ለደሀ ሀገራት 300 ቢሊዮን ዶላር እንዲሰጥ በCOP29 የተደረሰው ሥምምነት ተቃውሞ ቀረበበት
እሑድ፣ ኅዳር 15 2017
በተባበሩት መንግሥታት የከባቢ አየር ለውጥ 29ኛ ጉባኤ ውጤት 45 “በትንሹ ያደጉ” የሚባሉ ሀገራት መቆጣታቸውን እና በኃይል ማዘናቸውን አስታወቁ። ለሁለት ሣምንታት ከተካሔደ አድካሚ ድርድር በኋላ ውጤቱ ይፋ ሲሆን የደሀ ሀገራት ተወካዮች “ለአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ተጠያቂ የሆኑ ሀገሮች ዳግም ለውድቀት ዳርገውናል” ሲሉ ከሰዋል።
በአዘርባጃን ባኩ የተካሔደው የከባቢ አየር ለውጥ ጉባኤ የደረሰበት ሥምምነት ላይ ብርቱ ነቀፋ የሰነዘረው የተደራዳሪዎች ቡድን በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ዜጎች ያሏቸው 45 የአፍሪካ፣ የእስያ ፓሲፊክ እና የካሪቢያን ሀገራትን የሚወክል ነው።
የጉባኤው ውጤት “አሳዛኝ ነው” ያለው ተደራዳሪ ቡድኑ የከባቢ አየር ለውጥ ቀውስን የፈጠሩ ሀገራትን “ጠባብ ጥቅም ለማስጠበቅ” የዓለም ደሆችን እና እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን ፍላጎት “መስዋዕት አድርጓል” በማለት ተችቷል። የድርድሩ ውጤት “ከኅልውና እና ከፍትኅ ይልቅ ትርፍ እና ምቾትን አስቀድሟል” በማለት ነቅፏል።
ዓመታዊው የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባኤ በባኩ አዘርባጃን
በአዘርባጃን ባኩ ሲካሔድ የቆየው የተባበሩት መንግሥታት የከባቢ አየር ለውጥ 29ኛ ጉባኤ ለደሀ ሀገሮች በዓመት 300 ቢሊዮን ዶላር እንዲሰጥ ከሥምምነት ደርሷል። ተደራዳሪዎቹ ሀብታም ሀገራት ለድሆች የሚሰጡትን ገንዘብ በጎርጎሮሳዊው 2035 ወደ 1.3 ትሪሊዮን ዶላር ለማድረስ ሰፊ ዕቅድ አስቀምጠዋል። ገንዘቡ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ከድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ እና ጋዝ የኃይል ምንጮች ለመላቀቅ እንዲችሉ ለማገዝ እና በከባቢ አየር ለውጥ ምክንያት የሚያደርስባቸውን ጉዳት እንዲቋቋሙ ለመርዳት የሚሆን ነው።
ለሁለት ሣምንታት ሲካሔድ በቆየው ድርድር መጨረሻ የበለጸጉ ሀገራት በጎርጎሮሳዊው 2035 በዓመት ለመስጠት ቃል የገቡት የገንዘብ መጠን ግን ደሀ ሀገራት ከጠየቁት እጅግ ያነሰ ነው። በድርድሩ ደሀ ሀገራትን የወከሉ ተሳታፊዎች የገንዘቡ መጠን 1.3 ትሪሊዮን ዶላር ሊሆን ይገባል የሚል አቋም ነበራቸው።
ተደራዳሪዎች ከሥምምነት ላይ የደረሱት ጉባኤው ሊጠናቀቅ ከታቀደለት ጊዜ 33 ሰዓታት ዘግይተው ዛሬ እሁድ ማለዳ ነው። ትላንት ቅዳሜ የከባቢ አየር ለውጥ የበረታ ዳፋ የሚያሳድርባቸው ትናንሽ የደሴት ሀገራት እና አፍሪካውያን በጊዜያዊነት ረግጠው በመውጣት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ድርድሩ ይጨናገፋል የሚል ሥጋት ተፈጥሮ ነበር።
ሥምምነት ላይ ከተደረሰም በኋላ ቢሆን የከባቢ አየር ለውጥ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ከሀብታም ሀገሮች ለድሆቹ ሊሰጥ የታቀደው የገንዘብ መጠን ሁሉንም ተደራዳሪዎች ዕኩል አላስደሰተም። የሕንድ ተወካይ የሆኑት ቻንድኒ ራይና ገንዘቡ እጅግ አናሳ እንደሆነ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
“ይህ በእኛ አስተያየት ሁላችንንም የሚያጋጥሙ ፈተናዎች የሚፈታ አይደለም” ሲሉ ተችተዋል።
የሴራ ሊዮን የተፈጥሮ እና ከባቢ አየር ለውጥ ሚኒስትር ጂዎሕ አብዱላይ በበኩላቸው የድርድሩ ውጤት የዓለም ደሀ ሀገሮች የባሕር ከፍታ መጨመር እና ኃይለኛ ድርቅን ሲጋፈጡ ሀብታም ሀገሮች ከጎናቸው ለመቆም “መልካም ፈቃድ” ማጣታቸውን ያሳያል ብለዋል።
የናይጄሪያ ተወካይ ንኪሩካ ማዱክዌ “ይኸ ዘለፋ ነው” በማለት በድርድር የተደረሰበትን ሥምምነት አጣጥለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የከባቢ አየር ለውጥ 29ኛ ጉባኤ በሚካሔድበት ወቅት በተደረጉ ተቃውሞዎች የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ እና ጃፓንን የመሳሰሉ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት ከፍትኃዊ ሥምምነት ላይ እንዳይደረስ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እየተደራደሩ ነው የሚል ወቀሳ ተሰንዝሮባቸዋል።
በማደግ ላይ የሚገኙ የሚባሉት ደሀ ሀገራት ተወካዮች ከካሲፒያን ባሕር ዳርቻ ወደ ምትገኘው ባኩ ያቀኑት በጎርጎሮሳዊው 2009 ቃል ከተገባው 100 ቢሊዮን ዶላር በዓመት የተሻለ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ከባለጠጎቹ ለማግኘት ተስፋ ሰንቀው ነው። የማርሻል ደሴቶች ተወካይ የሆኑት ቲና ስቴገ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱት ከታገሉለት “እጅግ በጣም ትንሽ” አሳክተው ቢሆንም ባዶ እጃቸውን እንዳልሆነ ተናግረዋል።
በውቅያኖስ ከፍታ መጨመር የሕልውና ሥጋት የተጋረጠባትን ሀገር የወከሉት ቲና ስቴገ “ይኸ በቂ አይደለም። ነገር ግን ጅምር ነው” ብለዋል። ደሀ ሀገሮች “ቀልድ” እና “ዘለፋ” ብለው የድርድሩን ውጤት ቢያጣጥሉም የጀርመን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ግን ተከላክለዋል። “የዛሬ ውሳኔዎቻችን ብቻቸውን ሁሉንም ፍላጎቶች ለማሟላት በቂ እንዳልሆኑ እናውቃለን” ያሉት ቤርቦክ “ለታዳጊ ሀገራት የሚሰጠውን ፋይናንስ ወደ 1.3 ትሪሊዮን ዶላር የማሳደግን ርዕይ የደገፍንው ለዚህ ነው” ብለዋል።
ከዱባዩ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ምን ተገኘ?
በታሪክ በከባቢ አየር ብክለት ተጠያቂ የሆኑ የበለጸጉ ሀገራት የመሬት ሙቀት መጠን ሲጨምር ኃይለኛ ተጽዕኖ ለሚያርፍባቸው ደሀ ሀገራት ምን ያክል ገንዘብ ሊሰጡ ይገባል በሚለው ጉዳይ ላይ የጉባኤው ተሳታፊ ሀገራት ለረዥም ዓመታት የዘለቁ ልዩነቶቻውን ለማስታረቅ መቸገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በጉባኤው ለምድር ሙቀት መጨመር ዋና መንስኤ የሆኑ በካይ የኃይል ምንጮችን ለመተካት ከዚህ ቀደም በተገባው ቃል ኪዳን ላይም ከሥምምነት አልተደረሰም። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው የተባበሩት መንግሥታት የከባቢ አየር ለውጥ 28ኛ ጉባኤ በዱባይ ሲካሔድ የተገባው ቃል ኪዳን ከባኩ የመጨረሻ ሥምምነት ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል።
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ