መቀሌ ውስጥ የተፈጠረው ምንድነው ?
ሐሙስ፣ ኅዳር 25 2018
በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ጎልተው መታየታቸውን ተከትሎ ውጥረት ነግሶ መዋሉን የዓይን ምስክሮች ለዶቼ ቬለ ተናገሩ። ጠዋት የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት በመክበብ የተጀመረው የክልሉ ታጣቂ ቡድን እንቅስቃሴ ከሰዓት በኋላ ላይ ድምጸ ወያኔን ጨምሮ ዋና ዋና የክልሉ ተቋማትን ወደ መቆጣጠር መሸጋገሩን የአይን ምስክሮቹ ተናግረዋል።
ጠዋት ማልደው ወደ ስራ በማቅናት እያሉ የነብስ ወከፍ እና የቡድን የጦር መሳሪያ የታጠቁየትግራይ ኃይሎች የክልሉ ፕሬዚደንት ጽ/ቤት ከበው መመልከታቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ ብሎም ድምጻቸው እንዲቀየር የጠየቁን የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ተናግረዋል።
«ጠዋት ላይ ወደ ስራ ስሄድ ወደዛ አካባቢ የምስራበት አካባቢም እዚያ አካባቢ ነውና ቁጥራቸው በደንብ ባላየውም ከ70 በላይ ይሆናሉ ፤ የተለየ ነገር ነበር በርግጥ፤ ክላሽ ይዘዋል፤ ከክላሽ ውጭ ደግሞ የተለየ መሳሪያም ነበር፤ ዲሽቃ የሚሉት መሳሪያ ማለት ነው። እና በዚያ መንገድ እንዳናልፍ ነበር የተደረገው ። »
ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የከተማዋ ነዋሪውም ይህንኑ ያጠናከረ አስታየት ነው ያጋሩን።
«እዚያ ፕሬዚደንት ጽ/ቤት አካባቢ ያው በወታደሮች እንደተከበበ፣ እንደተያዘ ነው ፤ ምንድነው ምክንያቱየሚለው ነው እስካሁን የማይታወቀው እንጂ ያው እንደተያዘ ነው ያለው።»
የትግራይ ኃይሎች አባላት የሆኑ ወታደሮች ከሁለት ወራት ገደማ በፊት በመቀሌ ከተማ «የድሞዝ ጥያቄ» የሚል ለሶስት ቀናት የቆየ የጎዳና ላይ ተቃዉሞ ማድረጋቸው ይታወሳል። በወቅቱ የታጣቂዎቹ ጎዳና መውጣት መቀሌን ጨምሮ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ውጥረት አንግሶ የነበረ ሲሆን የታጣቂ ቡድኖቹ ተወካዮች ከክልሉ መስተዳድር ጋር ተነጋግረው ለጥያቄው አልባት በማበጀታቸው ታጣቂዎቹ «ይቅርታ ጠይቀው» ጉዳይ እልባት ማግኘቱ ተዘግቦ ነበር።
የዛሬውን ክስተት በአይናቸው መመልከታቸውን የነገሩን የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት ግን የዛሬው እንቅስቃሴ ለየት ያለ እና በጦር መሳሪያ የታገዘ ነው።
« የዛሬን ለየት የሚያደርገው ከነትጥቃቸው መሆኑ ፤ ሆን ተብሎ ዝም ተብሎ አካባቢውን በኃይል መያዝ ይህን ያህል አልነበረም እንጂ ጉዳዩስ የቆየ ነው።» ሌላው አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው እንደሚሉት
«ካሁን በፊትም ጥያቄው የነበራቸው ዜናው ላይ ተወርቶ ነበር እንደምታውቀው የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄየነበራቸው የሰራዊቱ አባላት ወደዚያ መጥተው ነበር። እንዲያውም ወደ መጀመሪያ ወደ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት መጥተው ነበር ። ከዚያ በኋላ ሌሎች መንገዶችን ሲዘጉ ነበር ። እንደዛሬው ትጥቅ ምናምም ግን አልነበራቸውም።»
ጄነራል ታደሰ ወረደ የሚመሩት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስደዳደር የሚገኝበትን ጽ/ቤት የከበቡ «የአርሚ 31» የተባለው ወታደራዊ ክፍል መሆኑን የነገሩን ነዋሪዎች እንደሚሉት ወታደሮቹ ረፋድ ላይ ከአካባቢው ከሄዱ በኋላ ወዲያው ተመልሰው ሌሎች መንግስታዊ እና የህወሓት ድርጅታዊ መገልገያ ተቋማትን በቁጥጥራቸው ስር እያዋሉ ነው። በዚህም የድምጸ ወያኔ የቴሌቪዥን ጣቢያ እና የህወሓት ዋና ጽ/ቤት በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነዋሪዎች ካዩት እና ከሰሙት ነግረውናል።
እንደ አስተያየት ሰጭዎቹ የታጣቂዎቹ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ፍላጎት እና ግብ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። የክልሉ ፕሬዚዳንት ያሉበት ተጨባጭ ሁኔታም በግልጽ አልታወቀም።
«እሱ ነው ትክክለኛ ምክንያታቸው ይሆን አላውቅም ፤ ጠጋ ብዬም አልጠየኩም ፤ እርግጠኛ ሆኜ መናገርም አልችም ። ነገር ግን እንደሰማሁት የሁለት ወር ደሞዝ አልተከፈለንም የሚል ጥያቄ እንደያዙ ነው። »
«እንግዲህ እሱ ሁለቴ ሶስቴ እየተደጋገመ ነው ያለው ፤ ማለት የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤትን ለሁለተኛ ጊዜ ነው መሰለኝ፤ በክልሉ በየቦታው ያው የቆየ ነው ። »
ድምጻቸውን እንዳንጠቀም ብሎም ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን እና ሁነቱን በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን የነገሩን የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው የወታደራዊ እንቅስቃሴው መዳረሻ ከወታደሮቹ የደሞዝ ጥያቄ በላይ ነው። እንደአስተያየት ሰጭው በጥቂት ወታደራዊ አዛዦች የሚመራው ይኸው ኃይል በክልሉ ፕሬዚደንት ታደሰ ወረደ ላይ ጫና በማሳደር «ለጊዜው የማይገልጹት ፍላጎት ለማሳካት ያለመ» ሳይሆንእንደማይቀርም ነው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ።
የሆነ ሆኖ ዛሬ መቀሌን ለከፍተኛ ውጥረት የዳረጋት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ህዝቡን ተስፋ ወደ ሚያስቆርጥ የስጋት ደረጃ እንደደረሰ ነው ነዋሪዎቹ የነገሩን።
«ነዋሪው መስጋት ራሱ አቁሟል መሰለኝ ፤ ሰልችቶታል መሰለን በመሪዎቹ ዙሪያ ያለው እሰጥአገባ አንዳንዴ ይሰለቻል መሰል ፤ ሰልችቶናል ፤ »
«እሱ በጣም ያሰጋል ፤ ምን መሰለህ በቃ ያሰጋል፤ ያው ድሮም መንግስት አልባ ነው ያለው ህዝቡ አሁን ደግሞ የባሰ እንደዚያ መንግስት አልባ እንሆናለን ፤ ወደ ከፋ ችግር እንወድቃለን የሚል አለ»
መቀሌ ከተማን ከማለዳው ጀምሮ ሲያብጥ በዋለው ውጥረት ከወታደራዊ እንቅስቃሴ በተጨማሪም የቦምብ ፍንዳታ እና የተኩስ ድምጾች መሰማታቸውን ዶቼ ቬለ ከነዋሪዎች አረጋግጧል። የከተማዋ የጸጥታ ባለስልጣናት እየሆነ ባለው ጉዳይ መልስ ይሰጡ ዘንድ ለከተማዋ የሰላም እና የጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ረዳኸኝ ፍሰሃ የእጅ ስልክ ላይ ብንደውልም ስልካቸው ባለመስራቱ አልተሳካልንም። የክልሉ ፕሬዘደንት በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር መዋል እና የፕሬዚደንቱን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለሆኑት ወ/ሮ ሸዊት አዲሱ መልስ እንዲሰጡን ስልክ ብንደውልላቸውም ስብሰባ ላይ ነን የሚል መልስ ሰጥተዉናል።
ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ