የኬንያ ምርጫ ውጤት መዘግየት ያነገሰው ውጥረት
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 7 2014
በምሥራቅ አፍሪቃ የ57 ሚሊዮን ግድም ሰዎች መኖሪያ የኾነችው ጎረቤት ኬንያ በዚሁ ሳምንት ሀገር አቀፍ ምርጫ አካሂዳለች። ዘንድሮ ለምርጫ ከተመዘገቡ 22 ሚሊዮን መራጮች መካከል ለምርጫ የወጡት ከቀድሞ አንጻር ዝቅተኛ መሆናቸው ተነግሯል። ማክሰኞ ዕለት በነበረው ምርጫ የተሳተፉት 60 በመቶ መሆናቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ዐስታውቋል። ሌሎች ታዛቢዎች ቁጥሩ ከዚያም እጅግ ያነሰ ነው ብለዋል። በ2007 አወዛጋቢው ምርጫ 80 በመቶ ግድም ተመዝጋቢዎች መርጠው ነበር።
የዶይቸቬለ የኬንያ ዘጋቢ አንድሩ ዋሲኬ በዋና ከተማዪቱ ናይሮቢ በመዘዋወር ስለምርጫው ቅኝት አድርጎ ነበር። በሀገር አቀፍ ደረጃ ለምርጫ የወጡት ቁጥራቸው መቀነሱ ቢነገርም ተሳትፎው ግን ንቁ ነበር።
«ከማለዳው አስራ አንድ ሰአት ነበር ወደ ምርጫ ጣቢያ ያቀናሁት። ሰልፉ በጣም ረዥም ነበር፤ በጣም በጣም ረዥም።»
በናይሮቢ ከተማ ምርጫ ከወጡ መራጮች መካከል ዶይቸ ቬለ የተወሰኑትን አነጋግሮ ነበር። በዘንድሮ ምርጫ ለውጥ እንደሚጠብቁ ከገለጡ መካከል ይህ ወጣት ይገኝበታል። ለዚያም ይመስላል ገና ሳይነጋ በሌሊት ምርጫ ጣቢያ የተሰለፈው።
«ሌሊት ዐሥራ አንድ ሰአት ላይ ነው እዚህ የመጣሁት። በምርጫው ሒደት በጣም ደስተና ነኝ። በዚህ ምርጫ የሰጠነው ድምጽፅ ተሰሚነት ይኖረዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በሁሉም መስኮች የሚወክሉንን፤ የሚረዱንን መሪዎች መርጠናል። በዚህ ዓመት ለውጥ ያመጣሉ ብለንም ተስፋ እናደርጋለን።»
በኬንያ ምርጫ ተመራጮች ከቀድሞው በተለየ መልኩ ለውጥ ለማምጣት ቃል መግባታቸው ተስፋ እንድትሰንቅ ያደረጋት ሌላኛዋ ወጣት መራጭ በምርጫ ሒደቱ ደስተኛነቷን እንዲህ ገልጣለች።
«እስካሁን ደህና ነው። ምንም ምርጫውን የሚያደናቅፍ ነገር የለም። ነገሮች በተረጋጋ መንገድ እየኼዱ ነው።»
ኬንያውያን አዲስ ፕሬዚደንት እና የምክር ቤት አባላት ለመሰየም በ291 የምርጫ ክልሎች ሀገር አቀፍ ምርጫ ያካኼዱት ከሞላ ጎደል ሰላማዊ በሆነ መንገድ መሆኑንም ታዛቢዎች ተናግረዋል። የኬንያን ምርጫ ከታዘቡት መካከል የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዚደንት ጃካያ ኪክዌቴ ይገኙበታል። ትዝብታቸውን እንዲህ ገልጠዋል።
«የኬንያ ምርጫ እና ቅድመ-ምርጫን ታዝበናል። የምርጫ ኮሚሽኑ በዘንድሮ ምርጫ ግልፅነትን፣ ለምርጫው ዝግጁነትን እና ሒደቱን በተመለከተ ከፍተኛ መሻሻል መኖሩን የታዛቢ ቡድኑ ተመልክቷል።
ምርጫ ታዛቢው ጃካያ ኪክዌቴ ነጻ እና ተአማኒ ምርጫ እንደታዘቡ ቢመሰክሩም፤ የኬንያ ምርጫ በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የመረጃ መዛባት እንደታየበት ተናግረዋል። በእርግጥ የምርጫ ዘገባ መዛባቱ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ብቻ ሳይሆን በታዋቂ ማሰራጪያ ጣቢያዎችም ተንጸባርቋል። የምርጫ ውጤቱ መጓተት በመላ ኬንያ ውጥረት አንግሷል።
በኬንያው ምርጫ በዋናነት ሁለት ተመራጮች ተፋጠዋል። የኬንያ የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የ77 ዓመቱ ራይላ ኦዲንጋ በአንድ በኩል፤ የኬንያ ምክትል ፕሬዚደንት የ66 ዓመቱ ዊሊያም ሩቶ በሌላ በኩል ምርጫውን ለማሸነፍ አሰፍስፈዋል። በእየ ፊናቸውም ስላገኙት ድል ለደጋፊዎቻቸው ከወዲሁ እየተናገሩ ነው። የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ከኮሚሽኑ ውጪ የምርጫ ውጤት ይፋ እንዳይደረግ አሳስቧል። አጠቃላዩ ውጤት ግን በምርጫ ኮሚሽኑ በኩል ከማክሰኞ በፊት የሚጠበቅ አይመስልም። በእዚህም አለ በዚያ ምርጫ ኮሚሽኑ በኬንያ ሕግ መሠረት ቢዘገይ ቢዘገይ ማክሰኞ ዕለት ውጤቱን ይፋ ማድረግ ይጠበቅበታል። እስከዚያው በኬንያ የምርጫ ውጥረቱ መቀጠሉ አይቀርም።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ