1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የከሸፈው ድርድር እና የቀጠለው የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 5 2018

አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ሲያካሂዱ የነበረው የተኩስ አቁም ድርድር ያለምንም ውጤት ተጠናቋል። ትናንት እሁድ የተጠናቀቀው ንግግሩ ዓለማቀፉ ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ያስከተለው ጦርነቱ እንዲያበቃ አንዳች ተስፋ ያስገኛል ተብሎ ቢጠበቅም ከተስፋነት አልዘለለም።

የከሸፈው ድርድር እና የቀጠለው የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ
የከሸፈው ድርድር እና የቀጠለው የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስምስል፦ REUTERS

ድርድሩ ከሽፏል ፤ ጦርነቱ ያገረሽ ይኾን ?

This browser does not support the audio element.

አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ሲያካሂዱ የነበረው የተኩስ አቁም ድርድር ያለምንም ውጤት ተጠናቋል። ትናንት እሁድ የተጠናቀቀው ንግግሩ ዓለማቀፉ ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ያስከተለው ጦርነቱ እንዲያበቃ አንዳች ተስፋ ያስገኛል ተብሎ ቢጠበቅም ከተስፋነት አልዘለለም። ከስምምነት ላለመድረሳቸው ሁለቱም ሃገራት በተለጠጡ ፍላጎቶች መቅረባቸው እና አንዱ ሌላዉን ተጠያቂ ማድረጋቸው በምክንያትነት ተጠቅሷል። በጦርነቱ ሁነኛ ሚና የነበራት እስራኤል በበኩሏ በኢራን ላይ ስትፈጽመው የነበረው ጥቃት ከተገታ በኋላ ፊቷን ወደ ሊባኖስ አዙራለች ። መዲናዪቱ ቤይሩትን ጨምሮ የደቡባዊ ሊባኖስ መንደሮች ወደ ፍርስራሽነት እየተቀየሩ ሲሆን ሊባኖሳዉያን መንግስታቸው ከእስራኤል ጋር ለመደራደር ፍላጎት ማሳየቱን ተከትሎ ለተቃዉሞ አደባባይ ወጥተዋል። የመካከለኛው ምስራቅ አሁንም ያተኩሳል። 

ኢስላማባድ ምናልባትም በታሪኳ እጅግ በተራራቀ ጽንፍ የቆሙ እና ለአመታት በጠላትነት ሲፈላለጉ የነበሩ ጦረኞችን የማሸማገል ዕድል ስታገኝ ይህ በርግጥ የዲፕሎማሲ ሽልማት የማሸነፍ ያህል ነው የሚሆንላት። የሴሬና ሆቴል እና የኢስላማባዱ ጂናህ የስብሰባ ማዕከልም ኃያላኑን ከወዲያ ወዲህ ለማሸማገል ሁነኛ ሚና መጫወታቸው ነው የተነገረው። አሜሪካ እና ኢራንም ከኢራኑ የአቢዮት ፍንዳታ ወዲህ ፊት ለፊት ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው። በርግጥ ሁለቱም ወደ ድርድር የሄዱት ወደው አይደለም። በእነርሱ ጦስ የዓለም ኤኮኖሚ ተናግቷል። የመካከለኛው ምስራቅ ከእስከ ዛሬው ሁሉ የከፋ ቀውስ አስተናግዷል። ዉጤት ያጣው ድርድር ሌላ የጦርነት ስጋት የእስካሁኑን ቀውስ የሚያባብስ ሌላ መዘዝ ይዞ እንዳይመጣም ገና ከወዲሁ አስግቷል።


እስቲ የድርድሩ መክሸፍ እና ስለሚከተለው ስጋት በጥቂቱ እንመልከት። 
በድርድሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የአሜሪካ ባለስልጣናት ንግግሩ የፈረሰው ኢራን የኒውክሌርፕሮግራሟን ለመተው ፈቃደኛ ባለመሆኗ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል። የኢራን ባለስልጣናት ደግሞ ለውይይቱ መቋረጥ ዝርዝር ነጥቦችን ሳያጋሩ አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል።
የአሜሪካውን ተደራዳሪ ቡድን የመሩት ምክትል ፕሬዚደንቱ ጄዲ ቫንስ በንግግሩ የአሜሪካን ፍላጎት ለኢራን በግልጽ መንገራቸውን ነው ያስታወቁት። 

«እንግዲህ ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ ሳንደርስ ነው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የምንመለሰው፤ ቀይ መስመሮቻችን ምን እንደሆኑ፣ በምን ጉዳዮች ላይ ልንስማማላቸው እንደምንችል እና በምን ጉዳዮች ላይ ደግሞ ልንስማማላቸው እንደማንችል በግልጽ አስታውቀናቸዋል።»


ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዲጄ ቫንስ አሜሪካ አሁንም ኢራን የኒኩልየር የጦር መሳሪያ ባለቤት ሆና ማየትን እንደማይፈልጉ እና በዚህ ረገድ የኢራን ቁርኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገቡበትን ሃሳብ አጋርተዋል።
“የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንደማይፈልጉ፣ እንዲሁም በፍጥነት የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችሏቸውን መሣሪያዎች እንደማይፈልጉ የሚያረጋግጥ ግልጽ ቁርጠኝነት ማየት አለብን።”
የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የመሩት የፓርላማው አፈ-ጉባኤ መሐመድ ባገር ቃሊባፍ በበኩላቸው በማህበራዊ መገናኛ ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት  ዩናይትድ ስቴትስ 'የእኛን እምነት ማግኘት ትችል እንደሆነ እና እንዳልሆነ የምትወስንበት ጊዜ አሁን ነው' ሲሉ ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጄዲ ቫንስ አሜሪካ አሁንም ኢራን የኒኩልየር የጦር መሳሪያ ባለቤት ሆና ማየትን እንደማይፈልጉ እና በዚህ ረገድ የኢራን ቁርኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገቡበትን ሃሳብ አጋርተዋል።ምስል፦ Jacquelyn Martin/AP Photo/picture alliance


የኢስላማባዱ ድርድር በ,ርሳቸው አቋም ላይ ብዙም ለውጥ እንደማያመጣ በድርድሩ ወቅት ጭምር ሃሳባቸውን ሲያጋሩ የነበሩት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከድርድሩ መክሸፍ በኋላ ትናንት እሁድ በትሩዝ ገጻቸው ላይ ያጋሩት መልዕክት በርግጥ አስደንጋጭ ሆኗል። 
ትራምፕ በዚሁ መልዕክታቸው አሜሪካ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ለማለፍ ለኢራን የከፈለ ማንኛውንም መርከብ እንደምታግት አስታውቀዋል።
በዓለም ላይ «ምርጡ » ያሉት ባህር ኃይላቸው ኢራን በባህር ወሽመጡ ያጠመደቻቸውን ፈንጂዎች ማጽዳት ይጀምራል ያሉት ትራምፕ፤ ባህር ኃይሉ ´´መርከቦችን ማገትን ጨምሮ ተልዕኮውን በይፋ ይጀምራል`´ ብለዋል።

ያለፉትን 40 ቀናት በአሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን መካከል የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ቀጠናውን  ቀውስ ውስጥ ከቷል። በጦርነቱ በርካታ ሰዎች የተገ,ደሉባት ኢራን ብርቱ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ማስተናገዷ ተዘግቧል። ጦርነቱ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ መሪዋን እና ከፍተኛ የጦር ሹማምንቷ የተገደሉባትኢራንይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ 3753 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ይፋዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ይገኙበታል ነው የተባለው።ኢራን ውስጥ የኢንተርኔት መስተጓጎል በመኖሩ ትክክለኛውን መረጃ ማግኘት አዳጋች በማድረጉ ትክክለኛውን የጉዳት አሃዝ ማግኘት አዳጋች ማድረጉን ነው የጦርነት መረጃዎችን የሚያቀርቡ ገለልተኛ ተቋማት የሚገልጹት። 

ያለፉትን 40 ቀናት በአሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን መካከል የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ቀጠናውን  ቀውስ ውስጥ ከቷልምስል፦ Farnood/SIPA/picture alliance


በጦርነቱ የኢራንን ያህል ባይሆንም በእስራኤል እና በቀጣናው ባሉ የአረብ ሃገራት ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል። እስራኤል 19 ሲቪላዉያን እንደተገደሉባት ይፋ ስታደርግ የኢራን የበቀል ርምጃ ገፈት ቀማሽ የሆኑት የአረብ ሃገራትም የከፋ ኤኮኖሚያዊ ጉዳት ያስከተሉ ጥቃቶችን ሲያስተናግዱ ሰብአዊ ጉዳትም ደርሶባቸዋል። የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ የሆነቸው ሌላዋ ሀገር ሊባኖስ ስትሆን እስራኤል ከኢራን ጎን ለጎን የሊባኖሱን ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላን ዒላማ ያደረጉ ናቸው ባለቻቸው ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት መዲናዋ ቤሩትን ጨምሮ የእስራኤል ጦር ኃይል ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ ባደረሰው ጥቃት የሄዝቦላ ታጣቂዎችን ጨምሮ 1,460 ሰዎች መገደላቸውን ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ጦርነት እንደመጀመር ቀላል አይሆንም እና   ልዕለ ሃያሏ ሀገር አሜሪካም ከፍተ|ኛ የሚባል ጉዳት ማስተናገዷ ሲገለጽ ቆይቷል። በቀጣናው ሃገራት የሚገኙ የጦር ሰፈሮቿ እንዳልነበር የሆኑባት አሜሪካ በጦርነቱ ወቅት 13 ወታደሮቿ ተገድለዉባታል፤  ለጦርነቱ በየቀኑ እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ስታደርግ መቆየቷንም ዘገባዎች ተመልክተዋል። ይህ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ የጦር አውሮፕላኖቿ እና በሌሎች የጦር ሰፈሮቿ ላይ የደረሱ ውድመቶችን ሳያካትት መሆኑ ነው።  ከምንም በላይ ደግሞ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ያስከተለው  በሦስት እጥፍ የዋጋ መጨመር የዓለምን ኤኮኖሚ ክፉኛ አንኮታኩቷል።

ለመሆኑ በቀጥታ በጦርነቱ ውስጥ ያሉ ሲቪሊያዉያን የድርድሩ መክሸፍ ምን ስሜት አሳድሮባቸው ይሆን የሚለውን እናስከትል ። 
ፋራድ ሲሚያ የመዲናዪቱ ቴህራን ነዋሪ ናቸው ። በርግጥ ጦርነቱን እንደሚቃወሙ ነው ለአሶሽየትድ ፕረስ የነገሩት ።
"እኔ ጦርነትን እቃወማለሁ። ድርድር የተሻለ መንገድ ነው ብዬ አምናለሁ። ኢራን በጦርነቱ ጠንክራ ተዋግታለች፣ የሚገባትንም አግኝታለች፤ ነገር ግን አሁን ውጊያው የሚቆምበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስለኛል።"
እንደዚያም ሆኖ ግን ሲሚያ የኢራንን አቋም ደግፈው ለንግግሩ መቋረጥ አሜሪካ ያቀረበችውን "ተገቢ ያልሆነ" ጥያቄ ነው ተጠያቂ አድርገዋል። 
የቴል አቪቭ ከተማ ነዋሪው እስራኤላዊቷ ላራ ካውፍ ማን እንዳሉት ከሃገራቱ የተለጠጠ ፍላጎት ተነስተው ቀድሞውኑ በድርድሩ ውጤት ይገኛል ብለው ተስፋ እንዳልሰነቁ ነው ።
«ድርድሮቹ በትክክል አንድ ነገር ይለውጣሉ ብዬ ቀድሞውኑ አላሰብኩም ነበር። ሁለቱ ወገኖች ሙሉ በሙሉ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ስለሚፈልጉ እና በእውነት ለመደራደር ፈቃደኛ የሆነ አካል ስላልታየ፣ ወደ ድርድሩ ሲገባ ብዙም ተስፋ አልነበረኝም።" ብለዋል።

የቴል አቪቭ ከተማ ነዋሪው እስራኤላዊቷ ላራ ካውፍ ማን እንዳሉት ከሃገራቱ የተለጠጠ ፍላጎት ተነስተው ቀድሞውኑ በድርድሩ ውጤት ይገኛል ብለው ተስፋ እንዳልሰነቁ ነውምስል፦ Ronen Zvulun/REUTERS


ሌላው እዚያው የቴል አቪቭ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የሶፍትዌር ኢንጂነር ዮታን የሊባኖስ ጉዳይ ለድርድሩ ዉጤት አልባናት ቦታ ሰጥተዉታል።
"ሊባኖስ በስምምነቱ ውስጥ መካተት አለባት ወይስ የለባትም በሚለው ጉዳይ፣በዩናይትድ ስቴትስእና በኢራን ፍላጎቶች መካከል፣ እንዲሁም በሁሉም ወገኖች ግቦች መካከል ልዩነቶች በመኖራቸው ጦርነቱ እንደገና ያገረሻል ብዬ እሰጋለሁ። በትክክል ሰላም ላይ የደረስን መስሎ አይሰማኝም፤ ለጊዜው ጋብ ያለ ብቻ ነው የሚመስለው።" ብለዋል። 
አሁን ጥያቄው ተስፋ የተደረገበት ድርድር ከከሸፈ በኋላ እና ኢራን እና አሜሪካ በተለይ በያዙት ግትር አቋማቸው ከጸኑ ከተፋላሚ ሃገራቱ ባሻገር የተቀረው ዓለም ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለው ያጠያይቃል። 

"ጥቂት የውሃ ፈንጂዎች ፤ እናንተ የውሃ ፈንጂዎች የምትሏቸውን ባህር ላይ ጥለዋል። እኛ ደግሞ ሁሉንም የውሃ ጀልባዎቻቸውን ድል አድርገናል። የባህር ኃይላቸው ጠፍቷል፦ 158 መርከቦች። 28 የውሃ ላይ ፈንጂ ጣይ መርከቦች፣ ፈንጂ ጣዮች ነበሯቸው አሁን ሁሉም ሰጥመዋል። ምናልባትም በውሃው ውስጥ ጥቂት ፈንጂዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እኛ እዚያ የፈንጂ ጠራጊ መርከቦች አሉን፤ የባህር ወሽመጡን እያጸዳን ነው::"
ፕሬዚዳንቱ ይህን ይበሉ እንጂ በደቡባዊ የሆርሙዝ ወሽመጥ የታዩ ሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ፈንጂ አጽጂዎች ሳይሆን እንዲሁ ተዋጊዎ መርከቦች ናቸው ። በዋሽንግተን የቅርብ ምስራቅ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት አጥኚ ፋርዚን ናዲሚ እንደሚሉት የአሜሪካ የጦር መርከቦች የኢራንን ቁመና ከመፈተሽ ያለፈ ርምጃ ይወዱ እንደሁ ጊዜ ወስዶ መጠበቅ ይበጃል ።


«ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ የባህር ኃይል አጥፊ መርከቦች  በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ለጥቂት ጊዜ ተጉዘው፣ ከዚያም ተመልሰው ወደ ኦማን ባሕረ ሰላጤ መውጣታቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች አሉ። ሁኔታው መርከቦቹ የባህር ላይ ፈንጂዎችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ማናቸውንም የኢራን ስጋቶች ምልክቶች ለመፈተሽ ሁኔታዎችን እያጠኑ እንደሆነ ያሳያል። በተጨማሪም፣ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ደቡብ አቅጣጫ፣ ለኦማን ጠረፍ በጣም ቅርብ የሆነና አሁን ካለው የተለመደው የባህር ላይ መተላለፊያ መስመርእንደ አማራጭ ሊያገለግል የሚችል አዲስ መንገድ እየፈለጉ ነው።»
 ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ከስምምነት መደረስ አለመቻሉን ተከትሎ ወደ ሆርሙ ሰርጥ የሚገቡ ሆነ የሚወጡ በተለይ ለኢራን ቀረጥ የሚከፍሉ መርከቦችን እንደሚያግቱ ትናንት እሁድ ማስጠንቀቃቸው ሌላ ድንጋጤ ፈጥሯል። የፕሬዚዳንቱን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ  እገዳው ዛሬ ሰኞ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ ወይም  በኢራን ሰዓት አቆጣጠር 11:30 ላይ እንደሚጀመር ገልጿል።
እገዳው “የኢራንን ወደቦች እና የባህር ዳርቻ አካባቢዎችን ጨምሮ፣ በአረብ ባሕረ ሰላጤ እና በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ የሚገኙ ሁሉም ወደ ኢራን ወደቦች በሚገቡ ወይም በሚወጡ የማንኛውም ሀገር መርከቦች ላይ ያለ አድልዎ ተፈጻሚ ይሆናል” ሲል ዕዙ አስታውቋል።

ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ከስምምነት መደረስ አለመቻሉን ተከትሎ ወደ ሆርሙ ሰርጥ የሚገቡ ሆነ የሚወጡ በተለይ ለኢራን ቀረጥ የሚከፍሉ መርከቦችን እንደሚያግቱ ትናንት እሁድ አስጠንቅቀዋልምስል፦ Mandel Ngan/AFP


ምንም እንኳ በፕሬዚዳንቱ እና በዕዙ መግለጫዎች መካከል መሰረታዊ ልዩነት ቢኖርም በሆርሙዝ ሰርጥ ከአሁን ቀደም የከፋ ቀውስ ለመጋረጡ ግን አመላካች ሆኗል። 
በሌላ በኩል ዛሬ ሰኞ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጁ እንደሆነ ነው። 
ይህ ማለት ደግሞ የ15 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነቱበፍጥነት ሊጣስ የሚችልበት ዕድሉ ቅርብ ነው ማለት ነው። ዛሬ በዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ በድጋሚ ጭማሪ ታይቶ ከ100 ዶላር በላይ መድረሱ ተነግሯል። እንደተፈ,ራው አሜሪካ በድጋሚ በኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘረች ለእስራኤል ሰርግ እና ምላሽ ሊሆንላት አልያም ጦርነቱን በ,ፍጥነት ልትቀላቀል የምትችልበት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ምንም እንኳ በ40 ቀኑ ጦርነት ብርቱ ጉዳት ብታስተናግድም።
አሁን ጥያቄው ይህንን በእብደት የተሞላውን እና መካከለናው ምስራቅ ብሎም ዓለምን ወደ ከፋ ቀውስ ሊወስድ የሚችለውን ጦረኝነት  ማን ሊያስቆመው ይችላል ነው።  በእርግጥ እስካሁን ካየነው ከፈጣሪ በታች ማንም የለም። ለፍትህ እና ለሃያልነት በሚደረገው በዚህ ጦርነት ከቀጣናው ሃገራት ባሻገር እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሃገራት ላይ የሚያሳድረው ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ከባድ ነው። 
የተስፋው ጭላኝጭል ያለው ኢራን አሁምንም ቢሆን በሯ ለዲፕሎማሲ ክፍት መሆኖኑን መግለጿ ነው። እንደ እንግሊዝ ያሉ ሃገራት የዶናልድ ትራምፕን መንገድ ላለመከተል አቋማቸውን በድጋሚ ሲያሳዉቁ ። እነ ቱርክ ተፋላሚዎቹ ወደ ድርድር እንዲመለሱ እየወተወቱ ነው። ጥርስ አልባው የመግስታቱ ድርጅት ግን የትልልቆችን ንግግር ቆሞ እንደሚያዳምጥ ህጻን ዝምታን መርጧል። 

ታምራት ዲንሳ 

አዜብ ታደሰ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW