1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሪደር ልማቱ ውጤትና ተግዳሮቱ

ረቡዕ፣ ሰኔ 5 2016

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሦስት ወራት ገደማ በፊት የተጀመረው የኮሪደር ልማት በብዛት ወደ መጠናቀቅ ምዕራፍ መጠጋቱ እየተነገረ ነው። በከተማዋ በስፋት እየተሠራ በሚገኘው በዚሁ የኮሪደር ልማት በተሰኘው ጎዳናዎችን የማስዋብ ጥረት በከተማዋ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እና አልፎ አልፎ ደግሞ የጎርፍ መትለቅለቅም ተከስቷል።

አዲስ አበባ
አዲስ አበባምስል Seyoum Getu/DW

የኮሪደር ልማቱ ውጤትና ተግዳሮቱ

This browser does not support the audio element.

 

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሦስት ወራት ገደማ በፊት የተጀመረው የኮሪደር ልማት በብዛት ወደ መጠናቀቅ ምዕራፍ መጠጋቱ እየተነገረ ነው። በከተማዋ በስፋት እየተሠራ በሚገኘው በዚሁ የኮሪደር ልማት በተሰኘው ጎዳናዎችን የማስዋብ ጥረት በከተማዋ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እና አልፎ አልፎ ደግሞ የጎርፍ መትለቅለቅም ተከስቷል። ይሁንና ልማቱ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች ኅብረተሰቡ የሚሰጠው አስተያየት አዎንታዊነቱ ያመዝናል። 

አቶ ጸጋዬ መኮንን ይባላሉ። የ76 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ናቸው። አዲስ አበባ ውስጥ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነው ተወልደው ያደጉት። ዕድሜያቸውን በሙሉ በዚችው ከተማ ማሳለፋቸውን የሚገልጹት አዛውንቱ በከተማዋ ክፉ ደጉን ማየታቸውንም ይገልጻሉ። ዛሬ አራት ኪሎ ከቅድስተ ማሪያም ቤተክርስቲያን መዞሪያ ወደ ፒያሳ የተሠራውን ሲቃኙ ተመልክተን ያነጋገርናቸው አቶ ጸጋዬ በዚህ አከባቢ ተለውጧል የተባለውን የከተማዋን ገጽታ ለመመልከት በእግራቸው ተጉዘው ወደስፍራው መምጣታቸውን ያስረዳሉ። «በዚህ ቀጭን መንገድ እና ደቃቃ ቤቶች ነበሩ» ያሉት አዛውንቱ በጎበኟቸው አካባቢዎች ተስፋ ሰጪ ያሏቸውን ለውጦች መመልከታቸውን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ኮረደር ልማት ምስል Seyoum Getu/DW

የኮሪደር ልማቱ የሰጠው ተስፋ

በዘሁ አቅራቢያ ከራስ መኮንን ድልድይ መሻገሪያ አካባቢ ተቀምጠው ሙሉ በሙሉ ገጽታው እየተቀየረ ያለውን ፒያሳን እየተመለከቱ የሚገኙት ሁለት ወጣቶችም ስለተለወጠው የአካባቢው ገጽታ ያላቸው አዎንታዊ አስተያየት ይጎላል። «ያየነው ለውጥ ደስ ይላል። ከአራት ኪሎ እስከ ፒያሳ ያረጁ የድሮ ቤቶች ፈርሰው ፎቆች እየተሠሩ ነው። ከእይታ አንጻርም ደስ የሚል ነገር ተመልክተናል። ከዚያም ባሻገር ይህ አካባቢ በጎርፍ የሚቸገር ማኅበረሰብ የሚገኝበት ነው። ምንም እንኳ እነዚያ ሰዎች ወዴት እንደተወሰዱ መረጃ ባይኖረንም የምናየው ነግር ደስ ይላል» በማለት አንደኛው ወጣት ሃሳቡን አጋርቷል።

ሌላኛውም ወጣት አስተያየቱን አከለ። «ከአራት ኪሎ በዚህ በራስ መኮንን ወደ ፒያሳ የሚወስደው መንገድ ከዚህ በፊት ጠበብ ያለ በመሆኑ በተለይም ጠዋት ለትራንስፖርት አመቺ ያልሆነና መጨናነቅ የሚስተዋልበት አካባቢ ነበር። ከዚያም ባሻገር እንዲህ ለእይታ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ሰው ቁጭ ብሎ የሚያስብበትና የሚያነብበትም ሁኔታ ስለሚፈጥር ጥሩ ነው» ብሏል። ወጣቱ አከለ «በተለይም በወንዝ ዳር ፕሮጀክቱ አካባቢ የነበሩ ሰዎች ክረምት በመጣ ቁጥር በጎርፍ ይሰቃዩ ነበር» በማለት አካባቢው ከሰው ንብረት ነጥቀው የሚሸሹ ሌቦች የሚበዙበትም እንደነበር አስታውሶ አሁን በሚታየው መልክ ተገላልጦ መሠራቱን አሞካሽቷል።

እኛም ቦታው ላይ ደርሰን የተመለከትነው ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ ለኮሪደር ልማት ተዘግቶ የነበረው መንገድ ገጽታው ተቀይሮ ለትራፊት ክፍት ሆኗል። በርካታ የከተማዋ ነዋሪም የተሠሩትን የመንገድ ዳር መናፈሻዎች ሞልተው ይስተዋላል። አሁንም ያልተጠናቀቁ የኮሪደር ማልማት ሥራውን በመሥራት የሚባትሉ ወጣቶችም በስፋት ይታያሉ።

ዶቼ ቬለ ካነጋገራቸው ወገኖች የኮሪደር ልማቱ የቀድሞውን ገጽታ መለወጡን በአዎንታዊነት የገለጹት ጥቂት አይደሉም። ምስል Seyoum Getu/DW

የልማቱ ሂደት ውስጥ የተስተዋሉ ተግዳሮቶች

ከዚህ ባሻገር ግን ላለፉት ሦስት ወራት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የሚሠራው የኮሪደር ልማት የፈጠረው ጫና በሚመስል መልኩ በርካታ የከተማዋ አካባቢዎች ላይ መጨናነቅ ተፈጥሮ ብዙ ሕዝብ በትራንስፖርት እጦትም ሲቸገር ተስተውሏል። መንግሥት በሦስት ወራት ውስጥ አጠናቅቃለሁ ብሎ በትኩረት ሢሠራቸው ከነበረው የዚህ የኮሪደር ልማቱ ሥራ ውጪ ያሉ መንገዶችም የተዘነጉ በሚመስል መልኩ የትራፊክ ፍሰቶችን ሲያስተጓጉሉ ታይተዋል። ዝናብ በጣለ ቁጥር ማፋሰሻቸው የተዘጋ በርካታ የመዲናዋ መንገዶችም የማጓጓዣ እክሎችን ሲፈጥሩ ነው የሚስተዋለው።

አራት ኪሎና ፒያሳ አካባቢ የተጠናቀቁትን በጎ ሥራዎች አወድሰው አስተያየታቸውን የሰጡን የከተማዋ ነዋሪዎችም ከዚህም ረገድ ትዝብታቸውን አጋርተውናል። «በጎርፍ  ችግር የሚደርስባቸው ቅድሚያ ትኩረት ሊያገኙ የሚገባቸው የከተማዋ አካባቢዎች አሉ» የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የተጀመሩ በጎ ሥራዎች ወደዚያ ቢሰፉ መልካም መሆኑን አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት በከፊል ምስል Seyoum Getu/DW

የጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አህመድ አስተያየት

ከሰሞኑ በኮሪደር ልማቱ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ የተሠሩትን ሥራዎች ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ሆነው የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሥራው ሂደት ላጋጠሙት ክፍተቶች የከተማዋን ነዋሪዎች ይቅርታ ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የተጀመረውን ከተማን የማዘመንና ሳቢ የማድረጉን ሥራ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍል ከተሞችም እንደሚሰፉ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት በአጽንኦት ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ አምብርት ጥንታዊት መንደር የፒያሳ መፍረስን ጨምሮ በከተማዋ በርካታ ቤቶችን በማፍረስ ከሦስት ወራት ገደማ በፊት የተጀመረው የኮሪደር ልማት በርካታ አወዛጋቢ አስተያየቶችን ማሰማቱ አይዘነጋም።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW