1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኩላሊት የጤና ችግር

ማክሰኞ፣ የካቲት 22 2014

የኩላሊት ህመም በአብዛኛው በዕድሜ ገፋ ያሉ እንዲሁም የደም ግፊት እና የስኳር ታማሚዎችን እንደሚያጠቃ ቢነገርም ወጣቶችም ለጤና ችግሩ እንደሚጋለጡ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

Bonn Nierentransplantation in einer Klinik in Nordrhein Westfalen
ምስል Ute Grabowsky/photothek/picture alliance

ጤና እና አካባቢ

This browser does not support the audio element.

በጎርጎሪዮሳዊው 2005 ዓ,ም በመላው ዓለም ከፍተኛ ደረጃ በደረሰ የኩላሊት ህመም ምክንያት 58 ሚሊየን ሕዝብ ሕይወቱን ማጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። የኩላሊት ህመም በአብዛኛው በዕድሜ ገፋ ያሉ እንዲሁም የደም ግፊት እና የስኳር ታማሚዎችን እንደሚያጠቃ ቢነገርም ወጣቶችም ለጤና ችግሩ እንደሚጋለጡ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በርከት ያሉ ሰዎች በኩላሊት ህመም እንደሚሰቃዩ በመግለጽ ለህክምና የገንዘብ ርዳታ ሲጠየቅ አጋጥምዎት ይሆን? በአብዛኛው ስለኩላሊት እጥበት እንዲሁም ንቅለ ተከላ ህክምና ሰዎችን ለመርዳት የሚንቀሳቀሱ ስለመኖራቸውም ሲነገርም ይኽ የጤና ችግር ለየት ባለ መልኩ እንዴት ነው የተበራከተው የሚል ጥያቄም ሊኖርዎት ይችላል። በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በኩላሊት ህክምን ክፍል የውስጥ ደዌ እና የኩላሊት ሀኪም ለሆኑት ዶክተር አቤል ዘመንፈስ እኛም ያስቀደምነው ይኽንኑ ጥያቄ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ የኩላሊት ታማሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ያመለከቱት ባለሙያው፤ የታማሚው ቁጥር የበረከተ መስሎ ለመታየቱ ሦስት ዋና ዋና ያሏቸውን ምክንያቶች ያነሳሉ። የሕዝብ ቁጥር በጨመረ ቁጥር አንድ ኅብረተሰብ ውስጥ የሚኖረው የህመም ሁኔታ ከፍ ብሎ ሊታይ እንደሚችል፤ የኩላሊት ህመም ዕድሜ ባይለይም በተለይ ከዕድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ በተለያዩ ምክንያቶች መከሰቱ፤ እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ እና ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ሊያስከትሉት እንደሚችሉ አንስተዋል።

ምስል Reuters/M. Dalder

ከዕድሜ ጋር በተያያዘም በወጣቶች ላይ ህመሙ የሚያጋጥመው በብዛት የሽንት መተላለፊያ መዘጋት፤ የኩላሊት መቆጣት እንዲሁም ሳይታወቅ ወይም ሳይታከም የቆየ የደም ግፊት የሚያስከትለው አንዳንዴም ከስኳር ህመም ጋር የተያያዘ እንደሆነም ነው አጽንኦት የሰጡት። ዶክተር አቤል የኩላሊት ህመም በአብዛኛው በምርመራ ካልሆነ በቀር ምልክት ባለመስጠቱ የጤና ይዞታቸውን የማይከታተሉ ሰዎች ለዚህ ችግር መጋለጣቸውን የሚያውቁት ህመምና ጉዳቱ በተባባሰበት ደረጃ ላይ ሲደርስ እንደሆነ ከዕለት ተዕለት ተሞክሯቸው አስተውለዋል። ውኃ አብዝቶ መጠጣት ለተወሰኑ የኩላሊት የጤና እክሎች የሚረዳ መሆኑ ቢታመንም በዕለት ለሰውነት ከሚያስፈልገው በላይ ማብዛት እንደማያስፈልግ ነው ያመለከቱት። እንደውም ኩላሊት የመድከም ችግር መኖሩ ከታወቀ አብዝቶ ውኃ መጠጣቱ ሌላ ችግር ሊሆን እንደሚችልም ዶክተር አቤል አጽንኦት ሰጥተዋል። ለእያንዳንዱ የኩላሊት የጤና ችግር የሚመከረው የውኃ አወሳሰድ መጠንም የተለያየ መሆኑ ልብ ሊባል እንደሚገባ በማሳሰብም የሀኪም ምክርን ማስተዋል ያስፈልጋል ነው ያሉት። በተለምዶ የኩላሊት እጥበት በህክምናው ዲያሊስስ ሲባል እንሰማለን፤ እንዴት አይነት ህክምና ነው? ለየትኛውስ የኩላሊት ህመም በመፍትሄነት ይሰጣል? እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችንም አንስተናል። በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በኩላሊት ህክምና ክፍል የውስጥ ደዌ እና የኩላሊት ሀኪም እንዲሁም በሆስፒታሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር መምህር ከሆኑት ዶክተር አቤል ዘመንፈስ ያገኘነውን ማብራሪያ ሳምንት ይዘን እንቀርባለን።

ሸዋዬ ለገሠ 

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW