1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የከሸፈው የቤኒን መፈንቅለ መንግሥት

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 4 2018

ቤኒን ውስጥ የመጨረሻው መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደው በጎርጎሪዮሳዊው 1972 ነበር። በዚህም ምክንያት ላለፉት ጥቂት የማይባሉ አስርት ዓመታት ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ዴሞክራሲያዊ አስተዳደሯ እያደገ በመሄድ ላይ ነው የምትባል ሞዴል ሆና ቆይታለች።

በቤኒን የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች በከፊል
በቤኒን የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች በመንግሥት ቴሌቪዝን መግለጫ ሲሰጡምስል፦ Benin TV/REUTERS

የከሸፈው የቤኒን መፈንቅለ መንግሥት

This browser does not support the audio element.

 

« እሑድ ዲሴምበር 7 ቀን 2025 የተሰበሰበው «ወታደራዊው የመልሶ ማቋቋም ኮሚቴ» CMR፤ የሚከተለውን ተነጋግሮ ወስኗል፤ ሚስተር ፓትሪክ ታሎን ከሪፐብሊኩ የፕሬዝደንትነት ቢሮ ይነሱ።»

እራሱን ወታደራዊ የመልሶ ማቋቋም ኮሚቴ የተባለው ስብስብ የቤኒን ፕሬዝደንት ላይ የከሸፈ መፈንቅለ መንግሥት ባካሄደበት ወቅት ከኮሚቴው አባላት አንዱ ለሕዝብ በቴሌቪዥን ቀርቦ ያስተላለፈው መልእክት ነበር። በቡድን የተባሰቡ ወታደሮች የቤኒን መንግሥታዊ መገናኛ ብዙሃንን በመቆጣጠር ይህን መግለጫ ሲሰጡ፤ የምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ዜጎች በድንጋጤ ተዋጡ። ፍርሃቱን ያባባሰው ሌላ ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር ተቀጨ የሚለው ስጋት ነው። ሆኖም ወዲያው የቤኒን መንግሥት ኃይሎች የወሰዱት ፈጣን እርምጃ መፈንቅለ መንግሥቱን ቀልበሰና ስጋቱን አረገበው። እንዲያም ሆኖ የፖለቲካ ተንታኞች ሁኔታው አሳሳቢ ነው እያሉ ነው።

ባለፉት ሦስት ወይም አራት ዓመታት በበርካታ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት በተደጋጋሚ ወታደራዊ መኮንኖች በየብሔራዊ ቴሌቪዥኑ መስኮቶች እየቀረቡ ሥልጣን ስለመቆጣጠራቸው ሲናገሩ ታይቷል። ቤኒን ውስጥ የመጨረሻው መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደው በጎርጎሪዮሳዊው 1972 ነበር።በዚህም ምክንያት ላለፉት ጥቂት የማይባሉ አስርት ዓመታት ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ዴሞክራሲያዊ አስተዳደሯ እያደገ በመሄድ ላይ ነው የምትባል ሞዴል ሆና ቆይታለች። ፕሬዝደንቱ በመጪው ሚያዝያ ወር ሥልጣን ይለቃሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነበር።

ታዲያ የከሸፈወን መፈንቅለ መንግሥት ምን አመጣው?

የከሸፈውን የመንግሥት ግልበጣ የሞከሩት ወታደሮች ለእርምጃቸው ምክንያት ያደረጉት በሰሜን ቤኒን አካባቢ እየተበላሸ ነው ያሉትን የጸጥታ ሁኔታ፤ በጦር ኃይሉ ውስጥ እየተሰጠ ነው ያሉትን ኢፍትሀዊ የሥልጣን እድገት እንዲሁም መንግሥት መሠረታዊ መብቶችን እያፈነ ነው የሚል ነው። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታን ሪግስ ሾንክፐ ግን ምክንያቱን አይቀበሉትም። 

«ቤኒንም ሆነ የትም ቢሆን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በፍጹም መፍትሄ አይደለም፤ አይሆንምም። ቤኒን በአሁኑ ጊዜ በዴሞክራሲ አቅጣጫ እያመራች ነው፤ ከጉድለት ብቻ ሳይሆን ስኬትም ጋር። እኛ በማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ሽግግር ውስጥ ያለን ሀገር ነን።»

ሌላዋ የጸጥታ ጉዳይ ተንታኝ ቤቨርሊ ኦቺያንግ  የከሸፈውን መፈንቅለመንግሥት የሞከሩት ወታደሮች ለምን እስከ ቀጣዩ ምርጫ መጠበቅ አቃታቸው ሲሉ ይጠይቃሉ። ተቋማት እንዳይሰሩ ስታስተጓጉል ምርጫው በታሰበለት ወቅት እንዳይካሄድ ማድረግህ መሆኑን መረዳት አለብህ የሚሉት ኦቺያንግ፤ በዚህ መሀል ሕዝብ እንዳይረጋጋ በማድረግ ማለቂያ የሌለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሊቀሰቅስ እንደሚችል ነው ያመለከቱት። 

ከመፈንቅለ መንግሥትና ድንገተኛs ስደት የተረፉት የቤኒን ፕሬዝደንት ፓትሪክ ታሎን ምስል፦ Ute Grabowsky/photothek/IMAGO

ሕዝብ ያስቆጣው የሕገመንግሥት ማሻሻያ

ባለፈው ወር የቤኒን ፓርላማ የፕሬዝደንቱን እና የአስፈጻሚውን አካል ሥልጣን ከአምስት ዓመት ወደ ሰባት ዓመት የሚያራዝመውን ረቂቅ አጽድቋል። ሆኖም የምርጫ ዘመን ከሁለት ዓመት እንዳያልፍ የሚደነግገውን አልቀየረም። በዚህ መሠረትም ፕሬዝደንት ታሎን በመጪው ሚያዝያ ከሚካሄደው ምርጫ በኋላ ከሥልጣን እንደሚለቁ ይጠበቃል። የቀረበው ረቂቅ ደንብ፤ ሴኔት አባላትን ቁጥር ከ25 ወደ 30 ከፍ እንዲል ይጠይቃል። ይህ ደግሞ የቀድሞ የሀገር መሪዎች እና ፕሬዝደንቶችን ያካትታል። እንዲያም ሆኖ ይህ ማሻሻያ የሕገ መንግሥታዊውን ፍርድ ቤት ይሁንታ ይጠብቃል።

የተቃውሞ ፖለቲካ ቡድኖች በቀረበው ማሻሻያ አለመደሰታቸውን ገልጸዋል። የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎችም የእነሱን ቅሬታ እንደተጠቀሙበት የፖለቲካ ተንታኞች ይገምታሉ።

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ቢከሽፍም ድርጊቱ በአፍሪቃ ሕብረትም ሆነ በምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ትብብር ኤኮዋስ በጥብቅ ተወግዟል። የቤኒንን ጦር ኃይል አፋጣኝ ጣልቃ ገብ እርምጃ በመደገፍም ናይጀሪያ የጦር ጀቶቿን እስከመላክ ደርሳለች። የቤኒንን መንግሥታዊ ቴኔቪዥንና ራዲዮ ተቆጣጥረው የነበሩ ያመጹ ወታደሮችንም ዋና ከተማ ኮቶኑ ላይ መደብደቧ ነው የተገለጸው። ኤኮዋስ በበኩሉ የጋና፤ ናይጀሪያ፤ የኮት ዴቪዋርና ሱራሊዮን እግረና ወታደሮችን ለዚሁ ተግባር ማሰማራቱን አስታውቋል። አካባቢው ላለፉት አምስት ዓመታት በመፈንቅለ መንግሥት ሲተራመስ መሰንበቱ ኤኮዋስን አሳስቦታል ነው የተባለው። ማሊ፤ ቡርኪናፋሶ፣ ኒዠር በቅርቡ ደግሞ ጊኒ ቢሳዎ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባቸው ሃገራት ናቸው። የተረጋጋች ስትባል የኖረችው ቤኒን ላይ ይህ እንዲደገም ኤኮዋስ አልፈቀደም። የታሎን መኖሪያ እና ፕሬዝደንታዊ ጽሕፈት ቤት በመፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹ ኃይሎች ጥቃት ሲከፈትበትና ያመጹት ወታደሮችም ያሰቡትን ለማሳካት ሰላማዊው ሕዝብ ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ በመታመኑ ናይጀሪያ እርምጃ እንድትወስድ ተፈቀደ።

መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፉ ያስደሰታቸው የፕሬዝደንት ታሎን ደጋፊዎች በዋና ከተማ ኮቶኑ አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን አሰምተዋልምስል፦ Charles Placide Tossou/REUTERS

በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ከቤተመንግሥት ወጥተው የነበሩት ፕሬዝደንት ፓትሪክ ታሎን ሀገሪቱን አረጋግቶ እሳቸውንም ወደ ስፍራቸው የመለሳቸውን የቤኒን ጦር ኃይል ተግባር በይፋ ወጥተው አመስግነዋል። ከጦር ኃይሉ ጋር በመሆን አማጽያኑን ከያሉበት እንደሚያጸዱም በአደባባይ ተናግረዋል።

«የጦር ኃይላችን እና መሪዎቹ በሪፑብሊካዊነት ለሀገራቸው ያሳዩትን ታማኝነት ላደንቅ እወዳለሁ። ከእነሱ ጋር በጥንካሬ እንቆማለን፤ ሥልጣናችንንም በድጋሚበመያዝ፤ የቀሩት አማጽያንን የሚገኙበትን ጉራንጉር እናጸዳለን። ይህ ቁርጠኝነት እና መነሳሳት የተሞከረውን ጀብደኝነት በመቀልበስ ሀገራችንን እንድናድን አድርጎናል። ይህ ክህደት ከቅጣት አያመልጥም።»

ምንም እንኳን የቤኒን ሕዝብ በመፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፍ ቢደሰትም፤ በፕሬዝደንት ታሎን ላይ ግን ቅሬታ አለው። በሀገሪቱ የብዙኀኑ ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት ተቃዋሚ ፓርቲ ሌስ ዴሞክራቲ በመጪው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እንዳይሳተፍ ታግዷል። ይህም ብዙዎችን አስከፍቷል። ሆኖም ግን ሕዝቡ ተቃውሞውን መግለጽ የተለማመደው በኃይል አመጽ ሳይሆን በፒለቲካዊ ሂደት እና በሲቪል እንቅስቃሴዎች ነው። እናም ይህ የሰከነው የቤኒኖች የፖለቲካ ባህል ፕሬዝደንት ፓርትሪክ ታሎን ከድንገተኛ ስደት አትርፏል። ያመጹባቸውም ለጊዜው ተበታትነዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW