1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ዕንግዳ

ዓርብ፣ ግንቦት 16 2016

ከግብዣ፣ መሞጋገስ፣ መመሰጋገኑ ጀርባ ሁለቱን መሪዎች የሰበሰቡ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳዮች ጥብቅ ዉይይት ተደረጎባቸዋል።ዩናይትድ ስቴትስ ምሥራቅ አፍሪቃን ሥታማትር ኢትዮጵያን አልመረጠችም።120 ሚሊዮን ሕዝብ የተሸከመችዉ ጥንታዊት፣ ታሪካዊት የነፃነት ተምሳሌይቱ ሐገር በግጭት፣ሁከት ሥርዓተ አልበኝነት እየዳከረች ነዉ።

የኬንያዉ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ዋይት ሐዉስ ሲደርሱ የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አቀባበል ሲያደርጉላቸዉ
የኬንያዉ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ዋይት ሐዉስ ሲደርሱ የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አቀባበል ሲያደርጉላቸዉምስል Yuri Gripas/CNP/picture alliance

የኬንያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ዕንግዳ

This browser does not support the audio element.

 

የኬንያዉ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ፣ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬደንት ጆ ባይደን ባደረጉላቸዉ ግብዣ ዩናይትድ ስቴትስን በይፋ እየጎበኙ ነዉ።ሩቶ ካለፈዉ ማክሰኞ ጀምሮ የተለያዩ የዩናይትድ ስቴትስ ተቋማትን ጎብኝተዉ  ከባለቤታቸዉ ከራሔል ሩቶ ጋር ረቡዕ ዋይት ሐዉስ ደርሰዋል። አንድ የአፍሪቃ መሪ ዋይት ሐዉስን በይፋ ሲጎበኝ ከ15 ዓመታት ወዲሕ ሩቶ የመጀመሪያዉ ናቸዉ።

ያዉ አሜሪካኖች ለይፋ እንግዳቸዉ ሁሌም እንደሚያደርጉት ለሩቶ፣ ለባለቤታቸዉና ለባለሥልጣኖቻቸዉ የተደረገዉ አቀባበል፣ ቀይ ምንጣፍ የተዘረጋበት-ፈገግታ የፈሰሰበት፣ቀለል-ዘና ያለ ልዩ ነዉ። መስተንግዶዉ ለቀቅ፣ በርቸስቸስ-የራት ግብዣ የተካለበት፣ አድናቆት-ምስጋና ሙገሳ የታከለበት ነዉ።
                                
«ግንኙነታችን እዚሕ ደረጃ ላይ የደረሰዉ ባብዛኛዉ በዚሕ ጠረጴዛ ዙሪያ በተሰበሰቡት መሪዎች ጥረት ነዉ።መልዕክቴ ቀጥታና ግልፅ  ነዉ።አመሰግናለሁ፤ አመሰግናለሁ።በዚሁ ቀጥሉበት።» 
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ናቸዉ-ይሕን ባዩ ትናንት።ሩቶም ለአፀፋ አላመነቱም። እንዲያዉም ከኬንያም አልፈዉ ድፍን አፍሪቃን የወከሉ እስኪመስሉ ድረስ አስተናጋጃቸዉን አመስግነዋል።
                                        
«አመሰግናለሁ-ክቡር ፕሬዝደንት። ይሕን ይፋ ጉብኝት እንዳደርግ ሥለጋበዙኝ በመልዕክተኞቼና በራሴ ስም ልዩ ምሥጋና አቀርባለሁ።ከኬንያ ሕዝብንና ከክፍለ ዓለሚቱ ወድምና እሕቶቻችን የተላከዉን በጣም ሞቅ ያለ ሰላምታ ይዤ መጥቻለሁ።»

የኬንያ ዉለታ፣ የአሜሪካኖች ካሳ

 

ከግብዣ፣ መሞጋገስ፣ መመሰጋገኑ ጀርባ ሁለቱን መሪዎች የሰበሰቡ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳዮች ጥብቅ ዉይይት ተደረጎባቸዋል።ዩናይትድ ስቴትስ ምሥራቅ አፍሪቃን ሥታማትር ኢትዮጵያን አልመረጠችም።120 ሚሊዮን ሕዝብ የተሸከመችዉ ጥንታዊት፣ ታሪካዊት የነፃነት ተምሳሌይቱ ሐገር በግጭት፣ሁከት ሥርዓተ አልበኝነት እየዳከረች ነዉ።
ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን አንድም በጦርነት አለያም በጠንካራ መንግስት እጦት እየተንገጫገጩ ነዉ።ኤርትራ አንድ ሰዉ ለ33 ዓመት እየጋለባት ነዉ።ጅቡቲ ከአቅሟ በላይ ቢሆንም የአሜሪካን ጦር እያስተናገደች ነዉ።ማን ቀረ? ኬንያ።

ከግራ ወደ ቀኝ የኬንያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶና የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ምስል Susan Walsh/AP Photo/picture alliance

የሩቶ መንግስት ከሶማሊያ እስከ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት አዝምቷል።አሁን ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ግርጌ የምትገኘዉን የሐይቲን ሠላም ለማስከበር 1000 ፖሊስ ለማዝመት ተዘጋጅቷል።ኬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራዉ የዩክሬን መከላከያ የግንኙነት ቡድን የተባለዉ ሥብስብ አባል ናት።በቅርቡ የየመን ሁቲዎችን ለሚወጋዉ ለአሜሪካ መራሹ የባሕር ኃይልም ጠንካራ ድጋፍ ትሰጣለች።

ለዚሕ ታዛዥነቷ ፕሬዝደንቷ ዋይት ሐዉስ ቢጋበዙ አይበዛባቸዉም።የኬንያ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ሁለቱ መሪዎች ትናንት ባደረጉት ዉይይት አሜሪካ 15 ዘመናይ ሔሊኮብተሮችና ቁጥራቸዉ ያልተጠቀሰ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ለኬንያ ለማስታጠቅ ቃል ገብታለች።

የሲሊከን ሳቫና እና ሲሊከን ቫሊ ሽርክና

ባይደንና ሩቶ ትናንት ከዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ኩባንዮች ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ዉይይት አሜሪካኖቹ የኬንያን ዘመናይ ቴክኖሎጂ እንደሚረዱ ፍንጭ ሰጥተዋል።ያዉ የዲፕሎማሲያዊ ቃሉ ትብብር ነዉ-የሚባለዉ።ፕሬዝደንት ባይደን።
                                
«በኬንያና በዩንያትድ ስቴትስ መካከል አዲስ የቴክኖሎጂ ዘመንና የቴክኖሎጂ ትብብር ጀምረናል።ግንኙነቱ በኬንያ የሳይበር ደሕንነት፣የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መስክ የቴክኖሎጂ  ልዉዉጥና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን የሚያካትት ነዉ።»
የኬንያዉ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶም ሐገራቸዉ በተለይ በቴክኖሎጂዉ መስክ የአሜሪካኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት አልሸሸጉም።እንዲያዉም ሩቶ እንዳሉት ፍላጎቱ የዛሬ አይደለም።
                               
«የኬንያዉን የሲሊከን ሳቫና እና የዩኤሱን ሲሊከን ቫሊን ግንኙነት ለማስተሳሰር ሥንጥር ነበር። ይሕ ስብሰባ ደግሞ በዲጂታዊ ሥራዎች፣ የንግድ ልዉዉጥን ለሦስተኛ ወገን ማሳለፍን፣ ምርምርና ልማትን በሚመለከቱ ጉዳዮች በጋራ ማድረግ ያለብንን ለመምከር ነዉ።»

ከግራ ወደ ቀኝ የኬንያ ፕሬዝደንት የዊሊያም ሩቶ ባለቤት ራሔል ሩቶ፣ ቤርሚስ ኪንግና ፕሬዝደንት ሩቶ የማርቲን ሉተር ኪንግን ጁኒየርንና የባለቤታቸዉን የኮሬታ ስኮት ኪንግን ቀብር ሲጎበኙምስል John Bazemore/ASSOCIATED PRESS/picture alliance

የኬንያዉ ፕሬዝደንት ዩናይትድ ስቴትስ ሲጎበኙ ትናንት ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም ባንክ በኩል ለደሐ ሐገራት የ250 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምትሰጥ ዋይት ሐዉስ አስታዉቋል።ድጋፉ ደሐ ሐገራት አደጋ ወይም ምጣኔ ሐብታዊ ቀዉስ ሲያጋችማቸዉ የሚሰጥ ነዉ።ሐገራቸዉ በቅርቡ በጎርፍ ለተጥለቀለችባቸዉ ሩቶ ጥሩ አጋጣሚ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ ዘንድሮ መጋቢት 60 ዓመት ደፍነዋል።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW