1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካቲት 13 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 13 2015

የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ መጓተት በሚሊዮን የሚቆጠር የብር ብክነትን አስከትሏል። ከንድፍ አንስቶ በግንባታ ሒደቱ ከ11 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የስታዲየም ግንባታ ጉዳይ በቢሊዮን የሚቆጠር ተጨማሪ የሀገሪቱ ሀብትን አደጋ ላይ ጥሏል። ነገ እና ረቡዕ የሻምፖዮንስ ሊግ ወሳኝ ግጥሚያዎች ይኖራሉ። ሪያል ማድሪድ ከሊቨርፑል ጋር ተፋጧል።

Fußball Bundesliga | Hertha BSC - Borussia Dortmund
ምስል Benjamin Westhoff

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ መጓተት በሚሊዮን የሚቆጠር የብር ብክነትን አስከትሏል። ከንድፍ አንስቶ በግንባታ ሒደቱ ከ11 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የዚህ የስታዲየም ግንባታ ጉዳይ በቢሊዮን የሚቆጠር ተጨማሪ የሀገሪቱ ሀብትን አደጋ ላይ ጥሏል። ከቻይናው ተቋራጭ ጋር የተገባው ውል መፍረሱ እጅግ አሳስቧል። ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተል ጋዜጠኛ ጋር ሰፋ ያለ ቃለ መጠይቅ አድርገናል። ነገ እና ረቡዕ የሻምፖዮንስ ሊግ ወሳኝ ግጥሚያዎች ይኖራሉ። ሪያል ማድሪድ ከሊቨርፑል ጋር ተፋጧል። ላይፕትሲሽ ማንቸስተር ሲቲን ለማስተናገድ ደፋ ቀና ሲል፤ ኢንተር ሚላን ፖርቶን ይገጥማል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት እና ናፖሊም ነገ ያገናኘን ብለዋል። በአውሮጳ ሊግ ፍልሚያም ባለፈው ሳምንት ሁለት እኩል የተለያዩት ባርሴሎና እና ማንቸስተር ዩናይትድ ለዳግም ፍልሚያ ሐሙስ ተቀጣጥረዋል። ጁቬንቱስ፤ ሞናኮ እና ሴቪያን ጨምሮ ሌሎች ቡድኖች የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም ይኖራሉ። 

አትሌቲክስ

አውስትራሊያ ባቱርስት ውስጥ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወነው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ፉክክር ኢትዮጵያ በ2ኛነት አጠናቃለች። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ 2 የወርቅ፣ 7 የብር እንዲሁም 1 የነሃስ በድምሩ 10 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ በኬንያ ተቀድማ ነው ሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው። በአጠቃላይ የወርቅ ሚዳሊያ ብዛት ግን ኡጋንዳንና አሜሪካንን ቀድማለች። ኬንያ 6 የወርቅ፤ 2 የብር እና 2 የነሃስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የአንደኛነት ደረጃን አግኝታለች። ኡጋንዳ 1 የወርቅ እና 3 የነሃስ ሜዳይ ስታገኝ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከወርቅም ሆነ ከብር ሜዳሊያ አንድም ሳታገኝ ቀርታለች። በ2 የነሃስ ሜዳሊያ ግንኬንያ፤ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳን ተከትላ የአራተናነት ደረጃን ይዛለች። በውድድሩ ወቅት የነበሩት 9 የወርቅ ሜዳሊያዎች በአጠቃላይ ወደ አፍሪቃ ለዚያውም ወደ ምሥራቅ አፍሪቃ ብቻ ሄደዋል። 

ቡንደስሊጋ፦ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከሔርታ ቤርሊን ጋርምስል Wunderl/BEAUTIFUL SPORTS/picture alliance

በዚህ ውድድር አሳዛኝ ክስተትም ታይቷል። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ 10 ኪሎ ሜትሩን አጠናቃ የወርቅ ሜዳሊያ ለማግኘት ጥቂት ሜትሮች ሲቀሯት ተደናቅፋ ወድቃለች።  ኬኒያዊቷ ቢያትሪስ ቼቤት የአንደኛ ደረጃ ስታገኝ፤ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጽጌ ገብረሰላማ 33,56 በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። አትሌት ለተሰንበትን ከወደቀችበት ለማንሳት ድጋፍ ስተደረገላትም ከውድድሩ ውጪ መሆኗ እጅግ የሚያሳዝን ክስተት ነበር።  ክስተቱ አሳዛኝ ቢሆንም ውድድሩ ጥሩ እንደነበር ወደፊት መመልከት እንደምትሻ አትሌት ለተሰንበት ገልጣለች። የዓለም የ5 ሺህ፤ 10 ሺህ ሜትር እና ግማሽ ማራቶን ክብረወሰን ባለቤቷ አትሌት ለተሰንበት በእርግጥም ወደፊት ብዙ አመርቂ ድሎችን እንደምታስመዘግብ ሳይታለም የተፈታ ነው።

በሌላ ዜና፦ በዓለም የቤት ውስጥ ሩጫ የ3 ሺህ ሜትር ርቀት ለሩብ ምእተ ዓመት በኬንያዊ አትሌት ተይዞ የቆየው ክብረወሰን በኢትዮጵያዊው አትሌት ለሜቻ ግርማ ባለፈው ሳምንት ፈረንሳይ ውስጥ ተሰብሯል። ክብረወሰኑ በጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1998 ዓ.ም ተይዞ የነበረው በኬኒያዊው አትሌት ዳንኤል ኮመን ነበር። ያኔ ዳንኤል የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድር ክብረወሰንን ሐንጋሪ ቡዳፔስት ውስጥ የሠበረው 7:24,90 በመሮጥ ነበር። ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ደግሞ ኢትዮጵያዊው ወጣት አትሌት ለሜቻ ግርማ በአንድ ሰከንድ ግድም አሻሽሎ 7:23,81 በመሮጥ ታሪክ ሠርቷል። ለሜቻ ግርማ በ1500 ሜትር፤ በ2000 እና በ3000 ሜትር የሩጫ ፉክክሮች ላለፉት ሦስት ዓመታት ምርጥ ሰአቶችን ያስመዘገበ እጅግ ተስፋ የሚጣልበት አትሌት ነው።  

ቡንደስሊጋ፦ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከሔርታ ቤርሊን ጋር ሲጫወት ጢስ የሔርታው ግብ ጠባቂው ኦሊቨርክሪስተንሰንን አፍኖትምስል Benjamin Westhoff

የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም መጓተት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ብክነት አደጋ ደቅኗል። ከ11 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የዚህ የስታዲየም ግንባታ 60 ከመቶ መጠናቀቁ ታውቋል። ሆኖም የስታዲየም ግንባታውን በማከናወን ላይ ያለው የቻይናው ተቋራጭ ኩባንያ ውሉን በማቋረጡ ስታዲየሙ ባለበት ደረጃ ይገኛል። ከመነሻው 2,7 ቢሊዮን ብር የነበረው የግንባታ ዋጋ በአሁኑ ወቅት እጅግ ከፍ ብሎ 19 ቢሊዮን ብር መጠየቁ የጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት ጭምር በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባበት አድርጓል። በሪፖርተር ጋዜጣ የአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ የስፖርት ክፍል አዘጋጅ ዳዊት ቶሎሳ ጉዳዩን በቅርበት ተከታትሎታል።

ሻምፒዮንስ ሊግ

በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ እግር ኳስ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ በሚደረገው የደርሶ መልስ የመጀመሪያ ግጥሚያ ነገ እና ከነገ በስትያ ወሳኝ ጨዋታዎች ይኖራሉ። በነገው እለት የእንግሊዙ ሊቨርፑል የስፔኑ ሪያል ማድሪድን በሜዳው አንፊልድ ያስተናግዳል። የተጎዱ ተጨዋቾቹን በፕሬሚየር ሊግ ዳግም አሰልፎ የቀድሞ አቋሙን ማሳየት የጀመረው ሊቨርፑል በሜዳው የሚያደርገውን የነገውን ጨዋታ ያሸንፋል የሚሉ ይበዛሉ። በእርግጥም ሊቨርፑል ሰሞኑን የቀድሞ የማሸነፍ ስነ ልቦናውን ያገኘ ይመስላል። ቅዳሜ ዕለት በፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ኒውካስል ዩናይትድን 2 ለ0 ድል አድርጓል። ሁለቱ ግቦች የተቆጠሩት ሊቨርፑል ፍጹም የበላይነቱን በተቆጣጠረበት የመጀመሪያው አጋማሽ 20 ደቂቃዎች ውስጥ ነበር። ቀዳሚዋን ግብ በ10ኛው ደቂቃ ላይ ዳርዊን ኑኔዝ ሲያስቆጥር፤ ከ7 ደቂቃ በኋላ ደግሞ ኦኪ ጋክፖ ሁለተኛዋን ደግሟል። ሊቨርፑል 22ኛው ደቂቃ ላይም በሞሐመድ ሳላኅ ሦስተኛ ግብ የማግኘት እድል ገጥሞት ነበር። ሆኖም የኒውካስትል ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ኒክ ፖፕ ከግብ ክልሉ ወጥቶ ኳሷን በእጁ በማጨናገፉ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲሰናበት ሞሐመድ ሳላኅም የግብ እድሉ መክኖበታል።

የባየር ሙይንሽን አሊያንትስ አሬና ስታዲየም ገጽታ ከውጪ በኩልምስል Harry Langer/DeFodi Images/picture alliance

ሪያል ማድሪድ በነገው ግጥሚያው ሁለት ወሳኝ አማካይ ተጨዋቾቹን ማሰለፍ አይችልም። የጀርመኑ አማካይ ተጨዋች የ33 ዓመቱ ቶኒ ክሮስ ከጤና ጋር በተያያዘ ችግር እንደማይሰለፍ ተነግሯል። ከቶኒ በተጨማሪ ሌላኛው አማካይ ተጨዋች ፈረንሳዊው አውሬሊ ቾዋሜኒም አይሰለፍም ተብሏል። ከአንጋፋው ሉካ ሞድሪች በተጨማሪ ፌዴ ቫልቬዴ እና ኤድዋርዶ ካማቪንኛ የሪያል ማድሪድ መሀል ሜዳን ሸፍነው እንደሚጫወቱ ተገልጧል። ለሪያል ማድሪድ አጥቂው ካሪም ቤንዜማ ከፊት መስመር መሰለፍ መቻሉ የቡድኑ ብርታት ተደርጎ ታይቷል። አምበሉ ካሪም ቤንዜማ ቅዳሜ ዕለት በላሊጋው ፍልሚያ ሪያል ማድሪድ ኦሳሱናን 2 ለ0 ካሸነፈ በኋላ ድካም ቢታይበትም ለማክሰኞው ግጥሚያ ትናንት ከቡድኑ ጋር ልምምድ አድርጓል። በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ትናንት ካዲዝን 2 ለ0 እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ አትሌቲኮ ቢልባዎን 1 ለ0 አሸንፈዋል።

ሊቨርፑል እና ሪያል ማድሪድ በጋራ 20 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ሰብስበዋል። ሪያል ማድሪድ የባለፈውን የፍጻሜ ግጥሚያ ሊቨርፑልን 1 ለ0 አሸንፎ ከነጠቀው ዋንጫ ጋር በአጠቃላይ 14 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን የሰበሰበ ጠንካራ ቡድን ነው። ኤስ ሚላን በ7 ዋንቻዎች የሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ሊቨርፑል እንደ ባየርን ሙይንሽን እስካሁን 6 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ማግኘት ችሏል።

የሪያል ማድሪድ ተጨዋቾች፦ በፊፋ የዓለም ዋንጫ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ፌዴሪኮ ቫልቬርዴ ከዳኒ ካራቫያልና ሉካ ሞድሪች ጋርምስል ANDREW BOYERS/Action Images/REUTERS

በነገው እለት በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ አምስት ሰአት ላይ የጀርመኑ አይንኅራኅት ፍራንክፉርትም የጣሊያኑ ናፖሊን ያስተናግዳል። ረቡዕ ምሽት የፖርቹጋሉ ፖርቶ ወደ ጣሊያን አቅንቶ ኢንተር ሚላንን ይገጥማል። ምሽቱን በተመሳሳይ ሰአት የጀርመኑ ላይፕትሲሽ የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲን ያስተናግዳል። ባለፈው ሳምንት አርሰናልን በፕሬሚየር ሊግ 3 ለ1 በሆነ ሰፊ ልዩነት ያስደነገጠው ማንቸስተር ሲቲ በሻምፒዮንስ ሊግ ጀርመን ውስጥ የሚጠብቀው በቡንደስሊጋው አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቡድን ነው። ሆኖም ግን በቡንደስሊጋው ቅዳሜ ዕለት ቮልፍስቡርግን በሜዳው 3 ለ0 ኩም ያደረገው ላይፕትሲሽ 39 ነጥብ ይዞ ከመሪው ባየርን ሙይንሽን የሚበለጠው በአራት ነጥብ ብቻ ነው። ትናንት ሔርታ ቤርሊንን 4 ለ1 ያሸነፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ከሻልከ ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው ዑኒዮን ቤርሊን በተመሳሳይ 43 ነጥብ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ቦሁምን ከትናንት በስትያ 2 ለ0 ያሸነፈው ፍራይቡርግ 40 ነጥብ ይዞ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  በፕሬሚየር ሊጉ ቅዳሜ ዕለት አስቶን ቪላን 4 ለ2 ድል ያደረገው አርሰናል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ54 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረZ መሪነቱን ከማንቸስተር ሲቲ ተረክቧል።

የአውሮጳ ሊግ

የባርሴሎናው ካምፕ ኑ ስታዲየም ከፊል ገጽታምስል Tony Marshall/dpa/picture alliance

የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያዎችም ቀጥለው ሐሙስ ዕለት ማንቸስተር ዩናይትድ እና ባርሴሎና ይፋለማሉ። ቀደም ሲል ስፔን ካምፕ ኑ ስታዲየም ውስጥ ሁለቱ ቡድኖች ሁለት እኩል ተለያይተዋል። ዛልስቡርግ ከሮማ፤ አያክስ አምስተርዳም ከዑኒዮን ቤርሊን፤ ሻካተር ዶኒዬትስክ ከሬኔ ጋር የሚጋጠሙት ሐሙስ ዕለት ነው። ሴቪያ ከፒኤስቪ አይንድሆቨን፤ ስፖርቲንግ ከሚቺላንድ፤ ጁቬንቱስ ከናንቴ እንዲሁም የጀርመኑ ባየር ሌቨርኩሰን ከፈረንሳዩ ሞናኮ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ሐሙስ ዕለት የሚጠበቁ ናቸው። በስፔን ላሊጋ 59 ነጥብ ይዞ በሚመራው ባርሴሎና እና በፕሬሚየር ሊጉ በ49 ነጥቡ የሦስተኛ ደረጃውን ካስጠበቀው ማንቸስተር ዩናይትድ መካከል የሚደረገው ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ እጅግ የሚጠበቅ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW