1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያው ፕሬዝደንት የጀርመን ጉብኝት እና ማሳሰቢያ

ዓርብ፣ መጋቢት 22 2015

የኬንያው ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ወደ ጀርመን ለጉብኝት የመጡት ሀገራቸው በኑሮ ውድነት ምክንያት በተነሳው ተቃውሞ ውስጥ ሆና ነው። ለሀገራቸው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት መንገድ ለመጥረግ ወደ አውሮጳ የዘለቁት የኬንያው ፕሬዝደንት የዩክሬን ጦርነት ባስቸኳይ መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል።

Berlin Präsident William Ruto Kenia und Kanzler Scholz
ምስል Political-Moments/IMAGO

የኬንያ ፕሬዝደት በጀርመን

This browser does not support the audio element.

የኬንያው ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ወደ ጀርመን ለጉብኝት የመጡት ሀገራቸው በኑሮ ውድነት ምክንያት በተነሳው ተቃውሞ ውስጥ ሆና ነው። የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ባስከተለው ተጽዕኖ ኬንያ ውስጥ የተፈላጊ ሸቀጦች ዋጋ በማሻቀቡ ምክንያት በመንግሥታቸው ላይ የተነሳው የህዝብ ተቃውሞ የተዳከመውን የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ጭራሹን እንዳያሽመደምደው ተሰግቷል። ለሀገራቸው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት መንገድ ለመጥረግ ወደ አውሮጳ የዘለቁት የኬንያው ፕሬዝደንት የዩክሬን ጦርነት ባስቸኳይ መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል። 

የኬንያው ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ወደ ጀርመን የመጡት ከፍተኛ ጫና የደረሰበትን የሀገራቸውን ኤኮኖሚ ማነቃቃት የሚያስችል የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ጥሪ ለማድረግ ነው። በዚህም ከጀርመን ትላልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ከንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ጋር የሁለትዮሽ ንግግግር እና ስምምነቶች ያደርጋሉ። በበርሊን ቆይታቸው ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የዩክሬን ጦርነት በእህል እና የማዳበሪያ ዋጋ አሳሳቢ ጫና ማስከተሉን አመልክተዋል። ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ሀገራቸው ኬንያ አጥብቃ የተቃወመችው ሊከበር የሚገባው ዓለም አቀፍ ሕግና ደንብ መኖሩን በማመን እንደሆነ የተናገሩት ሩቶ ጦርነቱ ባስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።

የኬንያ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ከዶቼ ቬለ ጋር ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉምስል DW

«ባስቸኳይ ማስቆም አለብን። እንዲቆም የሚያደርገው ዘዴም እንፈልግ፤ ኬንያን ጨምሮ የጦርነቱ ሰላባ የሆኑት በርካታ ሃገራት ማዳበሪያ እና እህል ማግኘት እንዲችሉ መርዳት አለብን። ኬንያ እንዲህ ያሉ ሸቀጦችን ከሚያቀርበው ዓለም አቀፍ ሰንሰለት ጥገኛነት ለመላቀቅ ነገሮችን በተለየ መንገድ ለመሥራት ትፈልጋለች። »

አውሮጳ ውስጥ የተከሰተው ውዝግብ አስመልክቶ በዲፕሎማሲው ረገድ አፍሪቃ የፍልሚ ሜዳ ለመሆኗ እየታየ ነው። የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ደቡብ አፍሪቃ፤ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝደንት ደግሞ ጋና የሚያደርጉትን ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው። ከአፍሪቃ ሃገራት ጠንካራ የኤኮኖሚ ትስስር የገነባችው የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ በቅርቡ ሞስኮን ጎብኝተዋል። ቻይና  የዩክሬን ሩሲያን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና ልትጫወት እንደምትችል ለማመላከት እየሞከረች ቢሆንም ዩናይትድ ስቴትስም ሆነች ሌሎች ምዕራባውያን ሃገራት እርምጃዋን በጥንቃቄ ነው የሚመለከቱት። ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ግን ከበርካታ ሃገራት ጋር ስልታዊ ጉድኝት ያላት ቻይና ጦርነቱ እንዲቆም ግፊት ታደርጋለች ባይ ናቸው።

«ስለዚህ ከስልት አኳያ ቻይና ጦርነቱ እንዲቆም ግፊት ማድረግ ይኖርባታል፤ ምክንያቱም ሁላችን ከቻይና ድንበር ባሻገር ከኮቪድ ወረርሽኝ አስከፊ ውጤት ውስጥ ያለፍን ነን። ቻይና ሀብቷን ባፈሰሰችበት አፍሪቃን ጨምሮ በበርካታ የዓለም ክፍሎች ላይ ፍላጎት አላት። በመሠረተ ልማቶች ግንባታ አግዘዋል፤ እንዲሁም ገንዘባቸውን አውጥተዋል። እናም ይኽ ጦርነት በምንም መንገድ እንዲያገግሙም ሆነ በዓለም ላይ ያፈሰሱትን መዋዕለ ንዋይ መልሰው እንዲያገኙ ሊረዳቸው የሚችል አይመስለኝም።»

ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ለኬንያው ፕሬዝደንት ሩቶ አቀባበል ሲያደርጉምስል Annegret Hilse/REUTERS

ኬንያ ውስጥ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ንረት ህዝብን ወደ አደባባይ ለታቃውሞ ማውጣቱ ታይቷል። ፕሬዝደንት ሩቶ ግን ተቃውሞው ከዚህ ጋር አይገናኝም ነው የሚሉት።

«ናይሮቢ ላይ የነበረው ተቃውሞ በአብዛኛው ስለኑሮ ውድነት ሳይሆን ፍርድ ቤት በዘጋው የምርጫ ውጤት ነው። በእርግጥ የዋጋ ንረት ቢኖርም ተፎካካሪዎቻችን አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት እየሞከሩ ነው፤ ሆኖም ግን የኬንያ ህዝብ የበለጠ ብልህ ነው።»

አያይዘውም ለኬንያ ህዝብ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ ከኬንያውያን ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ተቃዋሚዎቻቸው ግን በራስ ወዳድነት እና ውጤት የሌለው ጠባብ አጀንዳን በማነሳሳት ወቅሰዋል።

 ሸዋዬ ለገሠ/ሪቻርድ ዎከር 

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW