የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩዎች እና የማክሮን የአፍሪቃ ጉብኝት
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 23 2014
በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም የወቅቱን የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታን ለመተካት አራት እጩዎች እየተፎካከሩ ነው።ኬንያውያንም በጎርጎሪያኑ በመጭው ነሀሴ 9 ቀን አዲሱን ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ እየተዘጋጁ ነው።የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽንም ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ራይላ ኦዲንጋን፣ ጆርጅ ዋጃኮያህ፣ ዊሊያም ሩቶ እና ዴቪድ ማዋሬ ዋሂጃ የተባሉ አራት ዕጩዎችን አፅድቋል። ይህም ከ1990ዎቹ ወዲህ በጣም ትንሹ የዕጩዎች ቁጥር ነው ተብሏል።
የወቅቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከፍተኛውን የስልጣን ዘመን ማለትም ሁለት ጊዜ አምስት አመት ስላገለገሉ በድጋሚ መወዳደር አይችሉም።
ራይላ ኦዲንጋ የአዚሚዮ ላ ኡሞጃ የተባለው ጥምረት መሪ ናቸው።ይህም የገዥው የጁቢሊ ፓርቲ እና የኦዲንጋ ኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ፓርቲን ያካትታል።
በኬንያ የተቃውሞ ፖለቲካ በሰፊው የሚታወቁት የቀድሞ የፓርላማ አባል ኦዲንጋ ከ2008 እስከ 2013 ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፤ ከ2018 ጀምሮ የአፍሪካ ህብረት የመሠረተ ልማት ተወካይ ናቸው።
የኦዲንጋ የምርጫ ቁልፍ ቃል ኪዳን የኬንያ የኢኮኖሚ ለውጥ ነው።ኦዲንጋ በቀድሞ ምስራቅ ጀርመን በ1960ዎቹ መገባደጃ የሜካኒካል ምህንድስና የተማሩ እና በኬንያ ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ይሰሩ በነበረበት ወቅት በሀይል አቅርቦት ዘርፍ የንግድ ፍላጎት ማሳደጋቸው ይነገራል።
በጎርጎሪያኑ 1982 የወቅቱን ፕሬዝዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይን ከስልጣን ለማውረድ አሲረዋል በሚልም በሀገር ክህደት ለዕስር ተዳርገው ነበር።
ኦዲንጋ የአሁኑን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጨምሮ እስካሁን አምስት ጊዜ ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።በኬንያ ኪሱሙ አውራጃ የተወለዱት ኦዲንጋ ከፖለቲከኛ ቤተሰብ የወጡ ናቸው። አባታቸው ጃራሞጊ ኦጊጋ ኦዲንጋ ከኬንያ ነፃነት በኋላ የመጀመሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ።በኬንያውያን ዘንድ «ባባ» በመባል የሚታወቁት ኦዲንጋ፤ በኬንያ የተቃውሞ ፖለቲካን ሲቆጣጠሩ ቆይተዋል። ከዚህ ቀደም በሳቸው እና በፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ደጋፊዎች መካከል በነበረ ከፍተኛ ፉክክር በሀገሪቱ ሞትን ያስከተለ ሁከትም ተቀስቅሶ ነበር።
ሌላው ዕጩ ተወዳዳሪው ዶክተር ዊልያም ሩቶ ግን ይህንን ላለመድገም ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።ለዚህም የመራጩን ህዝብ ድምፅ ለማክበር ይገባል ባይ ናቸው
«የምርጫውን ውጤት እንደምንቀበል በግልጽ ተናግረናል። ምክንያቱም ያለንበት ዲሞክራሲ የኬንያ ህዝብ እንዲመርጥ ነው።የኬንያ ህዝብ ደግሞ ብቁ ተወዳዳሪዎችን የመምረጥ ችሎታ ስላለው ያንን ማክበር አለብን።»
ዊሊያም ሩቶ በአሁኑ ጊዜ የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፤ፓርቲያቸውም የተባበሩት ዴሞክራቲክ ጥምረት ይባላል። የሩቶ ፓርቲ አማኒ ናሽናል ኮንግረስ እና የኬንያ ዲሞክራሲ መልሶ ማቋቋም የተባሉ ፓርቲዎችን ያካተተው ኩዋንዛ ኬንያ የተባለ ጥምረት አባልም ነው።
ከ2013 ጀምሮ የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ዊልያም ሩቶ ከዚህ ቀደምም የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር፣የግብርና ሚኒስትር እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
በኡሲን ጊሹ አውራጃ የተወለዱት ዊሊያም ሩቶ ፤በ2021 ገዢውን ጁብሊ ፓርቲን በመልቀቅ ነበር የአሁኑን ፓርቲያቸውን የተባበሩት ዴሞክራቲክ ጥምረት የተቀላቀሉት።
ሩቶ በጎርጎሪያኑ 2017 ዓ/ም ከወቅቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ተፎካካሪ ነበሩ።
ሩቶ ከተመረጡ በ12 ወራት ውስጥ በመንግስት መስሪያ ቤቶች በተመረጡ የስራ መደቦች የሁለት ሶስተኛ የስርዓተ-ፆታ ህግን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም በካቢኔ ውስጥ ወንዶች እና ሴቶች እኩል እንዲወከሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አዲስ የኢኮኖሚ መዋቅር ለማስተዋወቅ ቃል ገብተዋል። የምርጫ ማኒፌስቷቸውም የችግረኞችን አቅም ለማጎልበት ሥር ነቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረግን ይጠቁማል።የ55 አመቱ ዕጩ ተወዳዳሪ በቅርቡ ከDW ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የግብርናውን ዘርፍ ለመቀየር ማቀዳቸውንም ገልፀዋል።
«እርሻ በኬንያ ያለን በጣም አስፈላጊው ዘርፍ ነው። ከቡናችን እስከ አበባችን እስከ አትክልቶቻችን ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ነን። በቂ ምግብ የማናመርትበት ምንም ምክንያት የለም። አራት ሚሊዮን ኬንያውያን የሚራቡበትም ምንም ምክንያት የለም።»
ሌላው ዕጩ ተወዳዳሪ ዴቪድ ሙዋራ ዋሂጋ ያባላሉ።ከተመረጡ ሙስናን እና ጎሰኝነትን ለመዋጋት ቃል ገብተዋል።ዴቪድ ሙዋሬ ዋሂጋ የህግ ባለሙያ እና የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሲሆኑ፤ በ2006 አጋኖ የተባለ ፓርቲን መስርተዋል። ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ ሲሆኑ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው።በ2013 በተካሄደው እና ኡሁሩ ኬንያታ ባሸነፉበት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከውድድር ራሳቸውን አግልለዋል።
ፕሮፌሰር ጆርጅ ዋጃኮያህ የዘንድሮው የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሌላው ተወዳዳሪ ናቸው። ፕሮፌሰሩ ሩትስ የተባለው ፓርቲ መሪ ሲሆኑ፤ ኬኒያውያን ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች ትርፍ እንዲያገኙ ለኢንዱስትሪ እና ለመድኃኒትነት የሚውል አደንዛዥ ዕፅን ሕጋዊ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ገቢው የሀገሪቱን ዕዳ ለመቀነስ እና ስራ አጥነትን ለመፍታት ይረዳል ሲሉ ዋጃኮያህ ተናግረዋል።
ከሙስና ጋር በተያያዘ «የሞት ቅጣት ብቸኛው መንገድ ነው»ብለው ያምናሉ።
ዶክተር ዊሊያም ሩቶ ግን ሙስናን ለመዋጋት ነፃ የገንዘብ ተቋማት ያስፈልጋሉ ባይ ናቸው።
«ከፖለቲካው ወገን ወይም ክፍፍል ውስጥ ላለ እንዲሁም በሌላ በኩል ለቆመ ሁሉ ሙስና ሙስና መሆን አለበት። ማንኛውም አካል ገለልተኛ በሆኑ ተቋማት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አለበት። ለዛም ነው ህገ መንግስቱ ተቋማት ነፃ እንዲሆኑ የደነገገው። እና ይህ ነፃነት የገንዘብ ተቋማት ነፃ መሆንንም ያካትታል። የፈለከውን ያህል ነጻ መሆን ትችላለህ ነገር ግን ፍቃድ የሚሰጠው ከሌላ ቦታ ከሆነ ነፃነትህ ትርጉም የለሽ ይሆናል።»
በኬንያ ዘ ስታንዳርድ የተሰኘው ጋዜጣ በኦንላይን እትም ላይ ባወጣው ዘገባ በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙትፕሮፌሰር ዋጃኮያህ በምዕራብ ግዛት ማትጉ ውስጥ የተወለዱ እና በአሥራዎቹ ዕድሜአቸው ጎዳና ላይ ወጥተው የነበሩ ሰው ናቸው።
እኝህ ሰው ከነሀሴው ምርጫ በፊት በተደረገ የምርጫ ቅድመ ግምገማ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የተሻለ ተወዳጅነት እንዳላቸውም ታይቷል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአፍሪቃ ጉብኝት
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዚህ ሳምንት በካሜሩን፣ በቤኒን እና ጊኒ ቢሳው ጉብኝት አድርገዋል።ፓሪስ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ከቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማስተካከል ያለመ ነው ብላለች።
ያም ሆኖ ማክሮን ሰኞ ከስዓት ያውንዴ ሲደርሱ በአፍሪካ የሩስያ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እየናኘ ነበር። የሞስኮ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሰርጌ ላቭሮቭ ከግብፅ ወደ ኮንጎ ሪፐብሊክ ከዚያም ወደ ኡጋንዳ እና ኢትዮጵያ በመዟዟር ላይ ነበሩ።ሳምንቱ እየገፋ ሲሄድ የፈረንሳዩ መሪ ትኩረታቸው አፍሪካ በሩሲያ ባላት አቋም ላይ ወደቀ።እናም ቤኒን ሲደርሱ እንዲህ አሉ።
« ልንገራችሁ አፍሪቃ በቅኝ ግዛት ኢምፔሪያሊዝም ስትሰቃይ የነበረች አህጉር ነበረች ። ሩሲያ ከመጨረሻዎቹ ኃያላን ኢምፔሪያል ቅኝ ገዥ ሀገሮች ውስጥ አንዷ ነች።»
የፈረንሳዩ መሪ ሩሲያ ምግብን እንደ አንድ “የጦርነት መሳሪያ” ትጠቀማለች ሲሉ ከሰዋል። ማክሮን ሞስኮንም አጥብቀው ያላወገዙትን የአፍሪካ መሪዎች ተችተዋል።
«አውሮፓውያን የመረጡት በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ ጦርነት ውስጥ መሳተፍ ሳይሆን፤ እውቅና መስጠት እና ስም መስጠት ነው። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ግብዝነት አይቻለሁ።በተለይ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ።»
የካሜሩኑ ፕሬዚዳንት ፖል ቢያ፣ የቤኒኑ ፓትሪስ ታሎን እና የጊኒ ቢሳው ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ ስለ ዩክሬን ጦርነት ከፈረንሳይ አቻቸው ጋር በግል ተወያይተዋል።
ከጎርጎሪያኑ 2020 ጀምሮ ስልጣን ላይ የሚገኙት ኢምባሎ ከውይይት መልስ ሩሲያን ተቃውመው እንዲህ ብለዋል።
"« ጊኒ-ቢሳው፤ ምንም እንኳን ግንኙነት የሌላት ሀገር ብትሆንም፤ ይህንን በዩክሬን ላይ የሚደረገውን ጥቃት አውግዛለች።. እኔ እንደማስበው በ 21 ኛው ክፍለ ዘመን ጦርነትን መቀበል የለብንም።በተለይ በጎረቤት ሀገሮች መካከል።»
እሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ ሩሲያ ለአፍሪቃ መሪዎች የጋራ ጠላት ሆና አልተገኘችም። በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ ሩሲያን በግልጽ አውግዘዋል የተባሉ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ብቻ ናቸው።በዚህ የተነሳ የማክሮን ጉብኝት የአፍሪካን መሪዎች ከምዕራቡ ዓለም ጎን እንዲቆሙ ለማሳመን ያለመ ቢሆን ከንቱ ጥረት ይሆን ነበር።ይላሉ የፈረንሳይ ዓለም አቀፍ እና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ካሮላይን ሩሲ ።
በቻተም ሃውስ የአፍሪካ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ትግስት አማረ በበኩላቸው የማክሮን አስተያየቶች ፈረንሳይ በዩክሬን ጦርነት ባላት አቋም ላይ የአፍሪካን ድጋፍ ለማግኘት የተደረገ ሙከራ ነጸብራቅ ነው»ብለዋል።
እንደ ሀላፊዋ ማክሮን ከአህጉሪቱ ጋር ያነበረውን ግንኙነት ለማደስ የሚያደርጉት ጥረት የሚያስመሰግን ቢሆንም፣በአፍሪቃ እየታዩ ያሉ ያልተጠበቁ ለውጦች ግን ይህንን ለማሳካት በጣም ከባድ ያደርጉታል። ስለሆነም በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የረዥም ጊዜ የፖለቲካ አጋርነት መፍጠር ጊዜ የሚወስድ ጉዳይ መሆኑን ዳይሬክተሯ አስምረውበታል።
ማክሮን ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝዳንት በሆኑበት ወቅት ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ባደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝታቸው ወደ ማሊ ሄደዋል። ነገር ግን ከማክሮን የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን ወዲህ በአፍሪካ ብዙ ነገር ተለውጧል። የቀድሞዎቹ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች ከፈረንሳይ እየራቁ ነው። በቅርቡ በማሊ፣ ቻድ እና ቡርኪናፋሶ የተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ከፈረንሳይ ጋር ያለውን ግንኙነት ሲጎዳ ይታያል። ማሊ ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን ወታደራዊ ስምምነት አቋርጣለች።
በአንድ ወቅት የፈረንሳይ ተፅዕኖ የነበራቸው አንዳንድ ሀገሮች አሁን ለሩሲያ እና ለቻይና በግልጽ ይወግናሉ። ሩሲያ እና ቻይና በአፍሪካ መድረክ ላይ የሚያደርጉት ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ተፅእኖ ፉክክር እንደ ማክሮን ላለ መሪ አሁን የበለጠ ጠንካራ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
ማክሮን፤ በካሜሩን እና በጊኒ ቢሳው እንዲሁም በአህጉሪቱ ለሚገኙ ሌሎች ሀገራት የምግብ ምርትን ለመጨመር እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል። አክራሪ ጽንፈኞችን ለመዋጋት ለካሜሩን እና ለቤኒን ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠትም ቃል ገብተዋል።
ነገር ግን ማክሮን አንድ ርዕሰ ጉዳይ ከማንሳት ተቆጥበዋል።የካሜሩንን የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ወይም የአንግሎፎን ክልሎች የሚታየውን ቀውስ ።
የፈረንሳዩ መሪ ከተቃዋሚው ሞሪስ ካምቶ ጋር አልተገናኙም። የካምቶ የካሜሩን ዳግም መወለድ ንቅናቄ (MRC) ምክትል ፕሬዚዳንቶች አንዱ የሆኑት ኢማኑኤል ሲም እንደተናገሩት የማክሮን ጉብኝት ምንም ተስፋ አልነበረውም ።
አንድ ክልሉን ከሀገሪቱ ለመገንጠል የሚፈልግ ቡድን ተወካይ ለDW እንደተናገሩት ማክሮን ቢያ በእንግሊዘኛ ተናጋሪ ክልሎች የሚወሰደውን የኃይል እርምጃ እንዲያቆም ያሳስባል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር።
የአንግሊዠኛ ተናጋሪ ክልልን ከካሜሮን ለመገንጠል የሚታገሉት የአምባዞንያን መከላከያ ሰራዊት ምክትል አዛዥ ካፖ ዳንኤል ይህንኑ ያጠናክራሉ።
«በእኛ የነፃነት ንቅናቄ ውስጥ ካሉ አንጃዎች አንዱ የኢማኑኤል ማክሮንን ጉብኝት ለመቃወም መንገድ እንዲዘጋ ጥሪ ማቅረብ ነው።ነገር ግን ሌሎች ንቅናቄዎች ይህንን ክስተት በተስፋ ይመለከቱታል። ፖል ቢያ ለጦርነቱ የሰላማዊ መፍትሄን እንዲመርጥ ኢማኑኤል ማክሮን ግፊት ሊያደርግበት ይችላል በሚል።ይህም ካሜሩን አሁን ለያዘችው ከአምባዞኒያ ተገንጣዮች ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ጦርነትን የመጠቀም አቋም እንደ አማራጭ ይሆናል።»
ቢያ በበኩላቸው የማክሮሮንን ጉብኝት በተመለከተ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መንግስታቸው በሚያዝያ ወር ከሩሲያ ጋር የነበረውን ወታደራዊ ስምምነት ማደሱን አረጋግጠዋል።
በቤኒን ማክሮን እና ታሎን ስለ ቤኒን ደህንነት እና ከፓሪስ የጦር መሳሪያ ወይም ወታደራዊ ስልጠና ሊያገኙ ስለሚችሉበት ሁኔታ ተወያይተዋል።
ነገር ግን የፈረንሳዩ መሪ ሽብርተኝነትን መዋጋትን በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የመንግሥታቸው አካሄድ በሀገራቱ ጥያቄ ላይ ተመስርቶ ጣልቃ መግባትን አፅንዖት ሰጥተዋል።
የቻተም ሀውስ ዳይሬክተር ትግስት አማረ ለDW እንደተናገሩት ምዕራባውያኑ ኃያላን በራሳቸው ጥቅም እና በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽርክናዎችን እያሳደጉ ባሉት የአፍሪካ ሀገራት የሚደረግ ግንኙነት ሁልጊዜ ሊጣጣም እንደማይችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው ።
ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ