የካቲት 26 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ የካቲት 25 2016በሳምንቱ መጨረሻ፦ ዳርዊን ኑኔዝ በመጨረሻዎቹ ሰከንዶች ሊቨርፑልን ታድጎ የፕሬሚየር ሊግ መሪነቱን አስጠብቋል ። ፊል ፎደን ማንቸስተር ሲቲ በማንቸስተር ዩናይትድ ላይ የበላይ ሆኖ ድል እንዲቀዳጅ አስችሏል ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የአትሌቲክስ ዘርፎች አሸናፊ ሆነዋል ።
አትሌቲክስ
በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ፉክክር ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ አንደኛ ሆና አጠናቀቀች ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ስኮትላንድ ግላስጎው ውስጥ በሳምንቱ መጨረሺያ በተካሄደው የአትሌቲክስ ፉክክር ከዓለም ደግሞ የአምስተኛ ደረጃን ይዟል ።
ከ130 ሃገራት በላይ ከ650 በላይ አትሌቶችን ያሳተፉበት የስኮትላንዱ ፉክክር ከዐርብ እስከ እሁድ ድረስ የተኪያሄደ ሲሆን፤ በ26 ዘርፎች ውድድሮች ተከናውነዋል ። ኢትዮጵያ፦ በ800 ሜትር፣ በ1500 ሜትር እና በ3000 ሜትር በሴትና በወንድ በአጠቃላይ በ8 ሴቶች እና በ5 ወንዶች በድምሩ በ13 አትሌቶች ተሳትፋለች ።
በግላስጎው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድር፦ ኢትዮጵያ በሴቶች 1500 ሜትር ፍሬወይኒ ኃይሉ እንዲሁም 800 ሜትር ፅጌ ዱጉማ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች ። በሴቶች 3000 ሜትር ጉዳፍ ፀጋዬ የብር፤ እንዲሁም በወንዶች 3000 ሜትር ሰለሞን ባረጋ የነሃስ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል ። በሴቶች 3000 ሜትር ፉክክር ኤሌ ሴን ፒዬር በወለደች በ364ኛ ቀኗ ተፎካክራ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ በርካቶችን አስደምሟል ። በዚህ ውድድር ያስመዘገበችው ሰአት የሀገሯ የአሜሪካ ክብረወሰንን ጭምር የሰበረ ነው ።
በዚህ የአትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ ሁለት የወርቅ አንድ የብር እንዲሁም አንድ የነሀስ በአጠቃላይ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሜዳልያ ሰንጠረዥ ከአፍሪቃ የአንደኛ ደረጃን አግኝታለች ። በተለያዩ የአትሌቲክስ ዘርፎች ተፎካካሪዎቻቸውን ካሰለፉ ከዓለም 130 ሃገራት በላይ ደግሞ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች ።
በግላስጎው ፉክክር ዩናይትድ ስቴትስ 6 የወርቅ፤ 9 የብር እንዲሁም 5 የነሐስ በድምሩ 20 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃ አግኝታለች ። ቤልጂየም በ3 የወቅር እና በአንድ የነሐስ፤ ኒውዚላንድ በሁለት የወቅር እና በ2 የብር እያንዳንዳቸው 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል ። ኔዘርላንድ ከኢትዮጵያ የበለጠችው በአንድ የነሐስ ሜዳሊያ ብልጫ በማግኘት በአጠቃላይ 5 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ነው ። ብሪታንያ እና ሰሜን አይርላንድ እንደ ኢትዮጵያ አራት ሜዳሊያዎችን አግኝተው የአምስተኛ ደረጃ ይዘዋል ። አንድ የወቅር እና አንድ የብርሜዳሊያ ያገኘችው ስዊድን በ7ኛ ደረጃ አጠናቃለች ። የካቲት 18 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በዚህ ፉክክር የኢትዮጵያ ብርቱ ተፎካካሪ ጎረቤት ኬንያ በአንድ የነሐስ ሜዳሊያ ብቻ ተወስና 27ኛ ደረጃ ላይ ሰፍራለች ። ጀርመን በአንድ የብር ሜዳሊያ ብቻ እንደ ዩክሬን፤ ፊንላንድ፤ ኩባ እና አፍሪቃዊቷ አልጄሪያ 20ኛ ደረጃን አግኝታለች ። ከአፍሪቃ ኢትዮጵያን ተከትላ የሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው ቡርኪናፋሶ ናት ።
ጃፓን ቶኪዮ ውስጥ ትናንት በተደረገው የማራቶን ሩጫ ፉክክር፦ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሱቱሜ አሰፋ የቦታውን ክብረ-ወሰን በመስበር ጭምር ድል ተቀዳጅታለች ። በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር ድሉ በቤንሰን ኪፕሩቶ በኩል የኬኒያውያን ሆኗል ። ሱቱሜ ውድድሩን ያሸነፈችው 2:15:37 በመሮጥ ሲሆን፤ የራሷን ምርጥ ሰአትም ከ2 ደቂቃ በላይ አሻሽላለች ።
በውድድሩ አምና አሸናፊ የነበረችው ኬንያዊቷ ሮዝመሪ ዋንጂሩ ሁለተኛ ስትሆን የዓለም ሻምፒዮናዋ ኢትዮጵያዊቷ አማኔ በሪሶ ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች። በውድድር ትልቅ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ትውልደ ኢትዮጵያዊት ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሀሰን አራተኛ በመሆን ውድድሯን አጠናቃለች።
የኬንያውያን የበላይነት ጎልቶ በታየበት የወንዶች ምድብ ቤንሰን ኪፕሩቶ አሸናፊ ሆኗል። የገባበትም ሰዓት 2 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ከ2 ሰከንድ ሲሆን ለራሱ ምርጥ ሰዓት በውድድሩ ታሪክ ደግሞ ሦስተኛው ምርጥ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። የሀገሩ ልጆች ቲሞቲ ኪፕላጋት እና ቪንሰት ኪፕኬሞይ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ሲገቡ ለውድድሩ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው እና በርቀቱ የቀድሞ የክብረወሰን ባለቤት ኪፕ ቾጌ 10ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቋል ።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው የማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ ግጥሚያ በሲቲ የበላይነት ተጠናቋል ። ማንቸስተር ሲቲ በአንድ ነጥብ ልዩነት ከሚከተለው የፕሬሚየር ሊጉ መሪ ሊቨርፑል ላለመራቅ ባደረገው ብርቱ ትግል ከመመራት ወደ አሸናፊነት ተሻግሯል ።
ለማንቸስተር ዩናይትድ ቀዳሚውን ግብ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ማርኩስ ራሽፎርድ ነበር ። የማንቸስተር ዩናይትድ ፈንጠዝያ ግን ከመጀመሪያው አጋማሽ በኋላ ብዙም መዝለቅ አልቻለም ። 56ኛው ደቂቃ ላይ ፊል ፎደን አቻ የምታደርገውን ግብ አስቆጠረ ። ቆየት ብሎም በ80ኛው ደቂቃ ላይ ማንቸስተር ሲቲን ለመሪነት ያበቃችውን ሁለተኛ ግቡን ከመረብ አሳረፈ ። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪው አንድ ደቂቃ ላይ ደግሞ የግብ ቀበኛው ኧርሊንግ ኦላንድ ሦስተኛ ግብ በማስቆጠር በፍጹም የማንቸስተር ሲቲ የበላይነት ጨዋታው 3 ለ1 ተጠናቋል ።
በዚህም መሠረት፦ ማንቸስተር ሲቲ በሊቨርፑል በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ በሰበሰበው 62 ነጥቡ በደረጃ ሰንጠረዡ 2ኛ ላይ ሰፍሯል ። ቅዳሜ ዕለት ወደ ኖቲንግሀም ፎረስት ያቀናው ሊቨርፑል ነጥብ ከመጣል ለጥቂት የተረፈው ጨዋታው መጠናቀቁን የሚያውጀው የዳኛው ፊሽካ ሊነፋ ቅጽበት ሲቀረው ነበር ። ያለምንም ግብ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆም ያለምንም ግብ የዘለቀው የሁለቱ ግጥሚያ በጭማሪው 9ኛ ማለትም 99ኛ ደቂቃ ላይ ግን በዳርዊን ኑኔዝ ግብ ነገሮች ተገለባብጠዋል ። ግቡ ከተቆጠረ በኋላ ዳኛው ጨዋታው መጠናቀቁን በፊሽካቸው አብስረዋል ። ለሊቨርፑል ተጨዋቾች፤ አሰልጣኝ እና ደጋፊዎች ግን የፈንጠዝያቸው መጀመሪያ ነበር ። በዚህች ብቸኛ ግብ ሊቨርፑል የመሪነቱን ስፍራ አስጠብቋል ። ሰሞኑን ቸልሲን አሸንፎ የካራባዎ ዋንጫን ላነሳው ሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ ግስጋሴ እጅግ ወሳኝ ድል ነበር የቅዳሜው የማታ ማታ ድል ። የካቲት 11 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
አርሰናል ዛሬ ማታ ተስተካካይ ጨዋታውን ከሼፊልድ ዩናይትድ ጋ ያደርጋል ። በ58 ነጥብ ሦስተኛ ነው ። ካሸነፈ በማንቸስተር ሲቲ የሚበለጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ይሆናል ማለት ነው ። ከመሪው ሊቨርፑል ደግሞ በሁለት ። ያም በመሆኑ የምሽቱ ግጥሚያ ለአርሰናል የሞት ወይ ሽረት ነው ።
ቅዳሜ ዕለት ሉቶን ታወንን 3 ለ2 ያሸነፈው አስቶን ቪላ በ55 ነጥብ አራተኛ፤ ክሪስታል ፓላስን 3 ለ1, የሸኘው ቶትንሀም 50 ነጥብ ይዞ 5ኛ ነው ። ሉቶን ታውን፤ በርንሌይ እና ሼፊልድ ዩናይትድ በ20፤ እና 13 ነጥብ ከ18ኛ እስከ 20ኛ ድረስ ከታች በወራጅ ቃጣናው ተደርድረዋል ።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ትናንት ሆፈንሀይም ቬርደር ብሬመንን 2 ለ1 አሸንፏል ። አንድ ተጨዋቹን በቀይ ካርድ ያጣው ኮሎኝ በሜዳው ሌቨርኩሰንን ገጥሞ የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። በተመሳሳይ ከገዛ ሜዳው አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ የተሰናበተበት ቦሁም በላይፕትሲሽ የ4 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ቮልፍስቡርግ በሽቱትጋርት 3 ለ2 ተሸንፏል ። የሳምንቱ ብርቱ ሽንፈት በተባለለት ግጥሚያ አውግስቡርግ ወደ ሀይደንሀይም አቅንቶ በ6 ግብ ተንበሽብሾ ተመልሷል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዑኒዮን ቤርሊንን በአልተን ፎይርስተራይ ስታዲየም ቤርሊን ከተማ ውስጥ 2 ለ0 ድል አድርጓል ። ማይንትስ ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋ አንድ እኩል ፤ ፍራይቡርግ ከባዬርን ሙይንሽን ሁለት ለሁለት ተለያይተዋል ። የጥር 20 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የቡንደስ ሊጋውን የደረጃ ሰንጠረዥ ባዬርን ሌቨርኩሰን በ64 እየመራ ነው ። ባዬርን ሙይንሽን በዐሥር ነጥብ ርቀት ዝቅ ብሎ ይከተላል ። ሽቱትጋርት 50 ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ 44፤ ላይፕትሲሽ 43 ነጥብ ሰብስበው በቡንደስሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ 4ኛ እና 5ኛ ናቸው ። ባለ 37 ነጥቡ አይንትራኅት ፍራንክፉርት 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።
ኮሎኝ በ17 ነጥቡ 16ኛ ወራጅ ቀጣና ጠርዝ ላይ ሰፍሯል ። ማይንትስ እና ዳርምሽታድት በ16 እና 13 ነጥብ 17ኛ እና 18ኛ ደረጃ ላይ ከታች ተደርድረዋል ።
ላሊጋ
በስፔን ላሊጋ ቅዳሜ ዕለት ከቫሌንሺያ ጋ ሁለት እኩል የተለያየው ሪያል ማድሪድ በ66 ነጥብ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው ። ሪያል ማድሪድ 100ኛው ደቂቃ ላይ ጁድ ቤሊንግሀምን በቀይ ካርድ አጥቷል ። ትናንት በማዮካ የ1 ለ0 ሽንፈት የገጠመው ጂሮና 59 ባርሴሎና 58 ነጥብ ሰብስበው 2ኛ እና 3ኛ ናቸው ። አትሌቲኮ ማድሪድ በ55 ነጥብ፤ አትሌቲክ ክለብ በ50 ነጥብ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። 42 ነጥብ ያለው ሪያል ቤቲስ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ካዲዝ፤ ግራናዳ እና አልሜሪያ በ19፤14 እና 9 ነጥብ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ይገኛሉ ።
ሴሪኣ
በጣሊያን ሴሪኣ ኢንተር ሚላን በ69 ነጥብ እየመራ ነው ። ጁቬንቱስ በ57፤ ኤስ ሚላን በ56 ነጥብ2ኛ እና 3ኛ ናቸው ። ቦሎኛ በ51 በጥብ 4ኛ፤ ሮማ በ47 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። 23፤ 20 እና 14 ነጥብ ያላቸው ካግሊያሪ፤ ሳሱዎሎ እና ሳሌርኒታና ከ18ኛ እስከ 20ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ