1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኬንያ ምርጫ የዋዜማ ድባብ

ሰኞ፣ ነሐሴ 2 2014

አራት እጩዎች ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታን ለመተካት የሚወዳደሩበት የኬንያ ምርጫ ነሐሴ 3 ይካሔዳል። ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ ለሁለት የሥልጣን ዘመን ኬንያን በመምራታቸው ዳግም ለምርጫ መቅረብ አይችሉም። የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩት ዊሊያም ሩቶ ትልቅ ትኩረት ያገኙ እጩዎች ናቸው።

Kenia Wahlen 2022
ምስል፦ Thomas Mukoya/REUTERS

የኬንያ ምርጫ የዋዜማ ድባብ

This browser does not support the audio element.

የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በሥልጣን ላይ የሚገኘው ጁብሊ ፓርቲ እና ኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ፓርቲ በጋራ የፈጠሩትን አዚሚዮ ላ ሞጃ የተባለ ጥምረት ይመራሉ። ኦዲንጋ የኬንያ ምክር ቤት አባል የነበሩ ሲሆን ያለፉትን ሶስት ዓመታት የአፍሪካ ኅብረት የመሠረተ ልማት ልዩ ልዑክ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።

ኦዲንጋ የምርጫ ማኒፌስቷቸው የኬንያን ኤኮኖሚ መለወጥ ነው። አባታቸው ጃራሞንጊ ኦጊንጋ ኦጊንጋ የመጀመሪያው የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ። የ77 ዓመቱ ፖለቲከኛ ለኬንያ ፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ የአሁኑ 5ኛቸው ነው። ኦዲንጋ ቢመረጡ ምክትላቸው ማርታ ዋንጋሪ ካሩዋ ይሆናሉ።

ራይላ ኦዲንጋ የፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ ድጋፍ አላቸው። ምስል፦ Raila Odinga press Team

ሶስት ፓርቲዎች ያበጁትን ኬንያ ክዋንዛ የተባለ የፓርቲዎች ጥምረት የሚመሩት ዊሊያም ሩቶ ያለፉትን ዘጠኝ ዓመታት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሰርተዋል። ከዚያ በፊት የኬንያ የአገር ውስጥ ጉዳዮች፤ የግብርና እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን መርተዋል።

በቅርቡ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ የኬንያን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን ያላቸውን ዕቅድ የ55 ዓመቱ እጩ ፕሬዝዳንት ተናግረው ነበር። ከገዢው ጁብሊ ፓርቲ የተለያዩት ባለፈው ዓመት ነበር። ሪጋቲ ጋቻጉዋ በምክትል ፕሬዝዳንትነት አብረዋቸው የሚወዳደሩ ናቸው።

ዊሊያም ሩቶ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሰርተዋል። ምስል፦ SIMON MAINA/AFP/Getty Images

ጠበቃ እና የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ዳቪድ ምዋሬ ምርጫውን ያሸንፋሉ የሚል ግምት ከተሰጣቸው ራይላ ኦዲንጋ እና ዊሊያም ሩቶ ጋር የሚወዳደሩ እጩ ናቸው። ሙስናን ለመዋጋት ቃል የገቡት ዳቪድ ምዋሬ ተሳክቶላቸው ቢመረጡ ሩዝ ሙቼሩ ሙቱዋ ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ይሆናሉ።

ሩትስ የተባለ ፓርቲ የሚመሩት ጆርጅ ዋጃኮያህ አራተኛው እጩ ናቸው። ጆርጅ ዋጃኮያህ ቢመረጡ ካናቢስ የተባለውን አደንዛዥ እጽ ኬንያውያን ወደ ውጭ አገር በመላክ ትርፍ እንዲያገኙ ለኢንዱስትሪ እና የሕክምና አገልግሎት ሕጋዊ ሊያደርጉት ቃል ገብተዋል። እጩ ፕሬዝዳንቱ እንደሚሉት ገቢው ኬንያ ያለባትን ዕዳ እና ሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት ያግዛል።

ከአራቱ እጩዎች ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታን የሚተካው ሰው ነገ ነሐሴ 3 ቀን 2014 በሚካሔደው ምርጫ ይለያል። የኬንያን የምርጫ ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ እሸቴ በቀለ መቀመጫውን በናይሮቢ ካደረገ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ጋር አጭር የስልክ ቃለ ምልልስ አድርጓል።

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW