1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ እና የጀርመን የስደት እና የሰለጠኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ሥምምነት

ረቡዕ፣ መስከረም 8 2017

የሰለጠኑ ኬንያውያን ሠራተኞች በጀርመን መሥራት እና መኖር የሚችሉበት ሥምምነት ባለፈው ሣምንት በበርሊን ከተማ ተፈርሟል። ሥምምነቱ በጀርመን የመኖር ፈቃድ የሌላቸው ኬንያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ነው። ኬንያ ለወጣቶቿ አመርቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን 82 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ዕዳዋን ለመክፈል የከበዳት ሀገር ሆናለች።

ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ እና መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ
ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ እና መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ጀርመን የሰለጠኑ ኬንያውያን ሠራተኞች በጀርመን መሥራት እና መኖር የሚችሉበት ሥምምነት ለሁለቱም ሀገሮች ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል። ምስል Christian Ditsch/epd

የኬንያ እና የጀርመን የስደት እና የሰለጠኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ሥምምነት

This browser does not support the audio element.

ኬንያዊቷ ሚሊሰንት ታቲየኖ የአውቶቡስ አሽከርካሪ ለመሆን ስልጠና እየወሰደች ነው። ሚሊሰንት በጀርመን ሥራ ለማግኘት በሚፈቅድ ፕሮጀክት በመሳተፍ ላይ ከሚገኙ ኬንያውያን አንዷ ናት። በስምንት ሣምንታት ገደማ ውስጥ በሰሜን ጀርመን በምትገኘው ፍሌንስቡርግ ከተማ የመኖር ፈቃድ አግኝታ በሰለጠነችበት ሙያ ሥራ ለመጀመር የምትጠብቀው ሚሊሰንት ታቲየኖ “እንደ ኬንያ የተቆፋፈረ መንገድ በሌለበት እና ከቦዳ ቦዳ በማትጋፋበት የጀርመን ጎዳና ላይ ልነዳ በመሆኑ ደስ ብሎኛል” ስትል ተናግራለች።

ለ14 ዓመታት የትምህርት ቤት አውቶቡስ ያሽከረከረው ስቲፊን ሰንደይ በሙያው የተካነ ቢሆንም መንጃ ፈቃዱ በጀርመን እውቅና ስለሌለው ዳግም ስልጠና መከታተል ነበረበት። ላለፉት አስር ዓመታት ወደ ጀርመን አቅንቶ ለመሥራት ሲመኝ እንደቆየ የሚገልጸው ስቲፊን የጀመረው ሒደት ተጠናቆ ወደ አውሮፓዋ ሀገር ሲያቀና ሌሎች ፈተናዎች እንደሚገጥሙት አላጣውም።

“በጀርመን ስላለው ዘረኝነት ሰምቺያለሁ” የሚለው ስቲፈን በጀርመን “በርካታ ጥቁሮች ይኖራሉ። ከሁኔታው መለማመድ ቢኖርብኝም ያን ያክል በእኔ ላይ ጫና አይኖረውም። ለዚያም ዝግጁ ነኝ” የሚል አቋም አለው።

ሚሊሰንት እና ስቲፊንን ጨምሮ ወደ ጀርመን የሚያቀኑ ኬንያውያን አሽከርካሪዎች ቋንቋን ጨምሮ አስፈላጊ ሥልጠናዎች ወስደዋል። የሰለጠኑ ሠራተኞች ከኬንያ የአውሮፓ ግዙፍ ኤኮኖሚ ባለቤት ወደ ሆነችው ጀርመን አቅንተው ለመኖር እና ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ባለፈው ሣምንት መገባደጃ በበርሊን ከተማ ተፈርሟል።

ሥምምነቱን የተፈራረሙት የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር እና የኬንያ የካቢኔ ሚኒስትር ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ናቸው። ሥምምነቱ የተፈረመው መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ በኬንያ ጉብኝቶች ባደረጉባቸው ወቅቶች ከተደረገ ውይይት በኋላ ነው።

ሥምምነቱን የተፈራረሙት የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር እና የኬንያ የካቢኔ ሚኒስትር ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ናቸው።ምስል Maja Hitij/Getty Images

መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ከፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሥምምነቱ ጀርመን እና ኬንያ በስደት ጉዳይ ላይ የበለጠ ለመተባበር የሚያደርጉትን ጥረት የሚያመለክት እንደሆነ ተናግረዋል። ባለፈው ሣምንት አርብ የተፈረመው ሥምምነት በጀርመን የመቆየት መብት የሌላቸው ኬንያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መንገድ የሚጠርግ ጭምር ነው።

ወደ ጀርመን የሚያቀኑ ተገን ፈላጊዎችን እና ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ቆርጦ የተነሳው የሾልስ መንግሥት ባለፈው ሣምንት ጥብቅ የድንበር ቁጥጥር ማድረግ ጀምሯል። በምዕራብ ጀርመን በምትገኘው ዞሊንገን ከተማ በስለት ከተፈጸመው ጥቃት እና ቀኝ አክራሪው አማራጭ ለጀርመን (AfD) በምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ ሁለት ግዛቶች የተካሔዱ ምርጫዎች ካሸነፈ በኋላ የሾልስ ጥምር መንግሥት በሕገ-ወጥ ስደት ላይ ጠንካራ አቋም እንዳለው ለማሳየት ጥረት እያደረገ ነው።

ሾልስ በጀርመን ለመቆየት ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ቁርጠኛ ቢሆኑም የሀገራቸው ኤኮኖሚ የገጠመውን የሠራተኞች እጥረት ለመፍታት የሰለጠነ የሰው ኃይል መቀበል እንደሚያስፈልግ ከኬንያ ጋር ሥምምነት ከተፈረመ በኋላ ከፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። 

ጀርመን በዜጎቿ ዕድሜ መግፋት እና በሰው ኃይል እጥረት ምክንያት ባለሙያዎች እንደሚሉት በየዓመቱ 400,000 የሰለጠነ ሠራተኛ መቀበል ይኖርታባል። ሾልስ “የሰለጠኑ ሠራተኞች ወይም ወጣቶች ለሥልጠና ወደ ጀርመን መምጣት ስለሚችሉ ለኬንያውያን ዕድል ይከፍታል” ሲሉ ተናግረዋል።

 ሥምምነቱ “ለአስርት ዓመታት አብሮን የሚዘልቀውን የሰለጠነ ሠራተኛ እጥረት ለማካካስ ይረዳናል” ያሉት ሾልስ “ከኬንያ ወደ እኛ የመጡ ነገር ግን የመቆየት መብት የሌላቸው ወደፊትም የማያገኙ ሰዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመመለስ የሚያስችል ሥርዓት የሚሰጥ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። ሾልስ “አሁን ወደ ሀገራቸው በቀላሉ እና በፍጥነት መመለስ ይችላሉ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የተፈረመው ሥምምነት “250,000 የሥራ ዕድሎች ለኬንያውያን ወጣቶች ይፈጥራል” ቢሉም የጀርመን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር አስተባብሏልምስል DW

የጀርመን መንግሥት ተመሳሳይ ሥምምነቶች ከሕንድ፣ ጆርጂያ እና ሞሮኮ ጋር መፈራረሙን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።  ከኡዝቤኪስታን እና ኪርጊስታን መንግሥታት ጋር ተመሳሳይ ሥምምነቶች ይፈረማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከሞልዶቫ፣ ፊሊፒንስ እና ጋና መንግሥታት ጋርም ውይይት እየተደረገ ነው። ሁሉም ሥምምነቶች የሰለጠኑ ሠራተኞች ወደ ጀርመን የሚያቀኑበትን መንገድ ሲያመቻቹ በአውሮፓዊቱ ሀገር የመቆየት ፈቃድ ያልተሰጣቸውን ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

በጀርመን ዜና አገልግሎት ዘገባ መሠረት ወደ ሀገሮቻቸው መመለስ አለባቸው የተባሉ 225,000 ስደተኞች በሀገሪቱ ይገኛሉ። በጀርመን ከተመዘገቡ 15,000 ኬንያውያን መካከል እስከ ሐምሌ መጨረሻ ወደ ሀገራቸው መመለስ አለባቸው የተባሉት 818 ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 738 ኬንያውያን በግዳጅ ወደ ሀገራቸው የሚመልሳቸው ውሳኔ በጊዜያዊነት ታግዷል።

ጀርመን በሠራተኞች እጥረት ስትፈተን ኬንያ በአንጻሩ ለወጣት ባለሙያዎቿ የሥራ ዕድል እና በቂ ገቢ መፍጠር ተስኗታል። ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ከዶይቼ ቬለዋ ፋቱዋ ኢሊካ ሙሎሺ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ መንግሥታቸው የተፈራረመው ሥምምነት “250,000 የሥራ ዕድሎች ለኬንያውያን ወጣቶች ይፈጥራል” ሲሉ ተናግረዋል።

የጀርመን ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን “ይህ መረጃ ስሕተት ነው” በማለት ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ የጠቀሱት ቁጥር ትክክል እንዳልሆነ አስታውቋል። መሥሪያ ቤቱ በኤክስ ባሰፈረው አጭር መልዕክት እንዳለው በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተፈረመው ሥምምነት “በጀርመን የመሥራት ዕድል የሚያገኙ የሰለጠኑ ሠራተኞችን ቁጥርም ሆነ ኮታ የሚያካትት አይደለም።” ሁሉም አመልካቾች የጀርመን የሰለጠኑ ሠራተኞች ጥብቅ የፍልሰት ሕግ ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

ሥምምነቱ ከመፈረሙ በፊት ለሙከራ ተግባራዊ በተደረገው ፕሮጀክት አምስት ኬንያውያን የአውቶቡስ አሽከርካሪዎች ፍሌንስበርግ ከተማ ደርሰዋል። በሥምምነቱ መሠረት ኬንያውያን የአውቶቡስ አሽከርካሪዎች፣ የምግብ አብሳዮች እና አረጋውያን ተንከባካቢዎች በጀርመን የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የሾልስ መንግሥት የተወሰኑ የስደት ሕግጋትን ለማላላት ተስማምቷል።

የፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥት ከስደት ጉዳይ በተጨማሪ ሰንጎ ለያዘው የውጪ ዕዳ መፍትሔ ለማበጀት ከጀርመን ዕገዛ ይፈልጋል። ሩቶ ሥልጣን ሲይዙ ሀገራቸው የዕዳ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ ነበር። በወቅቱ የኬንያ የውጪ ዕዳ 62 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 67 በመቶ ደርሶ ነበር።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት የኡኹሩ ኬንያታ መንግሥት ከናይሮቢ እስከ ሞምባሳ የተዘረጋውን 11,000 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባቡር ማጓጓዣ ጨምሮ ግዙፍ መሠረተ-ልማቶች ለመገንባት ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ቻይናን ከመሳሰሉ ሀገራት ያለ ቅጥ ተበድሯል። አብዛኞቹ ብድሮች ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልባቸው ከመሆናቸው ባሻገር የተገነቡት መሠረተ-ልማቶች የተጠበቀውን ገቢ አላስገኙም። እንዲህ አይነቱ ተቃርኖ የኬንያ ጎረቤት የሆነችው ኢትዮጵያን ጭምር በዕዳ ያጎበጠ ነው።

የፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ያዘጋጀውን የ2024 የፋይናንስ አዋጅ በመቃወም ዜጎች አደባባይ ሲወጡ ጸጥታ አስከባሪዎች በከፈቱት ተኩስ በርካቶች ተገድለዋል። ምስል Thomas Mukoya/REUTERS

ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ “ዛሬ እየከፈልን ያለንው ከ10 ዓመታት ገደማ የተበደርንውን ነው። ዕዳችን ከ1.8 ትሪሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወደ 10 ትሪሊዮን ሽልንግ አድጓል”  ሲሉ አስረድተዋል።  

ኬንያ ካለባት 82 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ወደ 8 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ከቻይና የተበደረችው ነው። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ ዓለም ባንክ፣ አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያን የመሳሰሉ ሀገሮችም ከኬንያ አበዳሪዎች መካከል ይገኙበታል።

የዊሊያም ሩቶ መንግሥት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ድጋፍ የሚያደርግላቸውን የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል። ኬንያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.9 ቢሊዮን ዶላር እንድትበደር መንገድ የጠረገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ኡኹሩ ኬንያታ ሥልጣን ላይ ሳሉ ዊሊያም ሩቶ ምክትል ፕሬዝደነት በነበሩበት በጎርጎሮሳዊው 2021 ነው።

ለ38 ወራት የሚዘልቀው ሥምምነት ኬንያ የገጠማትን የዕዳ ጫና ለማቃለል እና ለግሉ ዘርፍ መዋዕለ ንዋይ የተመቻቸ ኤኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታ ለመፍጠር የተወጠነ ነበር። ሁሉም ግን እንደታቀደው አልሰመረም። የኬንያ መንግሥት ለነዳጅ እና የአፈር ማዳበሪያ ግብይት የሚያደርገውን ድጎማ አቋርጦ የነበረ ቢሆንም በጎርጎሮሳዊው 2023 ተቃውሞ ሲቀሰቀስ የነዳጅ ድጎማ ወደ ነበረበት እንዲመለስ አድርጓል።

ለ2024 የተዘጋጀው የኬንያ የበጀት አዋጅ መንግሥት የቀረጥ ጭማሪ በማድረግ ተጨማሪ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ቢታቀድም በሀገሪቱ በተቀሰቀሰ ኃይለኛ ተቃውሞ ምክንያት ሳይጸድቅ ቀርቷል። የቀረጥ ጭማሪውን ተቃውመው አደባባይ የወጡ ኬንያውያን ላይ ፖሊስ በከፈተው ተኩስ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።

በወጣቶች የሚመሩት የኬንያ ተቃዋሚዎች በጸጥታ አስከባሪዎች ለተገደሉ ዜጎች ፍትኅ ከማረጋገጥ ባሻገር ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ሥልጣን እንዲለቁ እስከመጠየቅ ደርሰዋል። ዊሊያም ሩቶ ሥልጣን ለቀቁም አልለቀቁ ኬንያን ለወጣቶቿ አመርቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ዕዳዋንም መልሶ ለመክፈል የገጠማት ፈተና ግን እንዲህ በቀላሉ መፍትሔ የሚያገኝ አይደለም።

እሸቴ በቀለ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW