1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያው ተቃውሞ እና የፕሬዝዳንቱ ዛቻ፤ የደቡብ ሱዳን ተፈናቃዮች

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 15 2015

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሀገሪቱ በሚካሄደው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ላይ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ሩቶ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማካሄድ ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን መብቶችችን አለአግባብ በመጠቀም አመጽ በመቀስቀስ የህዝቦችን ደኅንነትና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥሉ ያሏቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን መንግሥታቸው እንደማይታገስ አስጠንቅቀዋል።

Kenia | Protest Steuererhöhung
ምስል James Keyi/REUTERS

የኬንያው ተቃውሞ እና የፕሬዝዳንቱ ዛቻ፤ የደቡብ ሱዳን ተፈናቃዮች

This browser does not support the audio element.

የታክስ ጭማሪንና የኑሮ ውድነትን በመቃወም በተለያዩ የኬንያ ከተሞች የሚካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች በፖሊስ ጫና ምክንያት በዚህ ሳምንት ረገብ ያሉ መስሏል። በቀደሙት ሳምንታትም ተካሂደው በነበሩት ሰልፎች በፀጥታ ኅይሎችና በሰልፈኞች መካከል በተነሱ ግጭቶች  ከ6 በላይ ሰዎች ተገድለዋል በርካቶች ቆስለዋል። በግጭቱ ሰበብ ነባር የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ጨምሮ ቢያንስ 300 ሰዎች ታስረዋል። የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሀገሪቱ በሚካሄደው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ላይ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ሩቶ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማካሄድ ሕገ መግንሥቱ የሰጣቸውን መብቶችችን አለአግባብ በመጠቀም አመጽ በመቀስቀስ የህዝቦችን ደኅንነት እና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥሉ ያሏቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን መንግሥታቸው እንደማይታገስ አስጠንቅቀዋል። 
« እንደ ቀድሞው አይቀጥልም። ሕገ መንግሥቱ የሰጠንን መብት ረብሻን ለመቀስቀስ፣ስርዓተ አልበኝነትን ለመፍጠር፣የሰዎችን ሕይወት ለማጥፋት አንጠቀምበትም። በተለይ ከተወሰኑ ህገ መንግሥታዊ መብቶች  ጀርባ ተደብቀናል። ይኽው ሕገ መንግስት ለመንግሥት ፣ለሕይወት፣ ለንብረት፣ለሁሉም ኬንያውያን ጥቅሞች ጥበቃ የማድረግ ሃላፊነት ይሰጣል።»
በራይላ ኦዲንጋ የሚመራው ተቃዋሚ ፓርቲ ካለፈው ረቡዕ እስከ አርብ ድረስ የጠራው የተቃውሞ ሰልፎች ካለፉት ሳምንታት አንስቶ ሲካሄድ የቆየው ተቃውሞ ሦስተኛ ዙር ነው። በረቡዕ ተቃውሞ በተለይ በዋና ከተማይቱ በናይሮቢ በኪቤራ ክፍለ ከተማ ሰልፈኞች ጎማዎች ሲያቃጥሉ እና ፖሊሶችም ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ ፖሊስ በአጸፋው ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጢስ ተኩሷል። በዚህ የተነሳም በማግሥቱ በማዕከላዊ ናይሮቢ የንግድ መደብሮችና ትምሕርት ቤቶች ተዘግተዋል። ፖሊስ በየመንገዱም ኬላ ዘርግቶ ቁጥጥር ሲያደርግ ነበር። 
ባለፈው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተወዳድረው የተሸነፉት ተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ኬንያውያን በሙሉ መሳተፍ አለባቸው ይላሉ።ኦዲንጋ ተቃውሞዎች እንዲራዘሙ የተወሰነው የህዝቡ የለውጥ ጥያቄ እያየለ በመሄዱ ነው ይላሉ።ስለዚህ ሰልፉ መደረግ አለበት ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።
«እንደ ኬንያውያን ሁሌም ስናደርግ እንደነበረው ራሳችንን ነጻ የማውጣት ሃላፊነት አለብን።ይህ ቀላል ሆኖም አያውቅም።ቀላልም አይሆንም ሆኖም ግን መደረግ አለበት»
በኬንያ የኑሮ ውድነት እና በነዳጅ ምርቶች ላይ የተጣለው አዲሱ የታክስ ጭማሪ ባለፈው መስከረም ሥልጣን በያዘው በሩቶ መንግሥት ቅር የተሰኙ የበርካታ ኬንያውያን ጭንቀት እንዲጨምር አድርጓል። የናይሮቢው ነዋሪ ማርቲን ኦሎ ከነዚህ አንዱ ናቸው። ኦሎ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት በኬንያ የኑሮ ሁኔታ ካልተደሰቱት ተቃዋሚዎች ጋር ድምጻቸውን ማሰማት ይፈልጋሉ።ትንኮሳ ያሉት የፀጥታ ኃይሎች እርምጃም አሳስቧቸዋል። 
«እኛን ስለ ሰላም ለማስታወስ እዚህ መምጣት አይችሉም። ሰላማችንን ለማደፍረስ እዚህ ለምንድነው የሚጡት?እኛ ሰላማዊ እንደሚሆን በደንብ እናውቃለን እዚህ መጥተው ግን ሊያውኩን አይገባም።»
ባለሥልጣናት እንዳሉት ባለፈው ሳምንት በተካሄዱ ተመሳሳይ ሰልፎች ላይ ቢያንስ የ15 ሰዎች ሕይወት አልፏል።በርካቶችም ቆስለዋል። የሀገር ውስጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፖሊስም ሰልፈኞችም ሕግና ስርዓት እንዲያከብሩ ተማጽነዋል።በርካታ አብያተ ክርስቲያንና የሲቪል መብቶች ተከራካሪ ቡድኖች ተቃውሞዎቹ እንዲቆሙ ጠይቀዋል።ፕሬዝዳንት ሩቶና ተቃዋሚው ኦዲንጋም ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።  የበርካታ ሀገራት ኤምባሲዎች በዚህ ሳምንት በጋራ ባወጡት መግለጫም ሁሉም ወገኖች ስጋቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ በሚካሄድ ትርጉም ባለው ውይይት  እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ሆኖም ሩቶ ታክስ የጨምሩት የደሀውን ጥቅም ለማስከበር ነው የሚሉ በርካታ ኬንያውያን የውይይቱ ሀሳብ ተቃዋሚዎች ናቸው። ሩቶን ከመረጡት ቅር የተሰኙ እንዳሉ ሁሉ ተቃዋሚዎች ደግሞ ለውጥ ይመጣል በሚል ተስፋ ጎዳናዎችን በተቃውሞ ማጨናነቁን መቀጠል ይፈልጋሉ 

ምስል Thomas Mukoya/REUTERS
ምስል Thomas Mukoya/REUTERS
ምስል Isaac Mugabi/DW

የደቡብ ሱዳን ተፈናቃዮች 
ለብዙ አሥርት ዓመታት የዘለቀው የደቡብ ሱዳን ቀውስ ከቀያቸው ያስደዳቸው በቤንቱና በዩኒቲ ስቴት መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሴቶች በሕይወት ለመቆየት አማራጭ መንገዶችን ለመፈለግ ተገደዋል። አብዛኛዎቹ ሴቶችና ቤተሰቦቻቸው ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ጎርፍ መንደራቸውንና መተዳደሪያቸውን ጠራርጎ የወሰደባቸው ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ በመንግሥት ኃይሎችና በአሁኑ የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር ታማኞች መካከል ሀገሪቱ ከዛሬ 12 ዓም በፊት ነፃነትዋን ካወጀች በኋላ በተካሄደው ውጊያ ወቅት ነው የተፈናቀሉት።
አንጀላ ንያታባ ማንዩንግ ከግብረ ሰናዩ ድርጅት «ዓለም አቀፉ ሕይወት አድን ኮሚቴ» በምህጻሩ IRC ድጋፍ ከሚያገኙ ሴቶች አንዷ ናቸው።«ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ሕይወት ወደ ቀድሞው እንደሚመለስ፣ጥሩም እንደሚሆን ነበር ያሰቡት። ይሁንና አሁን ደግሞ ከቤታቸው ካፈናቀላቸውና መንደራቸውን ካወደመባቸው ከጎርፍ ጋር ሌላ ጦርነት ላይ ነን ይላሉ።ከጎርፉ አደጋ በፊት ከብቶች እና ፍየሎች ነበሯቸው፣ልጆቻቸውንም ትምሕርት ቤት መላክ ይችሉ ነበር። አሁን ግን ሁሉም ነገር የለም።በአይ አር ሲ እርዳታ ነው የሚኖሩት። እርሳቸው እንደሚሉት ድርጅቱ መልሰው እንዲቋቋሙ እየረዳቸው ነው
«ከቀውሱ ወዲህ ሴቶች የሚገፉት ሕይወት በጣም አስቸጋሪ ነው። በርካታ ሴቶች ሊያግዟቸው የሚችሉትን ባሎቻቸውን እና ልጆቻቸውን አጥተዋል። ሆኖም በአይ አር ሲ ድጋፍ ህይወታችንን የቀየሩ ፕሮጀክቶችን መጀመር ችለናል። ወደ መደበኛ  ሕይወት መመለስ ነው የምንፈልገው።»
ማኑዩንግ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣የደቡብ ሱዳን ሴቶች ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ አቅማቸው አነስተኛ በመሆኑ በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመዋቸዋል። እንደ አይ አር ሲ ያሉ የእርዳታ ድርጅቶች ቤንቱ ለሚገኙ ሴቶች ቡድን እንዲመሰርቱ በማድረግ ጥልፍ እንዲማሩ የገበያ ቦታዎችን ማዘጋጀት እና ምግቤቶችን መክፈት እንዲችሉ ያግዟቸዋል። ሴቶቹ ከምርቶቹ ከሚያገኙት ገቢና ከሚቆጥቡት ገንዘብ ቤተሰቦቻቸውን በተሻለ ሁኔታ መንከባከብ ይችላሉ። 
«መቆጠብ ከጀመርን በኋላ ሕይወታችን ተሻሽሏል። ምክንያቱም በጋራ ነው የሚንቆጥበው።ከቡድኑ ስበደር ከተገዙት እና ከተሸጡት እቃዎች ትርፍ አገኛለሁ። በፊት በደረሰብን የስነ ልቦና ቀውስ ምክንያት ሕይወት ለኛ አስቸጋሪ ነበር።አንድም ጊዜ እንጨት ለቀማ ወደ ደን ሄደን አናውቅም። ምክንያቱም እንጨት ፍለጋ ስንሄድ ልንደፈር እንችላለን።»
ማንዩንግ ኑሮአቸውን ለማስቀጠልና ሕይወታቸውን ለማሻሻል ከአይ አር ሲ ፣ ብድርና ንግድ ለመጀመር መነሻ ካፒታል ከሚያገኙ ሴቶች አንዷ ናቸው። ማንዩንግ ዳንቴል ይሰራሉ። በዚሁ ሞያ አንድ ሺህ የደቡብ ሱዳን ፓውንድ ማለትም አንድ ዶላር ከሀምሳ ሳንቲም እየተከፈላቸው ሌሎች ሴቶችንም እያሰለጠኑ ነው።
«የጠረጴዛ ልብስ የአልጋ ልብስ እሰራለሁ ከዚህ በማገኘው ገቢ የፕላስቲክ የእቃ መያዣ ሳጥኖችን ከጁባ አዝና እዚህ ቤንቲዩ አትርፌ እሸጣቸዋለሁ። ከዚህ የማገኘው ገንዘብ ብድሬን ለመክፈል የልጆቼንም ትምህርት ቤትለመክፈል ያግዘኛል።»
በመጠለያው ውስጥ የሚኖሩት ማንዩንግና ሌሎች ሴቶች በየወሩ አንድ ሺህ የደቡብ ሱዳን ፓውንድ ይቆጥባሉ። ወደፊት ትናንሽ ንግዶችን ለመጀመር የመበደር እድልም ይኖራቸዋል። በመጠለያው ውስጥ የምትገኘው  የ32 ዓመትዋ ኤሊዛቤት ናያቱዋክ ባልዋ እርሷን እና ሦስት ልጆችዋ ትቶ ሌላ ሴት ይዞ ጥሏት ኻርቱም ገብቷል። ሆኖም በአይ አር ሲ ድጋፍአሁን ዳንቴል መስራት ተመራ ራሷን ለማገዝ እየጣረች ነው። 
ባሌ ጥሎኝ ከሄደ አንስቶ አይ አር ሲ በሕይወት መቆየት የምችልበትን ሙያ አስተምሮኝ፣ ለኑሮዬ የሚሆነኝ ገንዘብ አገኛለሁ። አሁን እኔ ጋር የሚኖሩትን አማቼን ጨምሮ ቤተሰቦቼን መንከባከብ ችያለሁ።»
ማንዩንግንና ንያቱዋክን የመሳሰሉ ሴቶችን ከመርዳት በተጨማሪ አይ አር ሲ ማኅበረሰቡ ከድንጋጤ እንዲያገግም የሙያ ስልጠናና ብድር በመስጠት ህይወቱን እንዲያድስ የሚያስችሉ አገልግሎቶችን ይሰጣል።።ካሮሊን ንኪዴ ሴክየዋ የድርጅቱ የደቡብ ሱዳን ተጠሪ ናቸው።ደቡብ ሱዳን የዜጎቿን ተግዳሮቶች ለመወጣት ማገገምንና ልማትን ባ,ንድ ላይ ማስኬድ ያስፈልጋታል ይላሉ።
«ዘላቂ መፍትሄዎችን በማፈላለግ፣ በመሠረተ ልማት፣ተግባራዊ ሊሆኑ በሚችሉ የአሰራር ስልቶች እና የደቡብ ሱዳንን ልማት የሚያጠናክሩ ሙያዎች ላይ ገንዘብ እንዲወጣ አይ አር ሲ ከመንግሥት ጋር በቅርበት ይሰራል። ሰዎች ወደ ቀድሞ መኖሪያዎቻቸው ሲመለሱ፣ድርጅቶች እንዲከፍቱ፣ መልሰው እንዲቋቋሙ፣ትምህርት ቤቶች፣ውኃ፣የንጽህና አጠባበቅ፣የስራ እድሎች ሊኖሩ ይገባል።የስነልቦና ድጋፎችም ያስፈልጋሉ።»
ንያንቴክ ወደ መንደሮቻቸው እንዲመለሱ የሀገራቸው የሰላም ድርድር እንዲፋጠን የሚመለከታቸውን ይማጸናሉ።እርሳቸው እንደሚሉት በደቡብ ሱዳን የሆነውን በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግት ነው። ምንም እንኳን የነዳጅ ዘይት ዋጋ መጨመር የሱዳንን ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት ገቢ ከፍ ቢያደርገውም፣ደቡብ ሱዳን አሁንም ጦርነቱ ባስከተላቸው እጅግ ትላላቅ የኤኮኖሚ ተግዳሮቶች ተጋርጠውባታል። ሀገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልከው ምርት ነዳጅ ዘይት 95 በመቶውን ድርሻ ይይዛል። ሆኖም በ2013 ዓም 350 ሺህ በርሜል ነዳጅ ዘይት ወደ ውጭ ትልክ የነበረችው ሀገሪቱ በጎርጎሮሳዊው 2022 ግን ወደ 150 ሺህ በርሜል ዝቅ ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ የሀገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ዋጋ በ60 በመቶ ቀነሷል። ይህም የደቡብ ሱዳንን የመግዛት አቅም በጅጉ አዝቅ አድርጎታል እንደ አይ አር ሲ ።

ምስል Isaac Mugabi/DW
ምስል Isaac Mugabi/DW

ኂሩት መለሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW