የኦፌኮ እና ኢዜማ መግለጫዎች
ሰኞ፣ ኅዳር 16 2017ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በአገሪቱ አላባራ ያለው የፀጥታ መደፍረሶች እልባት እንዲያገኙ ነፍጥ አስቀምጦ መወያየት እንደሚያስፈልግ ሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች በተናጥል ባወጡት መግለጫ ጠየቁ፡፡መግለጫውን ካወጡት የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በተዋረድ መጣ ያለው የመንግስታት ከዴሞክራሲ ጋር መቃረን ዋናው ምክንያት ነው ሲል፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በፊናው የዘውግ ፖለቲካ ለእልቅቶች ትልቁ ምክንያት ነው ብሏል፡፡
የኦፌኮ ማሳሰቢያ
በኦሮሚያ ክልል ሰላሌ ዞን በደራ ወረዳ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለዉን ግድያና ማፈቀናል ተቃውሞ መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ “በታሪኩ ለመብቱና ነፃነቱ በእምቢ ባይነታቸዉ የሚታወቁ ታጋዮችን በአፈራዉ የሰላሌ ኦሮሞ ሕዝብ” ላይ በደል ተደጋግሟል ነው ያለው፡፡ አከባቢው ላይ ተፈጸመ ያለውን በደል በስፍራው የሚንቀሳቀሱ አማጺያን እና መንግስት ማረጋገጣቸውን ያነሳው ኦፌኮ በአከባቢ በስፋት የሚከሰተውን ሰብዓዊ ቀውስ በተመለከተ ግን አንደኛው አካል በሌላኛው ወገን ላይ ያላክካል ሲል ተችቷል፡፡ የሆነ ሆኖም መንግስትም ሆነ በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ አማጺያን በምንም መልኩ ንጸሓን ላይ የሚወስዱት እርምጃ ተቀባይነት የለዉም ብሏልም፡፡ በዚሁ ላይ ለዶይቼ ቬለ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የፓርቲው ዋና ጸሃፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ “የችግሩ ምንጭ በተዋረድ የመጣው የኢትዮጵያ የፖለቲካ አመራር ወይም መንግስት ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑ” ነው በማለት የአሁናዊ አለመረጋጋቶች ዋነኛ መንስኤ የህዝብን ፍላጎት ማዕክል አድርጎ አለመስራት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ኦፌኮ በመግለጫው አክሎም “አንዱ ሌላዉን ሰበብ በማድረግ” ንጹሓን ዜጎች ላይ እየተፈራረቁ ጉዳት ያስከትላሉ በማለት “የሕዝብን ደም በከንቱ ማፍሰስ በአስቸኳይ መቆም ይኖርበታል” ሲል አሳስቧል፡፡ በኢትዮጵያና በመላዉ ዓለም ለሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጎችና ወዳጆች ላሏቸውም ህዝብ ላይ ይፈጸማል ያለውን ግፍ እንዲቃወሙት ጠይቋል፡፡
የኢዜማ መግለጫ
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በበኩሉ ሰሞነኛውን አለመረጋጋት ተከትሎ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፤ “ባለፉት ጥቂት ዓመታት ማንነትን መሰረት አድርገው በስፋት የተፈጸሙ ለአዕምሮ የሚክብዱ” ያሏቸው በደሎች ኢትዮጵያውያን መሃል የነበረውን መልካም እሴት ለመሸርሸር ሆን ተብለው የተፈጸሙ ናቸው ብሏል፡፡ ኢዜማ ለመንግሥት ያስተላለፈው ማሳሰቢያ
ለችግሩም ዋነኛ መንስኤ በአገሪቱ እየተተገበረ ያለው የዘውግ ፖለቲካ ፍሬ ነው ሲል የገለጸው ኢዜማ የመንግስት የአስተዳደር ስርዓት እንዲጤን ጠይቋል፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ
ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኝወርቅ በሰጡን ተጨማሪ ማብራሪያም፤ “ዘውግ ላይ የተመሰረተው ስርዓት የፈጠረውን ሁኔታ መሰረት አድርጎ ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አከባቢዎች ላይ የተፈጸሙ ብሔር ተኮር አሰቃቂ ድርጊቶች” በተለይም በመንግስት መግለጫዎች ላይ በመንተራስ መግለጫ ማውጣቱን አስረድተዋል፡፡ ዜጎች መሰል ተግባራትን በአንድነት እንዲያወግዙ፣ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እና በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጪ መረጃዎች ጥንቃቄ እንደሚያሻቸውም ነው ያመለከቱት፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶቹ ያስቀመጡት እልባት
ከአሁናዊው አጠቃላይ ሁለንተናዊ ቀውሶች ለመውጣት መፍትሄ ነው ያሉትንም የፖለቲካ ድርጅቶቹ ባለስልጣናት በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡ “ማንኛውም ወገን መሳሪያን ለማስቀመጥ መነጋገር ቀዳሚው እልባት” ያሉት ፖለቲከኛ ጥሩነህ ከዚህ ውጪ ምንም መንገድ እንደሌለ አመልክተዋል፡፡ ዶ/ር ሙሉዓለም በበኩላቸው፤ “ባለፉት ጢቂት ዓመታ እንኳ በምንከተለው የፖለቲካ ስርዓት ምክንያት ከተጋደልንበት ሁኔታ ተምረን ቆም ብለን በማሰብ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በመምጣት አማራጮችን መመልከት አለብን” በማለት መተማመን ላይ የተመሰረተ መንገድ መምረጥ እንደሚስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የኦፌኮ አመራሮች እስራት፤ የፓርቲው መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ተፈጸመ የተባለውን ዘግናኝ ግድያ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የፋኖ ታጣቂዎችን በድርጊቱ ከሶ፤ በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ የሏቸው “ሸነ እና ፋኖ” በማለት ሁለት የታጠቂ ቡድኖችን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ እና የአከባቢውን ጸጥታ በማወሳሰብ ከሷል፡፡ ክሱ ከቀረበባቸው ታጣቂዎች አንዱ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ መንግስትን ጨምሮ በአከባቢው የታጠቁ ተዋንያን መበራከት ለሚስተዋለው ህዝብ ላይ ለሚከሰት ቀውስ መንስኤ ነው ብሏል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ