የከተማ ልማት ሥራውን "ሀገራት፣ ግለሰቦች እና ቡድኖች በደስታ አያዩትም" - ጠ/ሚ ዐቢይ
ሐሙስ፣ መስከረም 22 2018
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የከተማ ሥራችንን "ሊያጣጥሉ የሚሞክሩ" ላሏቸው "ሀገራት እና አንዳንድ ቡድኖች" ጉዳዩን "ለእኛ ተውልን" አሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጅግጅጋ ከተማ በተሰራጬ መልዕክታቸው "ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን [የኮሪዶር ልማት] ሥራ ተጀምሯል" አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የከተማ ሥራችንን "ሊያጣጥሉ የሚሞክሩ" ላሏቸው እና በስም ላልጠቀሷቸው "ሀገራት እና አንዳንድ ቡድኖች የእናንተን ሥራ ሥሩ፤ ይህን ለእኛ ተውልን፣ ይህ ሀገር ባለቤት አለው" በማለት ገልፀዋል።
የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ የኢትዮጵያ የኮሪደር ልማት የባለሃብቶችን መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ የማድረግ ፍላጎት "ገድቧል" በማለት በዚህ ሳቢያ "የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኹኔታ "ለአሜሪካ እና ሌሎች የውጭ ንግዶች ፈታኝ ነው" ብሎ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትችቱ ከየትኛው ሀገር እና ቡድን እንደሆነ ባይጠቅሱም መንግሥታቸው የዜጎችን ሕይወት እና የአኗኗር ዘርቤ ለመቀየር እያደረገ ያለው ጥረት "በጣም ተስፋ ሰጪ" መሆኑን ገልፀዋል።
የከተማ ልማት ሥራውን "ሀገራት፣ ግለሰቦች እና ቡድኖች ብዙ ጊዜ በደስታ አያዩትም" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 22 ቀን በማኅበራዊ መገናኛ ዐውታር ገጾቻቸው ባጋሩትና ከጅግጅጋ ከተማ በተላለፈው መልዕክታቸው፣ በከተማዋ በመብራት፣ በመንገድ፣ በኮሪዶር ልማት እና በቤት ግንባታ የተከናወኑ ተግባራትን ዘርዝረው "ዕድገት መመዝገቡን" ገልፀዋል።
ጅግጅጋ ላይ "ያየነው ለውጥ በአዲስ አበባ ከምናውቀው ለውጥ በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ትልቁ ሥራ ሊሆን ይችላል፤ ይህም ተስፋ ሰጪ ነው" ሲሉም መንግሥታቸው የጀመረውን የከተማ - የኮሪዶር ልማት ሥራ አድንቀዋል። ይህንን "ድንቅ ሥራ ለምንድን ነው አንዳንዶች የማይቀበሉት"? የሚለውን ጠይቀው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ያላማረው" ያሉትን የቆሸሸ የከተማ ገጽታ በቂ ነው ብለው የሚያስቡ ያሏቸው በስም ያልጠቀሷቸው "ሀገራት፣ ግለሰቦች እና ቡድኖች ብዙ ጊዜ በደስታ አያዩትም" ብለዋል። ምክንያት ያሉት "ለምን አትሰሩም" የሚል ጥያቄ እያመጣባቸው መሆኑን በመጥቀስ በሥራው ላይ የሚቀርበውን ትችት መንግሥታቸው እንደማይቀበለው ገልፀዋል።
"ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ መሆን የሚችል ሥራ ተጀምሯል። ከተሞቻችን መድረስ የሚገባቸው ቦታ ላይ አልደረሱም። ይህንን ሥራችንን አይተው ሊያጣጥሉ የሚሞክሩ ሀገራት እና አንዳንድ ቡድኖች ደግሞ 'የእናንተን ሥራ ሥሩ። ይህን ለእኛ ተውልን። ይህ ሀገር ባለቤት አለው። ሕዝብ አለው። ራሱን የሚወድ፣ ራሱን የሚያከብር፣ መለወጥ የሚፈልግ ሕዝብና መንግሥት አለው'። ለእኛ ተውልን ሥራችንን ነው መልዕክቴ።"
የኢትዮጵያን የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት አመቺነት ኹኔታ የተመለከተው የአሜሪካ መንግሥት ዘገባ ምን ይላል?
የኢትዮጵያን የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት አመቺነት ኹኔታ የተመለከተው ሰሞነኛው የአሜሪካ መንግሥት ዝርዝር ዘገባ የኢትዮጵያ መንግሥት የከተሞች የመንገድና የዳርቻ ወይም የኮሪደር ልማት የባለሃብቶችን መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ የማድረግ ፍላጎት "ገድቧል" ሲል ገልጾ ነበር። ዝርዝር መረጃው "የውጭ ይዞታዎችን ጨምሮ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እና የንግድ ድርጅቶች ንብረታቸው ያለ በቂ ማስጠንቀቂ" በከተማ ሥራ ምክንያት መፍረሱን ተከትሎ እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረሱንም ጠቅሷል። ከዚህ በመነሳትም "የኢትዮጵያ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ኹኔታ "ለአሜሪካ እና ሌሎች የውጭ ንግዶች ፈታኝ ነው" ማለቱ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት ግን ይህ ተግባር "ሥራ በመፍጠር፣ የጭስ አልባውን ኢንደስትሪ በማነቃቃት የሰዎችን የአኗኗር ዘዬ በማሻሻል እየተጫወተ ያለው ሚና በጣም ከፍተኛ ነው" ሲሉ ለሚቀርቡ ትችቶች ቦታ መስጠት እንደማይገባ ጠቅሰዋል።
"ለእንደዚህ አይነቱ ጆሮ መስጠት አያስፈልግም። ለእኛ የሚበጀንን፣ የሚያስፈልገንን እኛ ነው የምናውቀው" በማለት።
"በሚቀጥሉት 15፣ 20 ዓመታት የአብዛኛው ማኅበረሰብ የመኖሪያ ስፍራ ከተማ ይሆናል" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሁሉም አካባቢዎች የተጀመረውን የከተማ ልማት ሥራ "ጅማሯችን ጥሩ ነው" በማለት የገለፁት ሲሆን "በትጋት፣ በልፋት፣ በእኛ ሀብት እና ድካም የዜጎቻችንን ሕይወት፣ የአኗኗር ዘርቤ ለመቀየር እያደረግን ያለነው ጥረት በጣም ተስፋ ሰጪ ነው" ብለዋል። ሊሠራ ከሚጠበቀው ጋር ሲታይ ብዙ ይጠይቃል ያሉት የሀገሪቱ ርእሠ መስተዳድር "በከተማ ሥራዎቻችን በአፍሪካ ምልክት እና ምሳሌ ተደርገን ተወስደናል" ተደምጠዋል።
"የከተማ የማስዋብ ሥራ መገንዘብ የሚያስፈልገው፣ በሚቀጥሉት 15 ፣ 20 ዓመታት ቢበዛ አብዛኛው የማኅበረሰብ የመኖሪያ ስፍራ ከተማ ይሆናል። ከተማን ስናዘምን ለልጆቻችን የሚመች፣ የሚመጥን ሀገር እየሠራን ነው ማለት ነው"
የአሜሪካ መንግሥት ሰሞነኛ መግለጫ የኢትዮጵያ የከተማ ልማት ሥራው "ንግድን የማይቻል" ያደረገበትን አጋጣሚ መፍጠሩን ጠቅሶ "የንግድ ሥራዎች ከሥራ እንዲወጡ" ማስገደዱንም ጠቅሷል።
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ "የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት ለእያንዳንዱ ጉዳይ ምላሽ ሊሰጥበት ይገባል" ምክንያቱም "ጉዳዩ ከፍተና ተጽዕኖ የሚኖረው በመሆኑ" ሲሉ ምክር መስጠታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ