የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ውጤት አንድምታ
እሑድ፣ ሐምሌ 23 2015በኢትዮጵያ ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንዲፈተኑ የሚያስገድደው አሰራር ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ተደርጓል። በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የመንግስት እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት »የጋራ መመዘኛ» ነው በተባለለት እና ተመራቂ ተማሪዎቻቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለፈተና ቢያስቀምጡም ፤ ከአጠቃላይ ተፈታኞች ፈተናውን ማለፍ የቻሉት 40 ከመቶ ገደማ ብቻ ናቸው ። የትምህርት ሚኒስቴር እንደሚለው ቀሪዎቹ 60 በመቶ ገደማ የሚሆኑ ወዳቂ ተማሪዎች በየስድስት ወሩ ተደጋግሞ የሚሰጠውን ተመሳሳይ የመውጫ ፈተና የመፈተን ግዴታ አለባቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም ተመራቂ ተማሪዎች የፈተሸው ይኸው የመውጫ ፈተና በተለይ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሊቋቋሙት እንዳልቻሉ ታይቷል። የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው በእነዚሁ የግል የትምህርት ተቋማት ለፈተና ከተቀመጡት 72,203 ተማሪዎች ውስጥ ፈተናውን ያለፉት 17 ከመቶ ገደማ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ከመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንጻር ቢታይም ፈተናውን ከወሰዱት 77,981 ተማሪዎች መካከል 37.23 ከመቶ የሚሆኑት ወድቀዋል። የመንግስትም ሆኑ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተናውን ማለፍ ላልቻሉ ተማሪዎቻቸው ዲግሪ መስጠት እንዳይችሉም የትምህርት ሚኒስቴር አሳስቧል። ሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም ተመራቂ ተማሪዎች ለመውጫ ፈተና እንዲቀመጡ የሚያስገድደውን አሰራር ተግባራዊ ካደረገች እና ውጤቱ ከታየ በኋላ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጥበት ይሰማል። ውጤቱ በአንድ በኩል የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ያለበትን ደረጃ ፍንትው አድርጎ ያመላከተ ነው የሚል አስተያየት ሲያስተናግድ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አለመሰራታቸው ፤ ለወትሮም የተመረቀ ስራ አጥ በከፍተኛ ደረጃ ተሸክማ ያለች ሀገር አሁን ደግሞ ተምሮ ነገር ግን ያልተመረቀ እና ቁጭ ብሎ ፈተና የሚጠብቅ ተጨማሪ ኃይል መፍጠሩ በመስኩ የሀገሪቱን ችግር ከድጡ ወደ ማጡ ያደርገው ይሆን የሚል ስጋት ማሳደሩ ሲገለጽ ይሰማል። ከዚሁ ጎን ለጎን የትምህርት ሚኒስቴር «ትምህርት ለዜጎች » በሚል መሪ ቃል የትምህርት መሰረተ ልማት በማደስ «የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ» ሀገራዊ ህዝባዊ ንቅናቄ ማስጀመሩም ተሰምቷል። ውይይታችን «የኢትዮጵያ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ውጤት ተስፋ እና ስጋት» ላይ ያተኩራል።
ታምራት ዲንሳ