1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኩፍኝ ወረርሺኝ በኮንጎ ሺህዎችን እየቀጠፈ ነው

ቅዳሜ፣ የካቲት 21 2012

የኮሮና ተሐዋሲ መላ ዓለምን ማስጨነቅ በጀመረበት በአኹኑ ወቅት አፍሪቃ ውስጥ የተዘነጉ የመሰሉ በሽታዎች የሰዎችን ሕይወት መቅጠፍ ጀምረዋል። በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ  6000 ሰዎች በኩፍኝ ወረርሽኝ መሞታቸውን ዓለም የዘነጋው ይመስላል።

Symbolbild Ausnahmezustand - Masernausbruch
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Wenig

ኩፍኝ በኮንጎ 6 ሺህ ሰው ገድሏል

This browser does not support the audio element.

የኮሮና ተሐዋሲ መላ ዓለምን ማስጨነቅ በጀመረበት በአኹኑ ወቅት አፍሪቃ ውስጥ የተዘነጉ የመሰሉ በሽታዎች የሰዎችን ሕይወት መቅጠፍ ጀምረዋል። በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ  6000 ሰዎች በኩፍኝ ወረርሽኝ መሞታቸውን ዓለም የዘነጋው ይመስላል። ይኽ ቁጥር በዓለም ዙሪያ በኮሮና ተሐዋሲ ከሞቱት አጠቃላይ ሰዎች በግማሽ የሚበልጥ ነው።  እስከ ትናንት ድረስ ብቻ በኮሮና የሞቱ ሰዎች ቊጥር  2,800 ነው። እንዲያም ኾኖ አፍሪቃ ውስጥ የተከሰተው የኩፍኝ ወረርሽኝ ትኩረት አላገኘም። ካለፈው አንድ ዓመት አንስቶ ኮንጎ ውስጥ ከ3 መቶ ሺህ በላይ ሰዎች በኩፍኝ ተሐዋሲ ተይዘዋል። 

በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምሥራቃዊ ክፍል የጎማ ከተማ በሚገኘው አንድ የጤና ጣቢያ ተሰብስበው የሚጠባበቊ ህጻናት ሴቶች እና ወጣቶች ትንሽ የተጨናነቊ ይመስላሉ። ጸረ-ኩፍኝ ክትባት ሊወጉ ነው የሚጠብቊት። አንዲት እናት ልጆቻቸውን ለምን ጸረ-ኩፍኝ ክትባት እንደሚያስወጌ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንዲህ ይናገራሉ።  

«ኩፍኝ ለሕጻናት ገዳይ ሊኾን እንደሚችል ሰምቻለሁ።  ስለዚህም ነው ስድስቱም ልጆቼ እንዲከተቡ ይዣቸው የመጣኹት።»

ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ውስጥ የኩፍኝ ወረርሺኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ከ6000 በላይ ሰዎች ሞተዋል። በበሽታውን የሚሞቱትን ሰዎች በክትባት መቀነስ ይቻል ነበር። ኾኖም ግን በአካባቢው ተቀስቅሶ የነበረው ሌላው ገዳይ ወረርሽኝ ኢቦላ የምዕራቡ ዓለም ላይ ስጋት በማሳደሩ የኩፍኝ ወረርሽኝ ላይ ጥላውን ዘርግቶ ነበር። ምንም እንኳን የኩፍኝ ወረርሽኝ ኮንጎ ውስጥ በርካቶችን ቢያረግፍም  የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ  ከፍተኛ ገንዘብ ያገኘው የኢቦላ ተሐዋሲን ለመዋጋት ነው። እስካሁን ድረስ ኮንጎ ውስጥ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ 18 ሚሊዮን ህፃናት ጸረ-ኩፍኝ ክትባት ተወግተዋል።

ኮርኔሌ ቢሁራ ጎማ ውስጥ በሚገኝ ጤና ጣቢያ ውስጥ ነው የሚሠሩት።

ምስል Imago Images/Xinhua Afrika

«እዚህ የመጣ ታማሚ በነጻ ነው የሚታከመው። በየቀኑ ኩፍኝ የጠናባቸው ከሦስት እስከ አምስት ህጻናት እኛ ጋር ይመጣሉ።  ለኹልም ታዲያ በቂ  መድኃኒት አለን።»

በእርግጥ ጎማ ምስራቃዊ ኮንጎ ውስጥ የምትገኝ ትልቅ ከተማ ናት።  ሌሎች ቦታዎች ላይ ኹኔታው የከፋ ነው። በኮንጎ በርካታ ግዛቶች ነዋሪዎች የጤና አጠባበቅ ቁሳቁስ የላቸውም ማለት ይቻላል። የክትባት መድኃኒቶቹ የሚቀመጡባቸው ማቀዝቀዣዎች አስተማማኝ አይደሉም፤ በዚያ ላይ ታጣቂዎች የጤና ጣቢያዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ይሰነዝራሉ፤ ያም በመኾኑ የሕክምና ባለሞያዎች ባሉበት ራቅ ብለው መቆየቱን ይመርጣሉ።  

«በርካታ ህጻናት  ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ በሕይወታቸው ሙሉ አንዳችም ክትባት አላገኙም፤ ይኼም ነገሮችን እጅግ አስቸጋሪ ያደርጋል» ይላሉ በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪቃ የድንገተኛ መከላከል ክፍል ኃላፊው ሚኬል ያኦ። በእርግጥ በኩፍኝ ተሐዋሲ የሚያዙ ሕጻናት ቊጥር ከበፊቱ አንጻር መቀነስ ይታይበታል። ግን ደግሞ የኩፍኝ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት አንድ ዓመት አንስቶ ወረርሽኙን መቆጣጠር አልተቻለም።

ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት እስከ 16 ያሉትን ልጆች ለመከተብ የገንዘብ እና የክትባት እጥረት ከፍተኛው ተግዳሮት መኾኑን ሚኬል ተናግረዋል። ከዐሥር ዓመት በፊት የተከተቡ ልጆች ቊጥር መጨመር እና የክትባት እጥረት ምናልባትም ወረርሽኙ ይበልጥ እንዲስፋፋ ሊያደርግ ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጠዋል።

የዓለምጤና ድርጅት ኩፍኝን የመዋጋት ጥረቱን አኹን ከፍ ያደረገ ይመስላል። ለዚያ ደግሞ 40 ሚሊዮን ዶላር ግድም እንደሚያስፈልግ ዐሳውቋል። በገንዘቡ ዕድሜያቸው ከአምስት እስከ 16 ዓመት የኾናቸው ልጆችን በሙሉ ለመከተብ ይቻላል። ዓለም አቀፍ ድርጅቱ ግን እዚያ ግቡ ላይ ለመድረስ ወላጆች በእርግጥም ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ ለማበረታታት በርካታ ገንዘቡን በማንቂያ ዘመቻ ማስታወቂያዎች ላይ ማፍሰሱ አልቀረም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ቤቲና ሩይል 

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW