1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦፌኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያስተላለፈው ጥሪ

ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2016

በኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፋው ግጭት በሰላማዊ መንገድ ብቻ እልባት እንዲያገኝ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፈኮ) ጥሪ አቀረበ። ፓርቲው ባስተላለፈው ጥሪ «አገራዊ ችግሮች በአንድ ገዢ ፓርቲ ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ሁሉም ተፋላሚ አካላትን ጭምር የሚያካትት አገራዊ ምክክር እንዲደረግ»ም ጠይቋል።

ኦፌኮ
የኦፌኮ የማዕከላዊ ኮሚቴ ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባ ተሳታፊዎች በከፊል ምስል Seyoum Getu/DW

የኦፌኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያስተላለፈው ጥሪ

This browser does not support the audio element.

የኦፌኮ ሦስተኛው መደበኛ ስብሰባ ጭብጥ

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፈኮ) ከሐምሌ 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሥራ ክንውን መገምገሙን ብሎም የፓርቲውን የየአካባቢ እንቅስቃሴ መመልከቱን አሳውቋል። ፓርቲው በአሁን ወቅት የአገሪቱ ጊዜያዊ ሁኔታን ገመገምኩ ብሎ ባወጣው መግለጫ ሕገመንግሥቱን የሚጻረሩ ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በሚካሄደው ጦርነትም የጅምላ ግድያዎች እና እስር ብሎም የቤቶች ቃጠሎ፣ ስርዓታዊ ሙስና መንሰራፋቱንና ከጦርነቱ የተነሳ በተዛባው የጤና ስርዓት ተላላፊ በሽታዎች መስፋፋታቸውን፤ ብሎም የሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት መክፋቱን በአቋሙ አስረድቷል።

ከአዲስ አበባ ውጪ ከምዕራብ ሸዋ እና አርሲ ዞኖች ውጪ ሁሉም ጽሕፈት ቤቶች በመንግሥት ተዘግቶብኛል ያለው ኦፌኮ ከ200 በላይ ጽሕፈት ቤቶቹ በኦሮሚያ ተዘግተው በመዝለቁ እስካሁንም ፖለቲካዊ ሥራውን በአግባቡ ለመሥራት መቸገሩን በዚሁ አመልክቷል። ፓርቲው በየመዋቅሩ ያሉ አመራሮቹ በኦነግ-ኦነሰ ደጋፊነት ተከሰው ይሰቃያሉም ነው ያለው።

በኦሮሚያ ክልል 22ቱም ዞኖች ግጭት ጦርነቱ መኖሩን ገምግሜያለሁ ያለው ፓርቲው በዚህም የቤቶች ቃጠሎና የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት መቀጠፍን ጨምሮ በርካታ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸማሉ ብሏል። ለዚህም ደግሞ በጉልህው የመንግሥት መዋቅሮች ላይ ወቀሳ ሰንዝሯል። በዚህን ወቅትም «ሁሉንም ተፋላሚዎች እኩል ለምን አተቹም?» ተብለው በጋዘጠኞች የተጠየቁት የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና፡ «ኳስ ያለው በመንግሥት እጅ ነው» በማለት ምላሻቸውን አብራርተዋል። «ኦነግን የፈጠሩ ዳውድ ኢብሳን አዲስ አበባ ውስጥ አስቀምጠው የኦነግ-ኦነሰ ሠራዊትን ከሚመራው መሮ ጋር ታንዛንያ ሄዶ መወያየት አያስፈልግም ነበር» ያሉት ፕሮፈሰር መረራ መንግሥት ነጻና ገለልተኛ የምርጫ ተቋም እንኳ ለመገንባት ሙሉ ቁርጠኛ ቢሆን «ለድርድር አንቀመጥም ያሉትን አካላት አፋችንን ሞልተን የማንቃወምበት ምክንያት የለም» በማለትም መንግሥት ለሁሉ አቀፍ እና ገለልተኛ ውይይቶችና ድርድሮች እራሱን እንዲያዘጋጅ ጠይቀዋል።

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የኦፌኮ ሊቀመንበርምስል Seyoum Getu/DW

የፓርቲው የአቋም መግለጫ

ኦፌኮ የፓርቲውየሥራ ክንውን እና ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይን እንደ ፖለቲካ ፓርቲው ከገመገመ በኋላ የአቋም መግለጫውን አውጥቷልም። በዚህም ኦፌኮ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚታገል መረዳቱንና ለዚህም ከመላው የኦሮሞ እና የኢትዮጵያ ብሔርብሔረሰብ ጋር ለመታገል ቁርጠኛ መሆኑን አሳውቋል። ኦፌኮ በሥልጣን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ ሁሉንም ችግሮች በራሱ እንደማይፈታና ሁሉም ተቀናቃን ኃይሎች ችግሮቹን አይተው ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ አብረው እንዲሰሩ ጥሪውን አስተላልፏል።

«ጦርነት እየተካሄደ አገራዊ ምክክር ማድረግ አይቻልም» ያለው ኦፌኮ አገራዊ ምክክር ለማድረግ በመላው አገሪቱ ግጭት ቆሞ ሁሉም ተፋላሚዎች የተሳተፉበት ምክር እንዲደረግ ጠይቋል። ፕሮፌሰር መረራ ፓርቲያቸው በአገራዊ ምክክር ሂደቱ እስካሁን ያልተሳተፈበትን ምክንያት ተጠይቀውም፤ «የኮሚሽኑ ገለልተኝነት እና አካታችነት በጉልህ በማጠያየቁ ነው» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ኦፌኮ በአገሪቱ በሰላማዊ መንገድ ለሚታገሉ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ለአገሪቱ የጸጥታ መዋቅሮች እና ለሕዝብ ተወካይ እንደራሴዎች ባስተላለፈው ጥሪም «እየመጣ ነው» ካለው አገራዊ አደጋ ለመዳን ሁሉም ተቀምጠው ዘላቂ እልባት ለማምጣት ቁርጠኛ እንዲሆኑ ጠይቋል። ፓርቲው ለሁለት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው በተለያዩ ምክንያቶች የተጓደሉ የፓርቲውን የሥራ አስፈጻሚ አባላት በአዳዲስ ሽግሽጎች ማሟላቱን ገልጿል። በዚሁ መሠረትም በአቶ በቀለ ገርባ ምትክ የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር በማድረግ አቶ ሙላቱ ገመቹን ሾሟል። ኦፌኮ ሌሎች የሥራ አስፈጻሚ አባላት ሹመቶችንም ሰጥቷል።

 ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW