1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሸገር ከተማ የኮሪደር ልማትና የነዋሪዎች አቤቱታ

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ ግንቦት 6 2017

በሸገር ከተማ በሁሉም አቅጣጫ ባሉ ክፍለከተሞቹ ለኮሪደር ልማት በሚል የፈረሱ ቤቶች አብዛኞቹ ህገወጥ ናቸው ሲል ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ እንዳለው ሕጋዊ ካርታ ለሌላቸው የሚከፈል ካሳም ሆነ የሚሰጥ ምትክ ቦታ የለም። ነዋሪዎች በከተማይቱ ዋና መንገዶች ዳርቻ የነበሩ ቤቶች በመደዳው ቢፈርሱም እስካሁን የተሰራ ልማት የለም።

Äthiopien Straßenrandabriss
ምስል፦ Seyoum Getu Hailu/DW

የሸገር ከተማ የኮሪደር ልማትና የነዋሪዎች አቤቱታ

This browser does not support the audio element.

“ያፈረስናቸው አስፓልትን ተከትሎ ያሉ አብዛኛው ቤቶች ህገወጥ ናቸው” የሸገር ከንቲባ

በሸገር ከተማ አስተዳደር በሁሉም አቅጣጫ ባሉ ክፍለከተሞቹ “ለኮሪደር ልማት” በሚል የፈረሱ ቤቶች አብዛኞቹ  ህገወጥ ናቸው ሲል ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡ የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ተሾመ አዱኛ ለዶይቼ ቬለ እንደነገሩት ከተማ አስተዳደሩ ሕጋዊ ካርታ ለሌላቸው የሚከፈል ካሳም ሆነ የሚሰጥ ምትክ ቦታ የለም፡፡በከተማው ህጋዊም ሆነው ቤት የፈረሰባቸው ግን፣ የተሰጣቸው ካሳም ሆነ ምትክ አለመኖሩን በምሬት እየገለጹ ነው፡፡በከተማ ፈርሰው የቆዩ ቤቶች ላይ ይሰራል የየተባለው ልማት ከመዘግየት ጋር ተያይዞም የቴሌ እና መብራት መሰረተልማት ስራውን ቶሎ መጀመር ላይ ፍግር መፍጠራቸው ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን በጊዜያዊነት እንዲያቆም አምነስቲ ጠየቀ

በሸገር ከተማ አስተዳደር የቡራዩ ክፍለ-ከተማ ሳንሱዚ አከባቢ አስተያየት ሰጪ የ73 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ከስምንት ወራት በፊት ከመኖሪያ ቤታቸው አስታከው የሰሩት የንግድ ሱቆች በሙሉ የመንገድ ዳር ልማት በተባለው የከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክት እስኪፈርስባቸው ያላቸው ብቸኛ መተዳደሪያቸውም ነበር፡፡ እስካሁን ከፈረሳው በቀረው አነስተኛ ቦታ መጠለላቸውንም በመግለጽ ለፈረሰባቸው የገቢ ምንጭ በነበሩ ሱቆቻቸውም ሆነ መኖሪያቸው ምትክ ቦታም ሆነ ካሳ ባለመከፈሉ ችግር ላይ መውደቃቸውን አመልክተዋል፡፡ “ሱቄ ቤቴ ከፈረሰ አሁን ስምንተኛ ወር ላይ በመሆኑ ችግር ላይ ነን፡፡ በቦታው ወይ ቤት አልተሰራበት ወይ ግምት ካሳ አልተሰጠንም፡፡ የኔ ቦታ ሙሉ ቤት እንዲነሳ ቢነገረኝም ሌላ ምትክ እስኪሰጣችሁ በሚል የተቀረች ቦታ ላይ ተጠልየ ነው ያለሁት፡፡ አሁን መተዳደሪያ ገቢዬ ተቋርጧል፡፡ በዚያ ላይ በሽተኛ ነኝ ሰርቼ መብላት አልችልም፡፡ እስካሁን የተመለከተን የለም ለማን አቤት እንላለን” ሲሉ ነው ምሬታቸውን የገለጹት፡፡

ፈርሶ በቆየው የሸገር ከተማ መንገድ ዳር ቤቶች የነዋሪዎች ቅሬታ

እሳቸውን ጨምሮ አስተያየታቸውን የሚሰጡ የከተማው ነዋሪዎች በያቅጣጫው ባለው ሰፊ በሆነው ሸገር ከተማ በዋና መንገዶች ዳርቻ የነበሩ ቤቶች በመደዳው ቢፈርሱም ባንድ በኩል እስካሁን ይሰራበታል የተባለው ልማትም አልተሰራበትም፡፡ በሌላ በኩል ቤቶቹ ከ8 ወራት ግድም በፊት በመፍረሳቸው ነግደው ሲያተርፉ የነበሩ እንዳልተጠቀሙባቸው ያነሳሉ፡፡

የሸገር ከተማ መንገድምስል፦ Seyoum Getu Hailu/DW


በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶ/ር ተሾመ አዱኛ ግን ከተማ አስተዳደሩ ሁሉንም ነገር በእቅዱ መሰረት እያስከደው መሆኑን በማንሳት ለመልሶ ልማቱ ተግዳሮት ሆኗል ያሉትን ግን ጠቅሰዋል፡፡ “የኮሪደር ልማቱን በተመለከተ በኛ በኩል ወደኋላ ቀረ የምንለው ነገር የለም፡፡ ሁሉንም በእቅዳችን መሰረት እያስከድነው ነው” ያሉት ዶ/ር ተሾመ የድንበር ማስከበር ስራዎች ከተሰሩ በኋላ ወደ ስራ መገባቱን ያነሳሉ፡፡ በለገጣፎ፣ ገላን እና አሸዋሜዳ በኩል የመንገድ ስራዎቹ መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡ የመብራት እና ቴሌኮም መሰረተ ልማት መልሶ ግንባታ ሌላኛው ወደ ልማት መግባቱን ያዘገየው ተግዳሮት መሆኑንም አንስተው አሁን ግን ችግሮቹ እየተቀረፉ ወደ ስራ ተግብቷልም ሲሉ ሞግተዋል፡፡


ከካሳ ክፍያ እና ምትክ ይዞታ ጋር በተያያዘም ሰፊ አቤቱታዎች በሚያሱበት ሸገር ከተማ ቤቶቹ ከፈረሱበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ስምንት ወራት የተሰጣቸው ምላሽ አመርቂ አለመሆኑን ነዋሪዎች ያነሳሉ፡፡ “መጀመሪያ ላይ ወደ ሸገር ሄደን አቤቱታ አቅርበን ነበር፡፡ ከንቲባውን ባናገኛቸውም ምክትላቸውን አነጋግረን ያለምትክ እንዴት ይፈርስባችኋል እናጣራለን ቢሉም ከዚያ ወዲህ የተመለከተን የለም” በማለት ጥያቄያቸው በእንጥልጥል መቅረቱን አንስተዋል። 

የሸገር ከተማ መንገድምስል፦ Seyoum Getu Hailu/DW

በሸገር ከተማ የመንገድ ዳር ቤቶች መፍረስ
በዚህ ላይም ዶይቼ ቬለ ጥያቄ ያቀረበላቸው የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶ/ር ተሸመ አዱኛ፤ “ሕጋዊ የሆኑትን ምትክ እንሰጣለን ግን ሕጋዊነቱን እያጣራን ነው” በማለት ከሸገር ምስረታ በፊት የነበሩ የካርታ አወጣጥ ስርዓት ላይ ችግሮች እንደነበሩባቸው ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው እየተለዩ መሆኑን ጠቁመው አብዛኛዎቹ አስፓልት ተከትሎ ያሉ ቤቶች ግን ሕገወጥ ናቸው ነው ያሉት፡፡ 
በከተማ አስተዳደሩ በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ወደ ስድስት ሺህ ቤቶች መነካታቸውን የገለጹት ዶ/ር ተሾመ ከነዚህ ውስጥ ህጋዊነታቸው ተለይቶ ለማጣሪያ የቀረቡት አራት መቶ ብቻ ናቸውም ነው ያሉት፡፡ በዓመት ስድስት ቢሊየን ግድም ገቢ ሲበሰብበት በነበረው ሸገር ከተማ በዚህ ዓመት እስካሁን 19 ቢሊን ብር ገቢ መሰብሰቡና በዓመቱ እቅዱም 26 ቢሊየን ብር መሰብሰብ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ 

ሥዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW