑ 1991 የገጠመውን ከአገር ገፍቶ የማስወጣት ታሪክ እንዳይደገም ስጋትም እንደነበር ገልጸው፤ ጽህፈት ቤታቸውም የተዘጋበትን አጋጣሚ አስታውሰዋል፡፡ “መጀመሪያ ሃምሌ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በመኖሪያ ቤታችን በአስገዳጅ ሁኔታ እንድንቆይ በፖሊስ ከተገደድን በኋላ በማግስቱ ወደ ቢሮያችን ስንመጣ ሌላ ሊቀምንበር ተሹሟል የሚል ጨምሮ የተለያዩ ግርግር ነበር፡፡ አባሎቻችን ስሜታዊ እንዳይሆኑ አረጋግተን ፖሊስ መጥቶ ይህን ለምን አደረገ የሚውን እንጠይቃለን ብለን መረጋጋትን ነበር የመረጥነው፡፡ እንደገና በማግስቱ ወደ ቢሮአችን ስንመለስ የፖሊስ ኃይል መጥቶ በሃይል ቢሮአችንን ለቀን እንድንወጣ ተደረገ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ በአባሎቻችን እና ሌሎችም አካላት ብርቱ ጥግልና ጥረት በተለይም በምርጫ ቦርድ ጥረት አሁን ይህ ቢሮ የተከፈተ ማለት ነው” ብለዋል፡፡
በትናንትናው የዋና ቢሮ መክፈቻ ስርስርዓቱ ላይ አክለው ማብራሪያ የሰጡት ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በመሰረቱ በሰላማዊ የትግል ስልት እንደሚያምን እና ቀዳሚው ምርጫው መሆኑን ገልጸው፤ ወደ የትጥቅ ትግል የወሰዳቸው ለሰላማዊ ትግል አመቺ ሁኔታ ባለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ ከመጫና ቱለማ ምስረታ ጀምሮ የነበረው ውጥን ሰላማዊ ትግል ማድረግ ነው ያሉት አቶ ዳውድ አሁን መልሶ የተከፈተውን ቢሮ ጨምሮ በመላው ኦሮሚያ በርካታ ጽህፈት ቤቶቻቸው መዘጋታቸውንም አስረድተዋል፡፡ “በተለያዩ ቦታዎች ያሉ የድርጅቱ ጽህፈት ቤቶች በነቀምት፣ ባሌ፣ ኢሉባቦር እና ሌሎችም አንዳንዶቹ በውስጡ ያሉ የምንጠቀምባቸው እቃዎች ተሰባብረው ሌሎችም ተወስደው በዚያ መልኩ ነው ፓርቲው እንቅስቃሴ እንዳያደርግ በሃይል በግፊት ከምርጫም ጭምር የወጣው፡፡ ፓርቲያችን ከብሔራዊ ምክክርም ራሱን ያገለለው የተቋሙ አመሰራረት ገለልተኝነት ላይ ከመነሻው ስላልረካን እንጂ ብሔራዊ ምክክር እንደሚያስፈልግ በጽኑ እናምናለን፡፡ ሀቀኛ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ትግልም ግቡን ሳይመታ አይቆምም፡፡ ይህ ደግሞ ዳውድ ስላሌ ሳይሆን ህዝቡ የደፈረሰው ሰላምና ሀቁን መመለስ ስለሚፈፈልግ ነው” ብለዋልም፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በ2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የመጣውን መንግስታዊ ለውጥ ተከትሎ ለ27 ዓመታት ተዘግቶ የነበረውን የአዲስ አበባውን ጽህፈት ቤቱን በ2011 ዓ.ም. ብከፍትም በኋላ ላይ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ጽህፈት ቤቱ ከ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ ተዘግቶ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር