የኮሌራ በሽታ በጋምቤላ ኑዌር ዞን መከሰቱ ተረጋገጠ
ሐሙስ፣ የካቲት 13 2017
የኮሌራ በሽታ በጋምቤላ ኑዌር ዞን መከሰቱ ተረጋገጠ
ከሳምንት በፊት በጋምቤላ ክልል የተከሰተው በሽታ «ኮሌራ» መሆኑ በቤተ ሙከራ መረጋገጡን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። የታማሚዎች ቁጥር ወደ 200 አሻቅቧል። በሽታው ቀደም ሲል ባልታየባቸው አካባቢዎችም እየተስፋፋ እንደሆነ ነው የክልሉ ባለሥልጣናት የገለጡት። በኑዌር ዞን በሽታው ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ 14 ሰዎች በበሽታው መሞታቸው ታውቋል። ዓለምነው መኮንን
ከየካቲት መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ በጋምቤላ ክልል ኮሌራ መከሰቱን በተደረገው የናሙና ምርመራ ተረጋገጠ። በሽታው በክልሉ ኑዌር ዞን አኮቦ፣ መኮይ፣ ላሬና ዋንቱዋ ወረዳዎች ተከስቶ በርካታ ሰዎችን ማጥቃቱና የሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ የጤና ባለሙያዎች ገልጠዋል። በወቅቱ የበሽታውን ምንንነት ለማወቅ ናሙና ወደ ኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት መላኩም ተገልጦ ነበር። የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አቤል አሰፋ ትናንት ለዶይቼ ቬሌ ከዚህ በፊት የበሽታው ምንነት እስኪታወቅ አጣዳፊ ተቅማጥና ተውከት እየተባለ ሲጠራ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን በቤተሙከራ በመረጋገጡ የተከሰተውን በሽታ «ኮሌራ» ብለን እንጠራዋለን ነው ያሉት።
የዓለም የጤና ድርጅት 1.6 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው መድኃኒት አቅርቧል
ኃላፊው የበሽታው ስርጭት መጨምሩንና ትናንት በጋምቤላ ከተማ ሦስት የኮሌራ ታማሚዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል። በሽታውን መከላከል የሚያስችል 1.6 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው መድኃኒቶችም ከዓለም የጤና ድርጅት ወደ ክልሉ መላኩን ገልጠዋል።
እስከ ትናንት ምሽት ድረስ በጤና ባለሙያዎች የተረጋገጠ የኮሌራ በሽተኞች ቁጠር 192 ደርሷል ያሉት ኃላፊው፣ ቀደም ሲል በሽታው ታይቶባቸው ከነበሩት ወረዳዎች በተጨማሪ በጋምቤላ ከተማ የታመሙ ሰዎች ህክምና እየወሰዱ እንደሆነም አብራርተዋል።
የጋምቤላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሮን ጎኝ በኮሌራ የተጠቁ አምስት ሰዎች በሆስፒታላቸው ህክምና እየወሰዱ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።
ባለው የመሠረተ ልማት ችግር አኮቦ ወረዳ በቀላሉ መድረስ አልተቻለም
የኑዌር ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋትቤል ግርማል የበሽታው ስርጭትበተለያዩ ወረዳዎች እየተስፋፋ መሆኑን ጠቁመው አኮቦ ወረዳ የመጓጓዣምም ሆነ የስልክ ችግር በመኖሩ የተሟላ መረጃ ማግኘት እንደማይቻል ገልጠዋል። አኮቦ ወረዳ ባለው የስልክ ኔትወርክ ችግር ምክንያት መረጃ ለማሰባሰብ በጀልባ ጉዞ በመሆኑ ደርሶ ለመመለስ ሦስት ቀናት እንደሚወስድ ተናግረዋል።
እስዛሬ በበሽታው 200 ሰዎች ተይዘዋል
በሌሎቹ ወረዳዎች ግን የበሽታው ስርጭት እየሰፋ መሄዱንና እስከዛሬ ጠዋት ድረስ የታማሚዎቹ ቁጥር ባለፉት ሦስት ቀናት ከነበረው 136 ወደ 200 ከፍ ሲል፣ የሞቱት ቁጥር ደግሞ ዛሬ ወደ 14 አድጓል ነው ያሉት። በሽታው በክልሉ በአኮቦ፣ በላሬ፣ በመኮይ፣ በዋንቱዋ፣ በጂካዎ ወረዳዎችና በጋምቤላ ከተማ አስተዳደር መሰራጨቱን አስረድተዋል።
በጂካዎ ወረዳ አዳዲስ የኮሌራ በሽተኞች ተመዝግበዋል
የጅካዎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንድሪው ቱት በወረዳው በሽታው ከትናንት ጀምሮ መታየቱንና የአንድ ታማሚ ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል። በአሁኑ ሰዓት በየወረዳው የሚገኙ ባለሙያዎች በሆስፒታሎችና በጤና ጣቢያዎች በመገኘት ለታማሚዎቹ የህክምና እርዳታ እያደረጉ መሆናቸውንም የጤና ኃላፊዎቹ ተናግረዋል። በተጨማሪም ኅብረተሰቡ ያልበሰሉና ያልተከደኑ ምግቦችን ከመመግብ እንዲቆጠብ፣ ውሀን አፍልቶ እንዲጠጣ ባለሙያዎቹ መክረዋል።
ኅብረተሰቡ የግልና የጋራ ንጽሕናውን እንዲጠብቅ
በሽታውን ለመቆጣጠር መንግሥት ከሚያደርገው ርብረብ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ የግልና የጋራ ንጽሕናውን በመጠበቅ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ የጤና ባለሙያዎች ከአደራ ጋር አሳስበዋል።
ከደቡብ ሱዳን እንደተዛመተ የሚገመተው ይህ የኮሌራ በሽታ ከየካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በጋምቤላ ክልል አኮቦ ወረዳ መከሰቱን የጋምቤላ ክልል የጤና ባለሥልጣናት አመልክተዋል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ