1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የክብር ሽኝት ለሜርክል 

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 5 2014

ሜርክል ለረዥም ዓመታት በመንግሥት ኃላፊነት ላይ በመቆየታቸውብዙ ጥቅማ ጥቅሞችንም ያገኛሉ። ጡረታቸው በወር 15 ሺህ ዩሮ ነው። እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ የግል ጠባቂ እና የመንግስት መኪና ከነሾፌሩ ይሰጣቸዋል። በጀርመን የ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አንድ ቢሮ ከአስተዳዳሪና ከሁለት አማካሪዎች እንዲሁም ከአንድ ጸሐፊ ጋር ይመደብላቸዋል።

BG Merkels letzter Tag
ምስል Markus Schreiber/AP Photo/picture alliance

የክብር ሽኝት ለሜርክል 

This browser does not support the audio element.

ጀርመንን ለ16 ዓመታት የመሩት አንጌላ ሜርክል ባለፈው ሳምንት ሥልጣናቸውን ለተተኪው መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ አስረክበዋል። ጀርመንን ለአራት የስልጣን ዘመናት የመሩት ሜርክል በጀርመን ታሪክ ለመራኄ መንግሥትነት የበቁ የመጀመሪያዋ ሴት ፖለቲከኛ ናቸው። ከፍተኛ ተሰሚነት ካላቸው የአውሮጳ መሪዎች አንዷ ሜርክል በጎርጎሮሳዊው ህዳር 2005 ዓም ነበር ከያኔው የጀርመን መራኄ መንግሥት ጌርሃርድ ሽሮደር ስልጣኑን የተረከቡት። «የተከበሩ መራኄ መንግሥት የሚቀር ነገር ቢኖር የተሳካ ስራ እንዲሆንልዎት በድጋሚ በመመኘት ነው። እነዚህን እያንዳንዳቸውን የስራ ባልደረቦች ከልብ እንዲቀበሉልኝ እጠይቃለሁ። ይገባቸዋል! በስልጣን ላይ የቆየሁባቸውን ዓመታት እንዳፈቅር አድርገውኛል ።በዚህ መንፈስ ለርስዎም ,ለነሱም በሙሉ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ። እርስዎን የስራ ባልደረቦቼን እና ቤተሰቦቻቸውን በጣም አመሰግናቸዋለሁ።መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ።»
ሽሮደር ያኔ መልካሙን ሁሉ በመመኘት ስልጣኑን ያስረከቧቸው ሜርክል  ሃሳብ አይግባዎ ሠራተኞቹንም ሆነ ጽህፈት ቤቱን ተንከባክቤ እይዛለሁ በማለት ለሽሮደር ቃል ገብተውላቸው ነበር ።
«በኔ በኩል ከልብ አመሰግናለሁ።ጽህፈት ቤቱንና እርስዎም በጀርመን መራኄ መንግሥት ያደረገጉትን ሁሉ ተንከባክቤ አቆያለሁ።»
ሲሉ ስልጣኑን ከሶሻል ዴሞክራቱ ሽሮደር የዛሬ 16 ዓመት የተረከቡት የሜርክል የመራኄ መንግሥትነት ስልጣን ባለፈው ሳምንት አብቅቷል። ሜርክል ራሳቸውን ከፖለቲካው ካገለሉም ቆይተዋል። አዲሱ የጀርመን ፓርላማ የመጀመሪያ ስብሰባውን ባደረገበት እለት እና አዲሱ መራኄ መንግሥትና ካቢኔያቸው ቃለ መሀላ በፈጸሙበት ወቅት ሜርክል በፓርላማው የእንግዶች መቀመጫ ስፍራ ላይ ሆነው ነበር ሁለቱንም ስነ ስርዓቶች ስርዓት የተከታተሉት።በሁለቱም ጊዜያት የፓርላማው አባላት ከመቀመጫቸው ተነስተው በረዥም ጭብጨባ ለሜርክል ያላቸውን አድናቆትና ክብር ገልጸውላቸዋል። የመስከረሙ ምርጫ አሸናፊ፣ ኦላፍ ሾልዝ ባለፈው ረቡዕ ሹመታቸው በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ በጀርመን መራኄ መንግሥትነት ቃለ መሀላ ከፈጸሙ በኋላ  ትልቁን የጀርመን ስልጣን  ከሜርክል ተረክበዋል ።ሜርክልም የዛሬ 16 ዓመት ለርሳቸው እንደተደረገው  መልካሙን ተመኝተው ፣መራኄ መንግሥትነት ምርጥ ስራ መሆኑን በመጠቆም  ለሾልዝ ስልጣኑን አስረከቡ
«ዛሬ ኦላፍ ሾልዝን በአካል ቀርቤ እንኳን ደስ ያለዎ ማለት አልቻልኩም ነበር። ምክንያቱም እኔ ከአሁን በኋላ የጀርመን ፓርላማ አባል አይደለሁም። በዚህ አጋጣሚ ይህንኑ ማለት እፈልጋለሁ። የተከበሩ መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ እንኳን ደስ አለዎ ከልምዴ እንደማውቀው ለዚህ ሃላፊነት መብቃት አስደሳች ነው። ስራው አስደሳች አጓጊና ጥንቃቄ የሚጠይቅ መሆኑን መገመት ይችላሉ። ስራውን ሙሉ በሙሉ በደስታ ካከናወኑት ለዚህ ሀገር ሃላፊነት ከሚወስዱበት ምርጥ ስራዎች አንዱ ነው።ለስርዎ በስራዎ ከልብ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ። ለሀገራችንም መልካም እድል እንዲገጥማት እመኛለሁ።»
ከአራት ጊዜው የሜርክል የመራኄ መንግሥትነት ዘመን በሁለቱ በሥራና ማህበራዊ ጉዳዮችና በገንዘብ ሚኒስትርነት ያገለገሉት አዲሱ መራኄ መንግሥት ሾልዝ በበኩላቸው ሜርክል ያሳለፉትን ውጣ ውረድ በማስታወስ ነበር ምስጋናቸውን ያቀረቡላቸው።
«ውድ ሜርክል ውድ መራኄ መንግሥት ባለፉት 16 ዓመታት ስላከናወኗቸው ስራዎች ላመሰግንዎት እወዳለሁ ።መራኄ መንግሥት የነበሩባቸው ዓመታት በጣም ጥሩ ጊዜ እንደነበሩ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል ብዬ አምናለሁ።።ብዙ ታላላቅ ስራዎችን ሰርተዋል።ብዙ ፈተናዎችን መሸከም ነበረብን። ከባድ ቀውሶችን መጋፈጥ ነበረብን ።አንዳንዶቹንም በተለያዩ ሃላፊነቶች በግልም እንደ ካቢኔዎ አባልነት አብረን ተጋፍጠናቸዋል።» 
ሾልዝና ሜርክል ከተለያዩ ፓርቲዎች ቢሆኑም የሚያመሳስላቸው ነገር እንዳለ ተችዎች ይናገራሉ ።ሁለቱም በሚያደርጓቸው ንግግሮች ስሜታዊነትን ባለማንጸባረቅና ፤ ከአነሳሽ ንግግሮችም በመቆጠብ ይመሰላሉ።  
ከዛሬ ሳምንት ረቡዕ አንስቶ የቀድሞ መራኄ መንግሥት ተብለው የሚጠሩት ሜርክል ጀርመንን የመሩበት ጊዜ አስተማሪያቸው ከሚባሉት የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲው የቀድሞ መራኄ መንግሥት ከሄልሙት ኮል የስልጣን ዘመን ጋር እኩል ነው። በምዕራብ ጀርመንዋ ከተማ ሀምቡርግ ተወልደው በህጻንነታቸው የፕሮቴስታንት ካህኑ አባታቸው ወደ ኮምኒስቷ ምሥራቅ ጀርመን ወስደዋቸው እዚያው ያደጉት ሜርክል ስልጣን በያዙበት በጎርጎሮሳዊው 2005 ጆርጅ ደብሊው ቡሽ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት፣ ዣክ ሺራክ በፓሪሱ የኤሊዜ ቤተ መንግሥት ፣ቶኒ ብሌር ደግሞ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ ። በፊዚክስ ትምህርት የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው የ67 ዓመቷ ሜርክል ከጊዜ ወደ ጊዜ ያዳበሩት በሀገራቸው በጀርመንም ሆነ በአውሮጳ ኅብረት ደረጃ ለችግሮች መፍትሄ የማግኘት ብልሀታቸው በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነታቸው ከፍ እያለ እንዲሄድ አድርጓል።ይህ ጥበባቸውም በጎርጎሮሳዊው 2008 የደረሰውን በዩሮ የሚገበያዩ ሀገራትን የገንዘብ ቀውስ፣ የ2015 ቱን የአውሮጳ የስደተኞች ቀውስ ለመፍታት እንዲሁም በጀርመን የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ታይቷል።
ረዥም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆዩት ሜርክል በርካታ ባለስልጣናትና የክብር እንግዶች በተገኙበት በወታደራዊ ስነስርዓት የክብር ሽኝት በተደረገላቸው ወቅት ባሰሙት ንግግር ከምንም በላይ ህዝቡ በርሳቸው ላይ ላለው እምነት ምስጋና አቅርበዋል።
« ዛሬ እዚህ ከናንተ ፊት ስቆም ከምንም በላይ ክብርና እርካታ ይሰማኛል። ለረዥም ጊዜ እንድለማመድበት በተፈቀደልኝ ጽህፈት ቤት ፊት ክብር ይሰማኛል ።እርካታው ደግሞ በተጣለብኝ እምነት ነው። እምነት በፖለቲካ ውስጥ ትልቅ እሴት መሆኑን ሁሌም የምገነዘበው ነገር ነው። ይህ ለማንም ግልጽ ነው። ለዚህም ከልብ አመሰግናችኋለሁ። »
ሜርክል ስልጣን ላይ የቆዩባቸው ዓመታትም ፈታኝ ቢሆንም ብቁ አድርገውኛል ብለዋል።
«በፌደራል መራኄ መንግስትነት የቆየሁባቸው 16 ዓመታት ብዙ ተግባራት የተከናወኑባቸውና ብዙውን ጊዜም በጣም ፈታኝ ዓመታት ነበሩ። በፖለቲካውም ሆነ በግሌ ፈትነውኛል። ሆኖም በሌላ በኩል እኔን ብቁ አድርገውኛል።»
ሜርክል በዚሁ የክብር ሽኝት ስነስርዓት ላይ እርሳቸውን ለተኩት ለኦላፍ ሾልዝ በአጠቃላይም ለአዲሱ መንግስት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
«አሁን ከፊታችን ለሚገኙት ፈተናዎች መፍትሄ መፈለግና መፃኤ እድላችንን መቅረጽ የቀጣዩ መንግሥት ስራ ነው።
ለዚህ ውድ ኦላፍ ሾልዝ በርስዎ የሚመራው የጀርመን መንግሥት መልካም እድልና ስኬት እንዲገጥመው መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ ። ቅር በተሰኘንባቸው ጉዳዮች ተስፋ ካልቆረጥን፣ቅናት ካላደረብን እና አሉታዊ አስተሳሰብ ከሌለለን መጻኤ እድላችንን በደንብ መቅረጻችንን መቀጠል እንችላለን ብዬ አምናለሁ።ከሦስት ዓመት በፊት እንዳልኩት ወደ ስራ ስትሄዱ ደስታን በልባችሁ ይዛችሁ ሂዱ። ቢያንስ እኔ ሁሌ ሳደርግ የነበረው  ይህንን ነው።ይህ በልባችን የሚኖር ደስታ በሁላችንም ላይ ወደፊትም እንዲሰፍን ምኞቴ ነው። ከልብ አመሰግናችኃለሁ።»

ምስል Sean Gallup/Getty Images
ምስል Michael Hanschke/dpa/picture alliance
ምስል Jens Krick/Flashpic/picture alliance

በአንድ ወቅት ታይምስ የተባለው የአሜሪካን መጽሔት ትልቅ ስልጣን ካላቸው የዓለማችን ሴቶች አንዷ ሲል የሰየማቸው ሜርክል ከመራኄ መንግሥትነት ከተሰናበቱ በኋላ በጡረታ ጊዜያቸው ምን ይሰራሉ የሚለው ብዙዎች የሚያነሱት ጥያቄ ነው።በቅርቡ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት መጀመሪያ ማረፍ ነው የሚፈልጉት። ለ16 ዓመታት በተዘጋጀላቸው አጀንዳ መሰረት ሲንቀሳቀሱ የቆዩት ሜርክል አሁን በርግጥ ምን እንደሚያስደስታቸው በርጋታ ማሰብ ይፈልጋሉ። ባለፉት የስልጣን ዓመታት ይህን ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንዳልነበሩ የገለጹት ሜርክል ምናልባት አሁን መጽህፍት ማገላበጥ ልጀምር እችላለሁ እተኛለሁ ምን እንደምሰራ ግን አላውቅም ብለዋል።
ሜርክል መራሂተ መንግስት ሳሉ በወር 25 ሺህ ዩሮ ነበር ደሞዛቸው። በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነታቸው 10 ሺህ ዩሮ ያገኙ ነበር። ሜርክል ስራቸውን ካቆሙ በኋላ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት ሙሉ ደሞዛቸው ይከፈላቸዋል። ለቀጣዮቹ 21 የሽግግር ወራት ደግሞ ከደሞዛቸው ግማሹ ይሰጣቸዋል። ሜርክል ለረዥም ዓመታት በመንግሥት ሃላፊነት ላይ በመቆየታቸውም ብዙ ጥቅማ ጥቅሞችንም ያገኛሉ። ጡረታቸው በወር 15 ሺህ ዩሮ መሆኑን እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ የግል ጠባቂ እና የመንግስት መኪና ከነሾፌሩ እንደሚሰጣቸው በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አንድ ቢሮ ከአስተዳዳሪና ከሁለት አማካሪዎች እንዲሁም ከአንድ ፀሐፊ ጋር እንደሚኖራቸው ዶቼቬለ የእንግሊዘኛው ክፍል በቅርቡ ባወጣው ጽሁፍ ተገልጿል። በዚህ መሰረት ሜርክል ሜርክል በጡረታ ዘመናቸው የገንዘብ ችግር አያሳስባቸውም ተብሏል። ታዲያ ሜርክል በጡረታ ዘመናቸው እንደ ሌሎቹ የቀደሙት የጀርመን መራኄ መንግስቶች የግል ስራ ይጀምራሉ ወይስ በሚሰጣቸው የክብር ቢሮ ይወሰናሉ የሚለው ለጊዜው አልታወቀም። ለጊዜው ግን በርሊን ይቆያሉ የሚል ግምት ነው ያለው። የኳንተም ኬሚስቱ ባለቤታቸው ዮአሂም ዛወር አሁንም ስራ የማቆም ሃሳብ ያላቸው አይመስልም የ72 ዓመቱ የበርሊኑ የሁምቦልት ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ዛወር የከፍተኛ ተመራማሪነት ውላቸውን ቢያንስ እስከ ሚቀጥለው ዓመት አራዝመዋል።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW