የኬንያ ጊዚያዊ ሁኔታ ከጋሪሳ ጥቃት በኋላ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 3 2007ያካባቢው ዕለታዊ ጋዜጣ «ዘ ደይሊ ኑሽን» እንዳመለከተው፣ ፖሊስ በጊዜ ዩኒቨርሲቲው ደርሶ ቢሆን ኖሮ ምናልባት ጭፍጨፋውን ማስወገድ ወይም ቢያንስ የሟቾችን ቁጥር ዝቅ ማድረግ ይቻል እንደነበረ ተገምቶዋል። አራቱ የአሸባብ ታጣቂዎቹ ያገቱዋቸውን ተማሪዎች የማዳኑ ተግባር በጊዜ አለመድረሱን የኬንያ ፕሬዚደንታዊ ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ማኖዋ ኤሲፒሱ አስታውቀዋል።
« በጋሪሳ ስህተት ሰርተናል ወይ? አዎ፣ ሰርተናል። ከዚሁ ስህተታችን ግን ትምህርት አግኝተናል። ስህተት የማይሰራው ጥቃቱን በየት እና መቼ እንደሚጥል የሚያቅደው አሸባሪ ብቻ ነው። አንተ ጥቃቱን ለማስቆም ርምጃ መውሰድ ነው የምትችለው፣ እና ይህንኑ ርምጃ በማስተባበሩ ወቅት፣ ስለሁኔታው ትክክለኛ መረጃ ስለሌለህ፣ ጊዜ ማጥፋትህ አይቀርም። »
የኬንያ መንግሥት በሀገሩ ህብረተሰብ ውስጥ ካለፉት ዓመታት ወዲህ አክራሪነት እየተጠናከረ መምጣቱን ከተገነዘበ ወዲህ የፀጥታ ጥበቃ ርምጃውን ማጠናከሩን አስታውቋል፣ በሀገራቸው አክራሪነት እየተጠናከረ ለተገኘበት ሁኔታ ትኩረት የሰጡት ከፍተኛ የገዢው ፓርቲ ባለሥልን እና የኬንያ ምክር ቤት እንደራሴ አደን ዱዋሌ እንዳስረዱት፣ ከሁለት ዓመት በፊት አንዳንድ ሙሥሊም መንፈሳውያን በሞምባሳ ወደብ ከተማ የሚገኙ መስጊዶችን ፅንፈኛ የእሥልምና ርዕዮትን ለመስበኪያ ሳይጠቅሙባቸው እንዳልቀሩ ከተሰማ በኋላ የፀጥታ ኃይላት መስጊዶችን ዘግተዋል።
« አንዳንዶቹ ተቋማት በወጣት ሙሥሊሞች ዘንድ አክራሪነትን የሚያጠናክረው ርዕዮት መስፋፋት ላይ ሚና አላቸው። ይህ ፈታኝ ጉዳይ የደቀነውን ስጋት ለማጥፋትም በሀይማኖት አክራሪነት ተግባር የሚጠረጠሩትን ግለሰቦች እና ተቋማት በቅርብ እንከታተላለን። »
የኬንያ ባለሥልጣናት የሶማልያ ዓማፂ ቡድን አሸባብ በኬንያ የሽብር ጥቃትን ለማስቆም ጥረት በያዙበት በዚህ ወቅት በጋሪሳው ጥቃት ልጆቻቸው እና ዘመዶቻቸው የተገደሉባቸው ቤተሰቦች ወደመዲናዋ ናይሮቢ የቺሮሞ ማዕከል ከተወሰዱት የተማሪዎቹ አስከሬኖች መካከል የልጆቻቸውን በመለየቱ አዳጋች ተግባር መጠመዳቸውን የማዕከሉ ኃላፊ ዶክተር ሶቢ ሙሉንዲ ገልጸዋል።
« በአሁኑ ጊዜ 97 አስከሬኖችን ሰብስበናል። የአንዳንዶቹን ማንነት በርግጥ ለይቶ በማወቁ ተግባር ላይ ችግር አጋጥሞናል።»
በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ላይ የተጣለውን የአሸባሪዎች ጥቃት ተከትሎ የኬንያ መንግሥት በመላ ሀገሩ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጥበቃ ማጠናከሩን አስታውቋል። ይሁንና፣ የኬንያ ዩኒቨርሲቲዎች ህብረት ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቻርልስ ሙክዋዬ የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበት ሰሜን ም ሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢ አሁንም አደገኛ ቦታ የማያስተማምን ቦታ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
አርያም ተክሌ
ማንተጋፍቶት ስለሺ