1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«የኮቴ ክፍያ» ያስመረራቸው የከባድ መኪና ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች

ሐሙስ፣ የካቲት 13 2017

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በየከተሞቹ መግቢያ እና መውጫ ላይ ገመድ እየዘረጉ ኬላዎች አበጅተው ከልክ በላይ በሚጠየቅ ክፍያ መማረራቸውን አሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች አማረሩ።

ኦሮሚያ ክልል
«በየቦታው የተዘረጉ የገመድ ኬላዎች የከባድ መኪና ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች እያማረሩ ነው።» ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Seyoum Getu/DW

በየኬላው «የኮቴ ክፍያ»

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በየከተሞቹ መግቢያ እና መውጫ ላይ ገመድ እየዘረጉ  ኬላዎች አበጅተው ከልክ በላይ በሚጠየቅ ክፍያ መማረራቸውን አሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች አማረሩ። ቅሬታ አቅራቢዎቹ በቅርቡ በጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገመድ እየዘረጉ ገቢ የሚያሰባስቡ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ቢያሳስቡም ድርጊቱ ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

«አንዳንድ ቦታ ላይ መሻሻል አሳይቷል። አሁን  እኛ ከሙገር እስከ አዳማ መስመር ነው በብዛት የምንሠራውና ከሙገር ወደ ሆለታ ስንመጣ ከነበሩት በሁለት ኬላዎች ሆለታ ላይ ነበረው አንዱ ተስቶ በእንጪኒ ከተማ ላይ ያለው ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው» ያሉን ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን አሽከርካሪ፤ በየቅርብ ርቀቱ ገመድ እየተዘረጋ በሚጠየቅ ክፍያ እጅጉን መማረራቸውን አስረድተዋል።

የአሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶች ምሬት

አሽከርካሪው እንደሚሉት፤ ከአዲስ አበባ አለፍ ብሎ ወደ አዳማ ሲኬድም በሁለቱም አቅጣጫ በየከተሞቹ መግቢያ እና መውጫ ክፍያ ይጠየቃል። «ሞጆ ላይ እንከፍላለን፤ አዳማ ላይም እንዲሁ። ወደ አምስት ሺህ ብር እንከፍላለን በዚህ መሃል ብቻ ባሉት ሦስት ኬላዎች” የሚሉት አሽከርካሪ በዚህም ክፉኛ መጎዳታቸውን አመልክተዋል። በአንድ ኬላ በትንሹ አንድ ሺህ ብር እንደሚጠየቅ ያስረዱት አሽከርካሪው ሺህ አምስት መቶ እና ሁለት ሺህም የሚከፈልባቸው ኬላዎች መኖራቸውንም አስረድተዋል፤ በ100 ኪ.ሜ. ርቀት ውስጥ ሦስት ኬላዎች ላይ ገንዘብ እንደሚጠየቁም በመግለጽ።

ይህ «የኬላዎች መብዛትና በየኬላዎቹ የሚጠየቁ ክፍያዎች በደል ነው» የሚሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ የተሽከርካሪ ባለንብረት ናቸው። እንደ እሳቸውም የሥራው ገቢና ወጪው አልመጣጠን እያላቸው ይገኛል። «የምንሠራውና የምናወጣው ወጪ እየተመጣጠነ አይደለም። መኪናው አስር ሺህ ከሆነ በኬላ ብቻ ስድስት ሺህ ብር እያወጣን ነው። ይህ የኬላ ክፍያ በመንግሥት እንኳ ይቁም ከተባለ ወዲህ እንዳለ እየቀጠለ ነው» በማለትም ሠርቶ መለወጥ አዳጋች እንደሆነባቸው አመልክተዋል።

የአሽከርካሪዎች ማሕበር አስተያየት

በዚህ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡን የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር ሥራ አስከያጅ አቶ ሰሎሞን ዘውዱ ነገሩ ከመቀነስ ይልቅ ተጠናክሮ መቀጠሉ አሳሳቢ ነው ብለዋል። «እንዳለ ነው ምንም የተለወጠ ነገር የለም። እንዳውም የተጨመረ ነገር እንዳለም ነው ከአሽከርካሪዎች የምንሰማው። እኛ ግን የምንለው ኬላ ነው ባጠቃላይ መፍረስ ያለበት። ለጸጥታ እና ለጉምሩክ ከሚዘጋጅ ኬላ ውጪ ያሉ ለኮቴ እየተባለ የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ምርት ጭኖ የሚንቀሳቀሰውን ባለንብረት ማስከፈል ምኑስ ነው ሕጋዊነቱ» በማለት ጠይቀዋል። መሰል ክፍያ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች መክፋቱን የገለጹት ሃላፊው በተለይም በመሃል ኦሮሚያ የጸጥታ ይዞታው የተሻለ በሚባልበት ይህን መቆጣጠር ተገቢ ነበር ነው ያሉት።

በኦሮሚያ ክልል የተሽከርካሪ ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች ምሬትምስል፦ Seyoum Getu/DW

የክልሉ መንግሥት የሰጠው አቅጣጫና አፈጻጸሙ

በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያባካሄደው ጉባኤ ላይ የመንግሥታቸውን አቅጣጫ ያመለከቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በየቦታው ገመድ እየዘረጉ ገንዘብ የሚሰበስቡ ድርጊቱን እንዲገቱ አሳስበው ነበር።

አሽከርካሪዎች ግን መሬት ላይ የወረደ አፈጻጸም አለመኖሩን አስረድተዋል። «መንግሥት እንዲህ ብሏል ብንል መሣሪያ ይዞ በየኬላው የሚቆም ሚሊሻ ሊያደምጠን እንኳ ፈቃደኛ አይደለም» ያሉት አስተያየት ሰጪው አሽከርካሪ በድርጊቱ ክፉኛ መማረራቸውን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ እንደማንኛውም ክልሎች አሰራር ሁለት ዓይነት የገቢ አሰባሰብ መኖሩ ይነገራል። እነዚህም በከተማ ልማት ቢሮ በኩል የሚዘረጋው የመዘጋጃ ቤት ገቢ እና በገቢዎች ቢሮ በኩል የሚዘረጋው መደበኛ ገቢ ናቸው። ሁለቱም መሥሪያ ቤቶች በየከተሞቹ ገመድ እየተዘረጋ የኮቴ በሚል የሚሰበሰበውን ገቢ እንደማያውቁ ከዚህ በፊት ለዶይቼ ቬለ መግለጻቸው አይዘነጋም።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW