1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንት ሩቶ እንዲነሱ እየጠየቁ ነው

ቅዳሜ፣ ሰኔ 22 2016

ሩቶ ለተቃዋሚዎች የእንነጋገር ጥሪም አቅርበዋል። ይሁንና በወጣቶች የሚመሩት ተቃዋሚዎች ፣ እንደተመረጡ ገቢራዊ ለማድረግ የገቡትን ቃል ባለመፈጸም የሚከሷቸው ሩቶ ስልጣን እንዲለቁ አጥብቀው እየጠየቁ ነው። የሩቶን ውሳኔም ምርጫ አጥተው ነው እንጂ ከልብ የወሰዱት እርምጃ አይደለም እያሉ ነው።

KENIA Proteste in Nairobi
ምስል Monicah Mwangi/REUTERS

የኬንያ ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንት ሩቶ እንዲነሱ እየጠየቁ ነው

This browser does not support the audio element.

የኬንያው ተቃዋሚዎች ፍላጎትና ትችት

ለሳምንታት የተካሄደው የኬንያው ተቃውሞ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የታክስ ጭማሪን ያካተተውን አወዛጋቢውን የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ ከመፈረም ወደ ኃላ እንዲሉ አስገድዷቸዋል። ህዝቡን አደምጣለሁ ሲሉ ባለፈው ረቡዕ ተቃውሞ የተነሳበት ሕግ እንዳይጸድቅ ፊርማቸውን ከማስፈር የተቆጠቡት ሩቶ  የታክስ ጭማሪዎችን የሚመለከቱ አንቀጾች በሙሉ የተሰረዙበትን ረቂቁን እንደገና ወደ ሀገሪቱ ፓርላማ  መልሰውታል። የሩቶ ውሳኔ ለወጣቶቹ ድል ነው። ምንም እንኳን ሩቶ ለተቃዋሚዎች ጥያቄ እጅ ቢሰጡም ተሰሚነት ያላቸው የፖለቲካ አራማጆች ተቃውሞው በዚህ እንደማይቆም ተናግረዋል። ወጣቶች የሚያመዝኑባቸው ተቃዋሚዎች የሩቶን እርምጃ ትንሽና የረፈደ ሲሉ ተችተው ከዚህም ከፍ ያሉ በሀገሪቱ ስር የሰደዱ ሙስናና የአስተዳደር ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ዓላማቸው መሆኑን እያሳወቁ ነው። 

ወጣት ኬንያውያን እንደሚሉት ፕሬዝዳንት ሩቶ ባለፈው ረቡዕ ያስቆሙት የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ የኬንያ ኤኮኖሚ ቢያድግም በርካታ ወጣቶች ስራ የማግኘት ተስፋቸው በመነመነባት በሀገሪቱ እንደወረርሽኝ የተስፋፉት በርካታ ችግሮች አንዱ ምልክት ብቻ ነው።ስለሆነም ወጣት ተቃዋሚዎቹ በኬንያ የታክስ ጭማሪ መሰረዝ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ስር በሰደዱት ችግሮች ላይም ለውጦችን ማየት ይሻሉ ። ይህን ለማሳካትም ይህ ተቃዋሚ እንደተናገረው ኬንያ በወጣቶች የምትመራ እንድትሆን ይፈልጋሉ። « በአሁኑ ጊዜ ፕሬዝዳንት መሆን የማይገባው ፕሬዝዳንት ነው ያለን። ፕሬዝዳንቱ ዊሊያም ሳሙኤል ሩቶ በሕገ መንግሥቱ ላይ የራሱን ትዕዛዝ ያስፈጽማል። ሕገ መንግሥቱ በጣም ጥሩ ነው። ሆኖም መንግሥት በህዝብ ለህዝብ የህዝብ ገዥ ነው። አሁን ግን ኬንያን ለወጣቶች የወጣቶችና በወጣቶች የምትመራ እንድትሆን እንቀይራታለን።»

የኬንያውያን ተቃውሞ በናይሮቢምስል Daniel Irungu/EPA

ፕሬዝዳንት ሩቶ ሥልጣን እንዲለቁ እየተጠየቁ ነው

እጣ ፈንታችን እንዲቀየር እንፈልጋለን የሚሉት ተቃዋሚዎች ሩቶ ከስልጣን ይነሱ እያሉም ነው። ዶቼቬለ ያነጋገራት ኬንያዊቷ ጋዜጠኛ ዊኒ ካሙ እንዳለችው ወጣቶቹ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ለችግሮቻቸው መፍትሔ እየፈለጉ አይደለም ብለው ነው የሚያስቡት። «ፕሬዝዳንቱ ይልቀቅ ነው የሚሉት። በሀገሪቱ ውስጥ ብዙ ነገሮች እየተከናወኑ መሆኑን ይናገራሉ። ግን ስራ የላቸውም። ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ቅርብ የሆነ ኢንተርኔት ማግኘት የሚችል እና መረጃዎችም ያሉት ወጣት ስራ አጥ ይሆናል። ወጣቶቹ ፕሬዝዳንቱ ለነርሱ እውነተኛ ችግር መልስ እንዳልሰጡ ነው አሁን የሚሰማቸው።»

የኬንያውያን ተቃውሞና የመንግሥት ምላሽ
የኬንያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ፖሊስ ተቃዋሚዎቹን ለማስቆም በወሰደው እርምጃ ቢያንስ 23 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል። ሩቶ ሕጉ ላይ እንደማይፈርሙ ባሳወቁ በማግስቱም ተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከነበሩ ወጣቶች ሁለት ተገድለዋል።

በተቃውሞ ሰልፍ ላይ የነበረ ወጣት በፖሊሶች ተይዞ እየተጎተተ ሲወሰድ ምስል Monicah Mwangi /REUTERS

ተቃዋሚዎች ሕጉ የጸደቀበትን ፓርላማ በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ጥሰው በገቡበት ወቅት ከህንጻው ከፊሉን አቃጥለዋል። ሩቶ ለተቃዋሚዎች የእንነጋገር ጥሪም አቅርበዋል። ይሁንና በወጣቶች የሚመሩት ተቃዋሚዎች ፣ እንደተመረጡ ገቢራዊ ለማድረግ የገቡትን ቃል ባለመፈጸም የሚከሷቸው ሩቶ ስልጣን እንዲለቁ አጥብቀው እየጠየቁ ነው። የሩቶ ውሳኔም ግድ ሆኖባቸው እንጂ ከልብ የወሰዱት እርምጃ አይደለም እያሉ ነው። ዶቼቬለ ያነጋገረው የወጣቶቹ ተቃውሞ አራማጅ እና ኬንያዊው የሕግ ባለሞያ ጂም ሊንዳ ይህን ከሚሉት አንዱ ነው። በርሱ አስተያየት የወጣቶቹ ጥያቄ እንዲሰማ የተኬደበት ርቀት ልብ የሚነካ ነው። የቀጠለው የኬንያ ተቃውሞ
«መሪዎቻችን እኛን እንዲያዳምጡ  ፓርላማው ውስጥ እስከመግባት መደረሱ ልብ ይሰብራል። እርሳቸው ረቂቁ ላይ ያልፈረሙት በግፊቱ እና በመገደዳቸው ምክንያት ነው።ፕሬዝዳንቱ  እጅ የሰጡት ከመልካም ፈቃድ ወይም ከጥሩ አስተሳሰብ አይደለም ፤ይልቁንም ምርጫዎች ስላልነበሯቸው እንጂ»

የተቃውሞው መንስኤና ሩቶ የገቡበት አጣብቂኝ


ተቃውሞውን የጫረው በኬንያ ታሪክ ትልቁ የተባለው የአራት ትሪሊዮን ሽልንግ ወይም የ31.1 ቢሊዮን ዶላር በጀት፣ ዳቦና ነዳጅን ጨምሮ በመሠረታዊ ፍላጎቶች ላይ የታክስ ጭማሪን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ነበር ። ተቃዋሚዎች እርምጃው በኑሮ ውድነት የሚሰቃዩትን  ድሆችንና የሠራተኛውን መደብ በእጅጉ የሚጎዳ ነው በማለት ነው አደባባይ የወጡት።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ተቃውሞው ከተጠከረ በኋላ ለህዝቡ ያደረጉት ንግግርምስል atrick Ngugi/AP Photo/picture alliance

የሩቶ ውሳኔ መንግሥት ታክስ በመጨመር ሊያገኝ ያሰበውን 2.7 ቢሊዮን ዶላር ያስቀራል። መንግሥት ጭማሪውን በሕጉ ያካተተው የበጀት ጉድለቱንና ብድርን ለመቀነስ አስፈላጊ ነው በማለት ነበር። የኬንያ አጠቃላይ እዳ በኬንያ ገንዘብ 10 ትሪሊዮን ሺልንግ ነው ይህም ከሀገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት ወደ 70 በመቶ አካባቢ ይሆናል።  የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኦ ኤም ፣ የአንድ አገር የብድር መጠን ከአጠቃላዩ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት ከ55 በመቶ እንዳይበልጥ ይመክራሉ። በዚህ የተነሳም ሩቶ መንግሥታቸው በአንድ በኩል ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኝ የበጀት ጉድለቱን እንዲቀንስ በሚወተውቱት በዓለም አቀፍ አበዳሪዎች በሌላ በኩል ደግሞ የኑሮ ውድነት በሚያሰቃየው ህዝባቸው ግፊት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። የኬንያው ተቃውሞ በቅርቡ የመቆሙ ምልክት አይታይም። ለሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ትልቅ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ መታቀዱ ተሰምቷል። 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW