1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የክልል ልዩ ኃይሎች ላይ የመንግሥት ዉሳኔ ፣ የፓርቲዎች ተቃውሞ

ዓርብ፣ መጋቢት 29 2015

በኢትዮጵያ የፌዴሬሽኑ አባል የሆኑት ክልሎች የገነቧቸው «ልዩ ኃይል» የሚባሉ የፀጥታ ኃይላት አስፈላጊነት የሰሞኑ ዋነኛ የፖለቲካ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል።

Äthiopien | Selamawit Kassa | Staatsministerin für Kommunikationsdienste
ምስል S. Getu/DW

ወቅታዊው የክልል ልዩ ኃይሎች ጉዳይ እና የፓርቲዎች መግለጫ

This browser does not support the audio element.

 የፌዴራል መንግሥት የኢትዮጵያን «ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት» መወሰኑንና ይህንን ተከትሎ «የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማደራጀቱ ሥራ» መጀመሩን ትናንት እና ዛሬ ባወጣቸው መግለጫዎች አስታውቋል። ከመንግሥት መግለጫ አስቀድሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲዎች በተናጠል ባወጧቸው መግለጫዎች በመርህ ደረጃ የክልል ልዩ ኃይሎች አያስፈልጉም የሚል አቋም እንደነበራቸው ገልፀው ፣ በአሁኑ ወቅት ለማፍረስ እየተወሰደ ነው ያሉት እርምጃ ወቅቱን ያልጠበቀ እና ነባራዊ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ ነው ብለዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት «ሂደቱ የትኛውንም ልዩ ኃይል ትጥቅ ማስፈታት አይደለም»፣ በጉዳዩ ዙሪያም ውይይት ተደርጓል ብሏል። ሦስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል እንዳሉት በተለይ ሕወሓት በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሠረት ትጥቅ ሙሉ በሙሉ ባልፈታበት ሁኔታ እና አማራ ክልል ግልጽ የፀጥታ ሥጋት እንዳለበት በመጠቆም ይህንን ውሳኔ ማሳለፍ ላልተፈለገ ለፀጥታ መናጋት ችግር የሚያጋልጥ በመሆኑ ሰፊ ውይይት እንዲደረግና ውሳኔው እንዲቀለበስ ጠይቀዋል።
የመንግሥት ውሳኔ «ከመዘግየቱ በስተቀር ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት አይገባም» ያለው ኢዜማ «የክልል ልዩ ኃይሎች ይፍረሱ» የሚለው አቋሙ ያለፈው ምርጫ አንዱ መከራከሪያው እንደነበር አስታውሷል። ሆኖም ይህንን ውሳኔ «በጥድፊያ እና በድብቅ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር አደገኛ ውጤት እንደሚያመጣ» የፌደራል መንግሥት ሊገነዘበው ይገባል ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ተግባሩ ወቅቱን ያልጠበቀ መሆኑን ገልጿል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በበኩሉ በመርህ ደረጃ «የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ እንዳለበት እና ሀገራዊ በሆነ ተክለ ሰውነት በተላበሰ የመከላከያ ሠራዊት መጠናከር እንዳለበት» እንደሚያምን ገልጾ «አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ጉዳዩ ተቀባይነት የለውም» ብሏል።
የፌዴራል መንግሥት የኢትዮጵያን «ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት» መወሰኑንና ይህንን ተከትሎ «የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማደራጀቱ ሥራ» መጀመሩን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ትናንት በጽሑፍ ዛሬ ደግሞ ሚኒስትር ድኤታ ሰላማዊት ካሣ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ይፋ ተደርጓል።
የመንግሥትን ውሳኔ በመቃወም መግለጫ ያወጡት ፓርቲዎች ሕወሓት የታጠቃቸው ያሏቸውን መሣሪያዎች መፍታቱ በግልጽ አለመታወቁ ይህንን ተከትሎ በተለይ በአማራ ክልል ሥጋት መኖሩን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ምስል Yohannes G/Egziabher/DW

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በተከታታይ ባወጣቸው ሁለት መግለጫዎች «ከበቂ የሽግግር ጊዜ በኋላ የክልል ልዩ ኃይሎችን አደረጃጀት ማስተካከል እንደሚገባ የሚያምን ቢሆንም ጉዳዩን ከሕጋዊነት ፣ ከወቅታዊ እና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር ውሳኔው ወቅቱን ያልጠበቀ ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ እና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን እና የኅብረተሰብ ክፍሎችን ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት እና አደጋ የሚዳርግ ውሳኔ ነው" በማለት መንግሥት ውሳኔውን እንዲቀለብስ ጠይቋል።ኢዜማ የክልል ልዩ ኃይሎች ጉዳይ ሕገ - መንግሥታዊ ማሻሻያ ሲደረግ መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ገልጿል። መንግሥት በበኩሉ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው «ለዘላቂ የሀገር ጥቅምና ደኅንነት» መሆኑን ጠቅሶ ኃላፊነቱን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚወጣም አስታውቋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW