1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካፋ ዞን ተፈናቃይ አርሶአደሮች ስሞታ

ማክሰኞ፣ የካቲት 19 2016

ሀብትና ንበረት ወደ አፈራንበት ዴቻ ወረዳ በመመለሰ እንደሚያቋቁሙን በተደጋጋሚ ገልጸውልን ነበር የሚሉት አርሶአደሮቹ “ ነገር ግን የተገባው ቃል አሁን ድረስ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም ፡፡ ይልቁንም የክልሉ መንግሥት የአርሻ መሬታችንን ለባለሀብቶችና ግለሰቦች መሰጠቱን መረጃ አግኝተናል ይላሉ።

ከካፋ ዞን ተፈናቃዮች በከፊል
ከካፋ ዞን ተፈናቃዮች በከፊልምስል DW/S. Wegayehu

“ መሬታቸን ለባለሀብቶች ተሰጥቶብናል “ የካፋ ዞን ተፈናቃይ አርሶአደሮች

This browser does not support the audio element.

አርሶአደር አማረች ኦላንጎ እና ጴጥሮስ አጥናፉ በ1996 ዓ.ም እነሱን ጨምሮ 267 አባወራዎች  በሠፈራ መረሃ ግብር አማካኝነት ከከምባታ ወደ ካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ መሄዳቸውን ያስታውሳሉ ፡፡ በወረዳው ሻሎ ፣ ዘንባባ እና አንገላት በተባሉ ቀበሌያት የተሻለ ህይወት መምራት ጀምረው እንደነበርም ተፈናቃዮቹ ይናገራሉ ፡፡

 ይሁንእንጂ በ2011 ዓ.ም በአካባቢው በሚገኙ ታጣቂዎች በደረሰባቸው ጥቃት ወደ ከምባታ  ዞን በመፈናቀልዛሬም ድረስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ነው ለዶቼ ቬለ የገለጹት ፡፡ አርሶአደር አማረች ምሬታቸውን ሲገልጹ “ አሁን ላይ እንደሰው መኖር ከብዶናል፤  ቤት ንብረት የለንም ፡፡ ይዘን የመጣነውን ገንዘብ ጨርሰናል ፡፡ የምንበላው የለንም ፡፡ ልጆቻችንም  ከትምህርት ውጭ ሆነዋል “ በማለት ተናግረዋል ፡፡

ክልሉ ተፈናቃዮችን መልሶ ማስፈር ለምን ተሳነው ?  


አርሶአደር አማረች ኦላንጎ እና ጴጥሮስ አጥናፉ  ክልሉ ወደ ቀደመ ቦታቸን ሊመልሰን  ያልቻለው የአርሻ መሬታችንን ለባለሀብቶችና ግለሰቦች በመሰጠቱ ነው ይላሉ ፡፡ የቀድሞው የደቡብ ክልልም ሆነ አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ባለሥልጣናት  ሀብትና ንበረት ወደ አፈራንበት ዴቻ ወረዳ በመመለሰ እንደሚያቋቁሙን በተደጋጋሚ ገልጸውልን ነበር የሚሉት አርሶአደሮቹ “ ነገር ግን የተገባው ቃል አሁን ድረስ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም ፡፡ ይልቁንም የክልሉ መንግሥት የአርሻ መሬታችንን ለባለሀብቶችና ግለሰቦች መሰጠቱን መረጃ አግኝተናል ፡፡ አቤቱታችንን ለፌዴራሉ መንግሥት እና ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አመልክተናል  “ ብለዋል ፡፡

እውን የተፈናቃዮቹ መሬት ለባለሀብቶች ተሰጥቷል ?

ከካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ የተፈናቀሉ አርሶአደሮች አቤቱታችንን አስገብተናል ያሉት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጉዳዩን የተፈናቃይ አርሶአደሮችን ጉዳይ እየተከታተለ እንደሚገኝ አስታውቋል ፡፡ አርሶአደሮቹ አቤቱታቸውን ህዳር ወር 2015 ዓም በኮሚሽኑ በሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በኩል ማቅረባቸውን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ አርሶአደሮቹ በሠፈራ ከነበሩባቸው አካባቢዎች በ2011 ዓም ቢፈናቀሉም እስከአሁን ዘላቂ መፍትኄ ሳያገኙ በችግር ውስጥ እንደሚገኙ ምክትል ኮሚሽነሯ ተናግረዋል ፡፡

የተፈናቃዮቹ የእርሻ መሬት ለሦስተኛ ወገን ተላልፎ ተሰጥቷል በሚል በቀረበው ቅሬታ ዙሪያ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ “ ከሚመከለታቸው የክልሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገናል ፡፡ የተወሰነው መሬት ለባለሀብቶች መሰጠቱና የተወሰነው ደግሞ በግለሰቦች መያዙ ነው የተገለጸለን ፡፡ መሬት ሳይኖራቸው መሬት አለን ብለው ከተፈናቃዮች ጋር አብረው የተካተቱም አሉ ፡፡ ይህን ማጣራት አለብን ብለውናል ፡፡ ትክክለኛ የመሬት ይዞታውን ካተጣራ በኋላ መሬታቸው እንደሚመለስ ቃል የተገባ  ቢሆንም እስከአሁን ግን ይህ ተፈጻሚ አልሆነም ፡፡ በእኛ በኩል የተባለው እንዲፈጸም  ክትትል እያደረግን እንገኛለን  “ ብለዋል  ፡፡
ዶቼ ቬለ ተፈናቃዮቹን ወደ ቀደም ቦታቸው ለመመለስ ያልተቻለበትን ምክንያት ከከፋ ዞን የዴቻ ወረዳ አስተዳደርም ሆነ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ የሥራ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት አድርጓል ፡፡ ይሁን እንጂ የሥራ ሃላፊዎቹ “ ስብሰባ ላይ ነን “ ከሚል በአጭር የእጅ ሥልክ መልዕክት ከመመለስ በስተቀር ጥሪ አንስተው ምላሽ መሰጠት ባለመቻላቸው በዚህ ዘገባ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም ፡፡


ሸዋንግዛው ወጋየሁ
የሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW