1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የክብር ዶክተር ዘነቡ ኃይሉ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 18 2015

ወይዘሮ ዘነቡ እንደሚሉት በአዕምሮ ጭንቀትና በተለያዩ የስነ ልቦና ችግሮች የሚሰቃዩት ሴት ስደተኞች ከብሪታኒያ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ሙያተኞች በሚያገኙት ትምሕርት፣ አስፈላጊ ምክርና ድጋፍ ውጤታማ ለመሆን በቅተዋል። ዘነቡ ለስደተኞችና እና ለተገን ጠያቂዎች ባደረጉት አስተዋጽኦ የሀደርስፊልድ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አበርክቶላቸዋል።

 Doctor Zenbu Hailu
ምስል፦ Privat

የክብር ዶክተር ዘነቡ ኃይሉ ኢትዮጵያዊቷ የስደተኞች ተንከባካቢ በሀደርስፊልድ

This browser does not support the audio element.

በተሰደዱባት በብሪታንያ ለስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ባደረጉት እገዛ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የበቁ ኢትዮጵያዊት ናቸው ወይዘሮ ዘነቡ ኃይሉ ። የወይዘሮ ዘነቡ ታሪክ ከተወለዱባትና ካደጉባት ከአላማጣ እስከ ብሪታንያዋ ትንሽ ከተማ ሀደርስፊልድ ይዘልቃል። አስተዋጽኦቸው የሚጀምረው በትውልድ አካባቢያቸው በአላማጣ በድጎማ መምህርትነትና በርዕሰ መምህርነት ከሰሩበት ጊዜ አንስቶ ነው። ከዚያም ለሰባት ዓመት በቆዩባት በሩስያ በላይብረሪና  ኢንፎርሜሽን ሳይንስ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ በጎርጎሮሳዊው 1991 የዛሬ 32 ዓመት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ተቋም እንዲሰሩ ተመደቡ በቤተ መጽህፍቱ የነበሩት መጻህፍት በሩስያኛ የተጻፉ  ስለነበሩ፣ሌሎች መጻህፍትን ለማሰባሰብና ከታዋቂ ግለሰቦች ፣በሀገር ውስጥ ካሉ ኤምባሲዎችና ቤተ መጻህፍት እንዲሁም በውጭ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች እገዛ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀምረው መጻህፍት ለማሰባሰብ በቁ ።ቤተ መጻህፍቱን ለማዘመን በነበራቸው እቅድ ደግሞ ዘንድሮ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ካበረከተላቸው የብሪታንያው ሀደርስፊልድ ዩኒቨርስቲ ጋር ተዋወቁ። የዛሬ 24 ዓመት ለልምድ ልውውጥ በሄዱበት በዚሁ ዮኒቨርስቲ የመስራት እድል አገኙ።ከዚሁ ጎን ለጎን በትርፍ ጊዜያቸው በሀደርስፊልድ ከተማ ውስጥ በሚገኘው በጎ ፈቃደኞች በመሰረቱት ሰሜን ኢንግላንድ ምዕራብ ዮሮክሸር በኪርክሊስ ወረዳ በተቋቋመው ከርክሊስ የሴቶች ማዕከል፣ ውስጥ በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውን ጨምሮ ከተለያየ የዓለም ክፍል የመጡ ስደተኞችንና ተገን ጠያቂዎችን በመርዳት ስራ ላይ ተሰማሩ። 
በማዕከሉ ለስደተኞች ድጋፍ የሚሰጡት ወይዘሮ ዘነቡ እንደሚሉት በአዕምሮ ጭንቀትና በተለያዩ የስነ ልቦና ችግሮች የሚሰቃዩት ሴት ስደተኞች ከብሔራዊ የጤና አገልግሎት በሚመጡ ሙያተኞች በሚያገኙት ትምሕርት፣ አስፈላጊ ምክርና ድጋፍ ውጤታማ ለመሆን በቅተዋል። የልምድ ልውውጡም እርሳቸው እንደሚሉት ከሌላው እንዲማሩ አግዟቸዋል።ሰጥተው እንዲቀበሉም አድርጓቸዋል። በድርጅቱ እገዛ የተለወጡ ብዙ ሴቶች እንዳሉ የተናገሩት ዘነቡ ከመካከላቸው አንዷ እኔ ነኝ ይላሉ። 
Women in Exile ፣ Women Together ፣ Women Together በ2002 ፣African Welcome በ2003 ከዚያም በኋላ Kraft ፣ Ethiopian Friends Together  የተባሉት እንቅስቃሴዎችን አቋቁመዋል። ወይዘሮ ዘነቡ እንዳሉት በ«Ethiopian Friends Together» እንቅስቃሴ በሊድስ ከተማ  ቤተ ክርስቲያን መክፈት ተችሏል። ከለንደን 321 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው በሀደርፊልድስ ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የራሳቸው ቤተክርስቲያን ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። የክብር ዶክተር ዘነቡ ላለፉት 21 ዓመታት በብሪታንያ የኢምግሬሽን ጉዳይ መስሪያ ቤትን ጨምሮ ለትርጉም በሚፈለጉባቸው የተለያዩ ተቋማት ስልጠና በወሰዱበት በአስተርጓሚነትም ይሰራሉ።  የክብር ዶክተር ዘነቡ በርሳቸውና በማዕከሉ  እገዛ መለወጥ ከቻሉት ብዙዎች መካከል ሁለት ሴት ስደተኞችን ያስታውሳሉ ።
ወይዘሮ ዘነቡ ለስደተኞችና እና ለተገን ጠያቂዎች ባደረጉት በነዚህን መሰል አስተዋጽኦዎች የሀደርስፊልድ ዩኒቨርስቲ ባለፈው አርብ በከፍተኛ ስነስርዓት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አበርክቶላቸዋል።ወይዘሮ ዘነቡ ዩኒቨርስቲው መመረጣቸውን በደብዳቤ ሲልክላቸው ሆነብለው የሚያሳስቱ ሰዎች የላኩላቸው መስሏቸው ጥለውት ነበር። በዚህም እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ቻሉ በስነስርዓቱ ላይ የተገኘው ገበያው ንጉሴ ያነጋገራቸው  ዶክተር ኬት ስሚዝ ፣ዘነቡ የክብር ዶክትሬት እንዲሰጣቸው የጠቆሟቸው የሀደርስፊልድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ይገኙበታል። ዘነቡ ክብሩ ይገባቸዋል ብለዋል። «ይሄን ለማየት እዚህ በመገኘቴ ታላቅ ክብር ይሰማናል። ለኔ ዘነቡ ሕይወታቸውን በሙሉ ስደተኞችን በመቀበል፣ ስደተኞች ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ በመስራትና በብሪታንያ የሚኖር ስደተኛ ይሰማዋል ስለሚባለው ጉዳይ እንዲገነዘቡ ተቀባዩን ለደኅንነታቸው ሲሉ ጦርነት ግድያና መሳደድን ሸሸተው እዚህ የመጡ ስደተኞች እንዲኖሩ የፈቀዱ ማኅበረሰብን በማገዝ ያሳለፉ ናቸው። »
የዩኒቨርስቲው ምክትል ሃላፊ ፕሮፌሰር ጄን ኦወንሊንችም ዘነቡ የመጀመሪያ ምርጫቸው እንደነበሩ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። አዶንያስ ደሳለኝ ዘነቡን ከ10 ዓመት በላይ ያውቃቸዋል። ለዚህ ክብር የበቁትም በስራቸው ነው ብሏል። የክብር ዶክተር ዘነቡ ፣እርጉዝ እያሉ በወጣትነቻው ባለቤታቸው በደርግ ጊዜ ተገድለውባቸዋል። በተመሳሳይ ጊዜና ሁኔታ ወንድማቸውም ሞተውባቸዋል። እርሳቸውና የ9 ወር ህጻን ልጃቸው እናታቸውም የታሰሩበትን ያን የሰቆቃ ጊዜ አልፈው ነው ለዚህ ክብር የበቁት። ወደፊትም መሰል ስራዎችን አጠናክሮ የመቀጠል እቅድ አላቸው።

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW