1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኬንያ ምረጫ ውጤት ተጽእኖ በጎረቤት አገራት እና ቃጣናው

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 10 2014

ትናንት ውጤቱ ይፋ የሆነው የኬንያ ምርጫ በርካታ አወዛጋቢ ነገሮች እንዳሉትም አብሮ ተነስቷል። ምርጫውን ያስፈጸመው የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን በሁለት መከፈል ጨምሮ የዊሊያም ሩቶን ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጥ አልቀበልም ያሉት ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዳቸው የድህረ ምርጫውን ሂደት ቀላል አላደረገውም።

Wahlen in Kenia I William Ruto
ምስል፦ Thomas Mukoya /REUTERS

ውጤቱ በቀጣናው የራሱ ተጽእኖ አለው

This browser does not support the audio element.

ትናንት ውጤቱ ይፋ የሆነው የኬንያ ምርጫ በርካታ አወዛጋቢ ነገሮች እንዳሉትም አብሮ ተነስቷል። ምርጫውን ያስፈጸመው የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን በሁለት መከፈል ጨምሮ የዊሊያም ሩቶን ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጥ አልቀበልም ያሉት ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዳቸው የድህረ ምርጫውን ሂደት ቀላል አላደረገውም። በዚህ ውዝግም ሳለ የሩቶን መመረጥ ተከትሎ የእንኳን ደስ ያለህ መልእክት ካስተላለፉት ደግሞ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ይገኛሉ። ይህም የሆነው ኬንያ ለኢትዮጵያም ሆነ ለቃጣናው እጅጉን አስፈላጊ አገር በመሆኗ ነው ይላሉ ተንታኞች።

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ምርጫ ያካሄደችው ኬንያ ትናንት በአገሪቱ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን በኩል የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው አሸናፊ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ወንበር ላይ የከረሙት ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ ማሸነፋቸውን ስታስተዋውቅ በአገሪቱ የነበረው ውጥረትና ጉጉት ቀላል አልነበረም፡፡ በአንድ በኩል የተመራጩ ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች ለደስታ አደባባይ ስያጨናንቁ በጠባብ ውጤት ተሸንፈዋል የተባሉት የተቀናቃኙ እጩ ፕሬዝዳንት ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች በፊናቸው መንገዶችን በመዝጋት ቅሬታቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ 
የምርጫ ውጤቱ ከመገለጹ አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ ሰባት አባላት ያለው የምርጫ ኮሚሽኑ በሁለት ተከፍለው የአራት አባላቶቹ ውጤቱን አንቀበልም ማለት ደግሞ ለተቃዋሚዎቹም ሆነ ለኦዲንጋ ውጤቱን በፀጋ አለመቀበል ከበቂ በላይ ምክኒያት ይመስላል፡፡ 

ምስል፦ Ben Curtis/AP/picture alliance

ውጤቱ እጅጉን ተጓቶ በተገለጸው የኬንያ ምርጫ በድህረ ምርጫ ሁኔታዎች ምን ሊያጋጥም እንደሚችልም መገመት ቀላል ሊሆን አልቻለም፡፡ ለአፍሪካ ቀንድ ቃጣና እጅጉን አስፈላጊ እና አንጻራዊ መረጋጋት የሚስተዋልባት ኬንያ ስጋቶችን የማትቆጣጠር ከሆነ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአከባቢው መጥፎ ዜና እንደሚሆን አስተያየታቸውን ካጋሩን ደግሞ ምርጫውን ታዝበው የተመለሱት ፖለቲከኛ እና የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ይገኛሉ፡፡ 

ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የትናንቱ የኬንያው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ አፋጣኝ የደስታ መግለጫ ከላኩት መሪዎች ውስጥ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህምድ ይገኛሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸውም ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ባስተላለፉት መልእክት፤ በሁለትዮሽ እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎትም ገልጸውላቸዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ ዶ/ር ሳሙኤል ተፈራ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈጣን የደስታ መግለጫ መላክ ከሁለቱ አገራት ከፍ ያለ ስልታዊ ግንኙነት ጋር ነው ያያዙት፡፡ የሁለቱ ተቀናቃኝ እጩ ፕሬዝዳንቶች አስቀድሞ በምርጫ ኮሚሽን ላይ ቅሬታ ማንሳት ለድህረ ምርጫው የቀውስ ስጋት ምክኒያት ነው የሚሉት ዶ/ር ሳሙኤል የምርጫ ኮሚሽኑ አባላት ሳይስማሙ ውጤት መገለጽም አግባብነት አይታያቸውም፡፡ 

ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና በበኩላቸው ኬንያ በድህረ ምርጫ በተወሰነ መልኩ ብትፈተንም ወደ ከፋ ግጭት ግን ትገባለች የሚል እምነት የላቸውም፡፡ የፖለቲከኞቹ የከዚህ በፊት የመደራደር ልምድ እና የምዕራባዉያን አገራት ጉዳዮን በቅርበት መከታተል ችግሩ የሰላም እልባት እንዲያገኝ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW