1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወረርሽኙ ቢያንስ 450 ሰዎች ሞተዋል።

ዓርብ፣ መጋቢት 29 2009

ድርቅ በተከሰተባቸዉ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች በተለይም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልና በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ከንጹህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን መረጃወች ያመለክታሉ።

Dossierbild Horn von Afrika Ostafrika Somalia Hungersnot Hungerskatastrophe Bild 1
ምስል AP

Cholera outbreak in Eth.Somali Region and Somalia - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዝርዝር መረጃ ለማግኜት ያደረግነዉ ጥረት ባይሳካም በሶማሊያ ወረርሽኙ የ 450 ሰወችን ህይወት መቅጠፉን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት በምህጻሩ ዩኒሴፍ ገልጿል።
የሶማሌ ክልል በኢትዮጵያ በድርቅ ከተጠቁ አካባቢወች አንዱ ነዉ። በክልሉ  2 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊወች መሆናቸዉ ሲገለፅ ቆይቷል።በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ባወጣዉ ዘገባ ደግሞ በክልሉ በድርቅ ከተጎዱ 43 ወረዳወች ዉስጥ በአብዛኛወቹ ላይ የኮሌራ ወረርሽኝ መቀስቀሱ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ አድርጎታል። ወረርሽኙ ለክልሉ ቀረቤታ ባላቸዉ  ሶማሊያና ሶማሌ ላንድን በመሳሰሉ ጎረቤት ሀገሮችም ቀድሞ መከሰቱ ተገልጿል። በቅርቡ  በሶማሌ ላንድ ሆደሌ በተባለ ስፍራ  በወረርሽኙ 9 ሰዎች  መሞታቸዉንና በርካቶች በጤና መታመማቸዉን የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚንስትር መግለጹን ከሀገሪቱ የሚወጡ ዘገባወች አመልክተዋል።ይህ ተላላፊ በሽታ ታዲያ ወደጎረቤት ኢትዮጵያ ይሸጋገራል የሚል ስጋት አይሎ ቆይቶ ነበር። ይሁን እንጅ በክልሉ በተከሰተዉ ድርቅ ሳቢያ እያጋጠመ ያለዉ የንጹህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት ችግር ለወረርሽኙ መቀስቀስ አይነተኛ ምክንያት መሆኑም ተመልክቷል። ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በርካታ የጤና ባለሙያወች ወደ ክልሉ እየገቡ መሆኑም እየተነገረ ነዉ። በምስራቅ አፍሪካ ድርቅ ከተከሰተባቸዉ ሀገሮች አንዷ በሆነችዉ ሶማሊያም የኮሌራ ወረርሽኝ ክፉኛ በመዛመት ላይ እንደሚገኝ ዘገባወች ያመለክታሉ። በሶማሊያ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት በምህጻሩ ዩ ኒ ሴ ፍ  እንደገለጸዉ በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል 450 ሰወች በበሽታዉ ህይወታቸዉ አልፏል። ወደ 25 ሺህ የሚጠጉ ሰወች  ደግሞ ለህይወት አስጊ በሚባል ሁኔታ የሚገኙ ሲሆን፤ በየቀኑ አዳዲስ 300 ሰወች በወረርሽኙ ይያዛሉ ብሏል።  በሶማሊያ የድርጅቱ ሰራተኛ ፀደይ ግርማ የሁኔታዉን አስቸጋሪነት እንዲህ ትገልጻለች።
«ሀገሪቱ ከባድ የኮሌራ ወረርሽኝ እያጋጠማት ነዉ።በተለይ ደግሞ በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል የበረታ ነዉ ።በ2015 ከተከሰተዉ የኮሌራ ወረርሽኝi የአሁኑ 3 እጥፍ ይሆናል።በዚህ 3 ወር የተከሰተዉ  ብቻ ባለፈዉ አንድ አመት ከታየዉ ይበልጣል።»

ምስል AP


በሶማሊያ ከድርቁ አደጋ ጋር ተደማምሮ የኮሌራ ወረርሽኝ የፈጠረዉን ችግር ለመቆጣጠር በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸዉም ተገልጿል። የገንዘብ ድጋፍ ማጣት ከችግሮቹ አንዱ  መሆኑን  ከባይደዋ የጤናጥበቃ ሚንስትር ሰራተኛ የሆኑት አይዛክ መሀመድ ተናግረዋል። የባይደዋዉ ነዋሪ አይዛክ መሀመድ  ችግሩ የገንዘብ ነዉ ይበሉ እንጅ ፤የጸጥታና የመንገድ ችግርም እርዳታዉን ለማድረስ ማነቆ ነዉ ተብሏል። ከሶማሊያ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ስቲቨን ላዉረር ይናገራሉ ።
«የኛ ትልቁ ተግዳሮት የተደራሽነት ችግር ነዉ።በአንድ በኩል የፀጥታ ችግር በሌላ በኩል ደግሞ የመንገድ ችግር አቅርቦቱ ዉሱን  አድርጎታል።» 
ድርቅ በተከሰተባቸዉ የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት ኮሌራ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ በሽታዉን ለመከላከል  ብቸኛዉ መፍትሄ ክትባት መሆኑን አለም አቀፉ የጤና ድርጅት አመልክቷል። ካለፈዉ መጋቢት አጋማሽ  ጀምሮ በእንክብል መልክ የተዘጋጁ  9 መቶ ሽህ ክትባቶች መለገሱንም ድርጅቱ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ስለ ወረርሽኑ ዝርዝር መረጃ ለማግኜት  ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም።

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW