የካሳ ክፍያ ከሕግ አንጻር እንዴት እየተተገበረ ነው?
ሐሙስ፣ ሐምሌ 17 2017
ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) መደበኛ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ካሳ በመክፈል ሰበብ ከፍተኛ ሐብት በክልሉ ውስጥ እንደሚባክን ገልጸው፤ መንግስታቸው ካሁን በኋላ ለግለሰቦች ካሳ ላይከፍል እንደሚችል ጠቁመዋል። በኦሮሚያ ክልል በተለይም ከተሞች አከባቢ የመንገድ ዳር ልማት ብሎ መንግስት የሚያፈርሳቸው በርካታ ቤቶችም ካሳ እንዳልተከፈለባቸው ሕጋዊ የይዞታ ባለቤትነት ጭምር ይዘው ካሳም ሆነ ምትክ ቦታ አለማግኘታቸውን የሚገለጹ በርካቶች ናቸው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር የቡራዩ ክፍለ-ከተማ ነዋሪው የ73 ዓመት አዛውንት እየተገባደደ ባለው በዓመቱ መጀመሪያ አከባቢ የፈረሰባቸው መኖሪያ ቤትና መተዳደራቸው የሆኑ የንግድ ሱቆች በሙሉ የመንገድ ዳር ልማት በተባለው የከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክት እንደፈረሰባቸው ይናገራሉ፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ ለዓመት እየተጠጋ ባለበት ወቅት የገቢ ምንጭ ሆኖዋቸው በነበሩ ሱቆቻቸውም ሆነ መኖሪያቸው ምትክ ቦታም ሆነ ካሳ ባለመከፈሉ ችግር ላይ መውደቃቸውንም ያመለክታሉ፡፡
"ሱቄ፤ ቤቴ ከፈረሰ አሁን ስምንተኛ ወር ላይ በመሆኑ ችግር ላይ ነን፡፡ በቦታው ወይ ቤት አልተሰራበት ወይ ግምት ካሳ አልተሰጠንም፡፡ የኔ ቦታ ሙሉ ቤት እንዲነሳ ብነገረኝም ሌላ ምትክ እስኪሰጣችሁ በሚል የተቀረች ቦታ ላይ ተጠልየ ነው ያለሁት፡፡ አሁን መተዳደሪያ ገቢዬ ተቋርጧል፡፡ በዚያ ላይ በሽተኛ ነኝ ሰርቼ መብላት አልችልም፡፡ እስካሁን የተመለከተን የለም ለማን አቤት እንላለን” ሲሉ ነው ምሬታቸውን የገለጹት፡፡
ለጋራ ልማት በፈረሱ ንብረቶች ምትክ ከካሳ ክፍያ እና ምትክ ይዞታ ጋር በተያያዘም ሰፊ አቤቱታዎች በሚነሱበት ሸገር ከተማ ላይ በቅርቡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የከተማው አስተዳደር ከንቲባ ዶ/ር ተሾመ አዱኛ፤ "ሕጋዊ የሆኑትን ምትክ እንሰጣለን ግን ሕጋዊነቱን እያጣራን ነው” በማለት ከሸገር ምስረታ በፊት የነበሩ የካርታ አወጣጥ ስርዓት ላይ ችግሮች እንደነበሩባቸው ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ህጋዊ ሰውነት ያላቸው እየተለዩ ካሳ እንደሚከፈላቸው ተናግረው ነበር፡፡
ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ እና ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ካሳ በመክፈል ሰበብ ከፍተኛ ሐብት በክልሉ ውስጥ እንደሚባክን ገልጸው፤ መንግስታቸው ካሁን በኋላ ለግለሰቦች ካሳ ላይከፍል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
"ከዚህ የጨፌ አባላት የተነሳው የልማት ጥያቄ ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡ ግን የጋራ የሕዝቡ እና የመንግስት አቅም በጠነከረ መጠን ነው እነዚህ ጥያቄዎች ልመለሱ የሚችሉት፡፡ ባለፉት ዓመታት ከፕሮከት ጋር ተያይዞ በርካታ ስራዎች በፌዴራል እና በክልሉ ብጀመሩም ሶስት ነገሮች ናቸው ባለፈው ዓመት የፈተኑን፡፡ የፀጥታ ችግር አንዱ አንቆ የያዘን ጉዳይ ሲሆን በርካታ ማሽነሪዎች በኦሮሚያ ውስጥ ተቃጥለዋል፡፡ በኦሮሞ ስም ለኦሮሞ እታገላለሁ የሚል አካል ለኦሮሞ እናት ሆስፒታል የሚገነባ፣ መንገድ ውኃውን የሚስገባውን ማሽነሪ ያቃጥላል፡፡ የፈተነን ሌላኛው ነገር የኮንትራክተሮች እና መንግስታችን የማስፈጸም አቅም ነው፡፡»
«በሦስተኝነት ግን የፈተነን ካሳ ነው፡፡ ካሳ እና ልማት አብሮ አይሄዱም፡፡ ካሳን በተመለከ ደግሞ አሁን አንድ ቀመር አለ፡፡ አስፈጻሚ የመንግስት አካል ከሕግ አካል ጭምር ጋር ተግባብቶ አቀናጅተው ዝርፊያ እየተካሄደ ነው፡፡ ይህ በሁሉም የፌዴራል እና ክልል ፕሮጀክቶች አጋጥመውናል፡፡ መረር ያለ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል፡፡ ፍርድ ቤት የሚወስነው ሕጋዊ ዝርፊያ ነው እየተካሄደ ያለው፡፡ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ካለቁ በኋላ እንኳ ካሳ የሚከፈልባቸው አሉ፡፡ ለአንዳንድ ፕሮጀክቶች የተከፈለው ካሳ ከፕሮጀክቱ ወጪ ይልቃል፡፡ ይህ ጨፌ በዚህ ላይ ጥልቅ ክትትል እንዲያደርግ እጠይቃለሁ፡፡ በዚህ ላይ ተቀናጅተው የዘረፉ መዋቅሮቻችን ፈትሸን የማያዳግም ርምጃ እንወስዳለን፡፡ ሕዝባችን ደግሞ መረዳት ያለበት ሆስፒታል እየጠየቀ ለዚያ ካሳ መፈለግ ልክ አይደለም፡፡ ሕዝብ ተቀናጅቶ መፍትሄ መፈለግ አለበት፡፡ ለክልል ፕሮጀክቶች ካሳ ከፍለን አናውቅም፡፡ ወደፊትም አንከፍልም፡፡ አንዳንድ ቦታ ኤርፖርት እንደሰራለን ብለን ለካሳ ከግንባተው ወጪ በላይ ከፍለን እናውቃለን፡፡ ይህ እየሆነ የተጠየቀውን ልማት ማምታት አንችልም” ሲሉ አማረው አንስተዋል፡፡
ለመሆኑ መንግስት ለግለሰቦች ንብረት ከሳ ስለሚከፍልበት አሰራር የአገሪቱ ሕግ ምን ይላል በሚለው ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ጠበቃ እና የህግ ባለሙያ አንዱዓለም በዕውቀቱ፤ "በኢትዮጵያ ሕገመንግስት አንቀጽ 40 አንተ የያዝከው ነገር ከአንድ ሰው ከሚጠቀምበት በላይ ሆኖ ስገኝና ለህዝብ ጥቅም ብውል በሚል አሳማኝ ሆኖ ስገኝ ከሳ ተከፍሎ ብቻ ልወሰድ ይችላል” በማለት ይህም ቅድመ ሁኔታ እንዳለው አስረድተዋል፡፡ ካሳው በቅድሚያ ከልማቱ በፊት መከፈል እንዳለበት የገለጹት ባለሙያው ካሳው ተመጣጣጭ መሆን እንዳለበትም ህጉ ይደነግጋል ነው ያሉት፡፡ የሕግ ባለሙው አቶ አንዱዓለም መንግስታት በተለይም ሕጋዊ ሰነድ ላለው ንብረት ፈጽሞ ይህን ሕግ ቢጥሱ ኢ-ሕገመንግስታዊ ድርጊት እንደሚሆንም በሙያቸው አስረድተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ