1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኮንጎ የምርጫ ቀዉስ፣ የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ጉብኝት

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 20 2016

ምርጫዉ እንደገና እንዲደረግ ለመጠየቅ ተቃዋሚዎች ድምፅ በተሰጠ በሳምንቱ ሮብ የአደባባይ ሰልፍ ጠርተዉ ነበር።መንግስት ከለከለ።ሕገ-መንግስታዊ መብታቸዉን ለማስከበር የቆረጡ የተቃዋሚ ደጋፊዎች ግን የመንግስትን ክልከላ አልተቀበሉትም።ኪንሻ አደባባይ ከወጡት ተቃዋሚዎች አንዱ እንዲሕ ይላሉ።

የተቃዋሚ ሰልፈኞችና የፖሊስ ትንቅንቅ ኮንጎ ርዕሰ ከተማ ኪንሻሳ
ኪንሻ፣ ፖሊስ የሚያሳድዳቸዉ ተቃዋሚ ሰልፈፎች ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አንደኛዉ ፅሕፈት ቤት ለመግባት ሲሞክሩ ምስል፦ John Wessels/AFP

የኮንጎ የምርጫ ዉዝግብ፣ የሱዳን መሪዎች ጉብኝት

This browser does not support the audio element.

291223

ጤና ይስጥልኝ እንደምን አላችሁ።ለዛሬዉ ትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን ሁለት ርዕሶች መርጠናል።ርዕሶቹን፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የምርጫ ማግስት ቀዉስ እና የሱዳን ጦርነትና ዲፕሎማሲ ብለናቸዋል።በየተራ ይሰማሉ።አብራችሁኝ ቆዩ።
ጠንካራዉ፣ አምባገነኑ፣ ሙሰኛዉ-ንጉስ አከል ገዢ ሞቡቱ ሴሴሴኮ ይገዟት በነበረበት ዘመን ዛኢር ትባል ነበር።ከ1997 ወዲሕ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ባጭሩ ኮንጎ፣ ረዘም ሲል ኮንጎ-ኪንሻሳ በጣም ሲረዝም ግን  የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትባል ይዛለች።በዲሞክራሲና በሪብሊክ ቅፅል ያሸበረቀዉ ይፋ ስሟ ግን «መልከ ጥፉ---በስም ይደግፉ» ከማሰኘት በቀር  አንዱም የላትም።

እርግጥ ነዉ በጣም ሰፊ ነች።ከአፍሪቃ ሱዳን እሁለት ከተገመሰች ወዲሕ ከአልጄሪያ ቀጥላ ሁለተኛ ናት።ማዕድኖች፣ የዱር እንስሳቶች፣ ዉኃ፣ ደን በሽ ነዉ።የዲሞክራሲ-ሪፐብሊኩ ተቀፅላ ስምም ሆነ የምድር ዉስጥና ላይ የተፈጥሮ ሐብት 112 ሚሊዮን ለሚገመተዉ የኮንጎ ህዝብ ሕይወት፣ ደም አካሉን የሚያስከፍል ዕዳ-ነዉ የሆነበት።
ከቤልጂግ ቅኝ ገዢዎች በ1960 ነፃ ከወጣች ወዲሕ ተስፋ የተጣለባቸዉ ዉድ መሪዎችዋ ሳይቀሩ በምዕራባዉንና ለምዕራባዉያን ባደሩ ታጣቂዎች ተገድለዉበታል።ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ደግሞ ከሩዋንዳ እስከ አንጎላ የሚገኙ የአፍሪቃ ሐገራት በቀጥታ፣የአዉሮጳና አሜሪካ ሐብት ዘራፊዎች በተዘዋዋሪ ያን መከረኛ ሕዝብ በየአጋጣሚዉ እያነኮሩት ነዉ።ከ1996 ወዲሕ በተደረጉ ግጭት፣ ጦርነት፣ ጥቃትና መዘዛቸዉ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አልቋል።ዘገቦች እንደሚጠቁሙት የቆሰለ፣ የተደፈረች፤የተሰደደና የተፈናቀለዉ ከሟቹ በአስር እጥፍ ይበልጣል።
አሁንም ከ120 የሚበልጡ አማፂያን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የምስራቅ አፍሪቃ ማህበር ያዘመቷቸዉ የበርካታ ሐገራት በሺሕ የሚቆጠሩ ወታደሮች ይርመሰመሱባታል።ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ።

የኪንሻሳ ፖሊስ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ጎማ ከሚያቀጣጥሉበት ቦታ ሲያባርር ምስል፦ John Wessels/AFP

 

በ2000 ማብቂያ ላይ በሰዉ እጁ የተገደሉ አባታቸዉን ተክተዉ የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን የያዙት ጆሴፍ ካቢላ፣በ2019 በተደረገዉ ምርጫ ላሸነፉት ፌሊክስ አንቶኒ ሼሴኬዲ ሥልጣናቸዉን ሲያስረከቡ በቀዉስ ለምትናጠዉ ሐገር የመጀመሪያዉ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር፣ የሩቅም ቢሆን የሰላም ጭላንጭል ፈንጥቆ ነበር።ዳር ግን አልዘለቀም።ባለፈዉ ሳምንት ሮብ የተደረገዉ ምርጫ ደግሞ ሌላ ተስፋ መፈንጠቁ አልቀረም።
ፕሬዝደንታዊ፣ የብሔራዊና የክፍለ-ግዛቶችት መማክርት እንደራሴዎች የሚመረጡበት ድምፅ አሰጣጥ ገና ከጅምሩ የተዘበራረቀና የተሳከረ ሆኖ አረፈዉ።የነበሩ እንዳሉት ከ71 ሺዉ ድምፅ መጪያ ጣቢያዎች ብዙዎቹ ለረጅም ጊዜ አልተከፈቱም።የተከፈቱት ሰዎች በሥርዓት ድምፅ የሚሰጡባቸዉ ቦታና ቁሳቁች አልነበራቸዉም።እሱ ርዕሰ ከተማ ኪንሻ ዉስጥ የሚገኝ የአንድ የድምፅ መስጪያ ጣቢያ ታዛቢ ነበር። 
«ለረጅም ጊዜ እዚሕ ቆመናል።የአካባቢዉ ታዛቢዎች ነን።ድምፅ መስጪያ ጣቢያዉ ዉስጥ ገብተን ሂደቱን መከታተል ነበረብን።ግን እዚሕ እንድንጠብቅ ነገሩን።ምን እየተደረገ እንደሆነ አልገባኝም።»
ብዙዎች አልገባቸዉም።ገባን ያሉት የምርጫ ኮሚሽን ባለስልጣናት ለሮብ ብቻ ተይዞ የነበረዉን የድምፅ መስጪያ ዕለተ ወደ ሐሙስ አራዘሙት።ተቃዋሚዎችን ለማሳመን ግን በቂ ምክንያት አልነበራቸዉም።የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አጠቃላይ የድምፅ አሰጣጡን «አሳፋሪ» በማለት ዉድቅ አደረጉት።

ምርጫዉ እንደገና እንዲደረግ ለመጠየቅ ተቃዋሚዎች ድምፅ በተሰጠ በሳምንቱ ሮብ የአደባባይ ሰልፍ ጠርተዉ ነበር።መንግስት ከለከለ።ሕገ-መንግስታዊ መብታቸዉን ለማስከበር የቆረጡ የተቃዋሚ ደጋፊዎች ግን የመንግስትን ክልከላ አልተቀበሉትም።ኪንሻ አደባባይ ከወጡት ተቃዋሚዎች አንዱ እንዲሕ ይላሉ።
                                    
«ህዝቡ እየተቃወመ ነዉ።እየተቃወምን ነዉ።መሰለፍ ሕገ መንግስታዊ መብታችን ነዉ።ቀዉሱ አላበቃም ምክንያቱም ሚስተር ካዲማ የፈጠሩት የምርጫ ሁከት እንደቀጠለ ነዉ።ኃላፊነቱን መዉሰድ አለባቸዉ።መጠየቅ አለባቸዉ።ኮንጎ አትሸጥም።ከአቋማችን ፈቅ አንልም።»
ዴኒስ ካዲማ ካዛዲ «ገለልተኛ» የሚባለዉ የኮንጎ አስመራጭ ኮሚሽን የበላይ ኃላፊ ናቸዉ።ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸዉ ለድምፅ አሰጣጡ ሒደት መዝረክረክ ካዲማን ዋና ተጠያቂ ያደርጓቸዋል።ባለፈዉ ሮብ ደጋፊዎቻቸዉን አስከትለዉ ኪንሻ አደባባይ ከወጡ ፕሬዝደንታዊ አጩዎች አንዱ ማርቲን ፋዩሉ ካዲማ ያዘጋጁት ያሉትን ምርጫ ሂደት «አሳፋሪ» ብለዉታል።
«ይሕን የተተራመሰ፣ አሳፋሪ ምርጫ  በመቃወም እንሰለፋለን ብለናል።ለረጅም ጊዜ ስነግራችሁ ነበር።ሚስተር ካዲማና የምርጫ ባለሙያ ተብዬዎቹ የምርጫ ሁከት እየፈጠሩ ነዉ ብዬ ተናግሬ ነበር።ይኸዉ አሁን ታየ።»
ሰልፈኞቹ ተቃዉሟቸዉን ለማሰማት በተለይ ወደ ምርጫ ኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት ለመጠጋት እድል አላገኙም።ፖሊስ ባስለቃሽ ጢስ-ያጥናቸዉ፣ በአስደንጋጭ ተኩስ ያሸብር፣ በዱላ፣ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት በእዉነተኛ ጥይትም ይደበድባቸዉ ያዘ።

በአስር የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ቆሰሉ።ሌሎች ታሰሩ።ፕሬዝደንታዊዉ እጩ ማርቲን ፋይሉ እንዳሉት ቢያንስ 11 ደጋፊዎቻቸዉ በጥይት ተመትተዉ ቆስለዋል።
«ምንድነዉ የያዝኩት? ጥይት የተሞላ  ካርታ ነዉ።ይታያችኋል 11 ሰዎች በጣም ተጎድተዋል።ሆስፒታል ለማድረስ በጣም ተቸግረን ነበር።አመጣናቸዉ ግን ይሕን ተመልከቱት አጠገቤ ነዉ ያረፈዉ።ጥይት ነዉ።እዉነተኛ ጥይት።እዚያ የነበራችሁ አይታችሁታል።ከባድ ተኩስ ነበር።»

የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዉና የተቃዋሚ ፓርቲዉ ዕጩ ዴኒስ ሙክዌግ ድምፅ ሲሰጡምስል፦ ZOHRA BENSEMRA/REUTERS

የኪንሻሳ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ብላይስ ኪሊምባሊንባ ግን ረጋ፣ቀዝቀዝ ግን ኮስተር ብለዉ «ነገር ፈላጊዎቹ» ሰልፈኞቹ ናቸዉ ዓይነት አሉ።
                      
«እንዴት እንደሆነ አይታችኋል።የሰልፉ አደራጆች ክልከላዉን አንቀበልም ሲሉ አይታችኋል።ፖሊስ ነገሩን ለማብረድ ጣልቃ ሲገባ አንዳድ ረባሽ ሰዎች ድንጋይ ሲወረዉሩና  ሰዎች ላይ አደጋ ለማድረስ ሲሞክሩ አይተናል።»
የድምፅ አሰጣጡ ሒደት ብዙ መዛባት እንደነበረበት የዉጪ ታዛቢዎችም እየተናገሩ ነዉ።የምርጫዉ ዉጤት ግን እስከ ትናንት በይፋ አልተነገረም።መወዛገብ፣ መወቃቀስ፣ መካሰሱ  ቀጥሏል።ኮንጎ ለምዳዋለች።
                                         
ከኮንጎ የምርጫ ቀዉስ ወደ ሱዳን ግጭት ምስቅልቅል እንለፍ።በ2011 ደቡብ ሱዳንን ከተገነጠለች ወዲሕ በስፋት ከአፍሪቃና ከአረብ ሊግ አባላት አንደኛ፣ ከዓለም 10ኛነቷን ለአልጄሪያ ብትለቅም ዛሬም ትልቅ ናት።ከአፍሪቃ ሶስተኛ።አብዛኛ የነዳጅ ዘይት ጉርጓዶችዋ ከነደቡብ ሱዳን ጋር በመሄዱ የምትኩራራበት የተፈጥሮ ሐብት ብዙ የላትም።
ኩሾች፣ ኑብያዎች፣ መሕዲዎች፣ ቱርኮች፣ ግብፆች፣ ብሪታንያዎች የተፈራረቁባት ጥንታዊ ሐገር ሱዳን በ1956 ነፃ ከወጣች ወዲሕ መፈንቅለ መንግስት፣ የድንበር ግጭና የእርስ በርስ ጦርነት ተለይቷት አያዉቅም።ባለፈዉ ሚዚያ ርዕሰ ከተማ ካርቱም ዉስጥ የተጫረዉ የርስ በርስ ጦርነት ግን በዓይነት፣ ምክንያት፣ሰበቡ ከዚሕ ቀደም ከሚታወቀዉ ብዙ የተለየ ነዉ።

የሱዳን ርዕሰ ከተማ ካርቱም በርስበርስ ጦርነቱ ክፉኛ ከተጎዱት አካባቢዎች አንዱ ነዉምስል፦ AFP

የቀድሞዉ የሐገሪቱ መሪ የዑመር አል በሽር እኩል አገልጋዮች፣ በአልበሽር ላይ አኩል አማፂዎች፣ አልበሽርን ተባብረዉ እኩል ያስወገዱ፣ የሲቢል ተቃዋሚዎቻቸዉን በጋራ የመከቱ-የመቱም፣ አለቃና ምክትል ጄኔራሎች ተጣሉ።ዋናዉ አለቃ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አልቡርሐን የሱዳንን መከላከያ ሠራዊት፣ ምክትላቸዉ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐሚቲ) የፈጥኖ ደራሹን ጦር ይዘዉ በገጠሙት  ዉጊያ በትንሽ ግምት 10 ሺሕ ሰላማዊ ሰዉ ተገድሏል።ወደ 10 ሺሕ የሚደርስ ቆስሏል።45 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሱዳን ሕዝብ 5 ሚሊዮኑ አድም ተሰድዷል አለያም ተፈናቅሏል።ቤት ንብረታቸዉ ከወደመባቸዉ ተፈናቃዮች አንዷ ሐዋ ሱሊማን ባስተርጓሚ እንዳሉት ፈጣሪያቸዉን ከመማፀን በላይ የራሳቸዉም የልጆቻቸዉም የአጠቃላይ ሱዳናዉያንም ቀጣይ ፣ ኑሮና ሕልዉናን እንዴትነት አያዉቁትም።

«እዚሕ ሁኔታዉ መጥፎ ነዉ።ዉጊያ ባለመቆሙ የወደፊቱ ኑሮና ሕልዉናችን አይታወቅም።ጦርነቱ ቢቆም እንኳ ባስቸኳይ ወደ ቀያችን መመለስ አንችልም።ምክንያቱም መኖሪያችን ወድሟል።ጦርነቱ ይቆማል፤ወደየቀያችንም እንመለሳለን የሚል ተስፋ ግን አለን።»
የተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ጦርነቱን እንዲያቆሙ ለማግባባት ከዚሕ ቀደም የአረብ፣ የአፍሪቃና የአሜሪካ መንግስታትና የተለያዩ  ድርጅቶች ብዙ ጥረዋል።የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች ባለፈዉ በጋ በዩናይትድ ስቴትስና በሳዑዲ አረቢያ ሸምጋይነት ጂዳ-ሳዑዲ አረቢያ ላይ ያደረጉት ድርድር ለሁነኛ ስምምነት ይደርሳል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር።ከተስፋ ግን አላለፈም።
ከጂዳዉ ድርድር በፊት የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ሁለቱን ወገኖች ለማስታረቅ ያቀረበዉ ጥያቄ ተቀባይነት አላገኝም።የሱዳን ተፋላሚዎች ሐገራቸዉ የመሰረተችና አባል የሆነችበትን ድርጅት ትተዉ ጂዳ ላይ መደራደራቸዉ ድርድሩ የልብ ሳይሆን የኃይልና የጥቅም እንደነበረ በድርድሩ መሐል የተናገሩ ታዛቢዎች ነበሩ።
የጅዳዉ ድርድር እስኪ ከሽፍ ድረስ የታዛቢዎቹን አስተያየት የሰማ እንጂ የተቀበለ አልነበረም።የፖለቲካ ተንታኝ አብደልሞኒም አቡ ኢድሪስ በቀደም እንዳሉት ጦርነቱን ለማቆም አሁንም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ መቀጠል አለበት።

የሱዳን ወታደራዊ ገዢ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አልቡርሐን ባለፈዉ ወር ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪቃ ሐገራትን ጎብኝተዋልምስል፦ Sudanese Army/AFP

 

«ግጭቱን ከሱዳን አጠቃላይ አካባቢ 40 በመቶዉን አዳርሷል።ግጭቱ በሰፋና በተራዘመ ቁጥር የሟች-ስደተኞቹ ቁጥር እየጨመረ ነዉ።ግጭቱ ባለበት እንዲቆም ካልተደረገ ወደ አጎራባች ሐገራትም ሊዛመት ይችላል።»

ጦርነቱ እየሰፋ፣ ዉጤቱ እየከፋ፣ኃብታም-ኃላኑ መንግስታት ቀጥታ በተማገዱበት በሌላ ጦርነትና ግጭት እየተወጠሩ ሲመጡ  የሱዳን ተፋላሚዎች ፊታቸዉን ወደ አፍሪቃ በጣሙን ወደ ኢጋድ የመለሱ መስለዋል።ጄኔራል አብዱፈታሕ አል ቡርሐን ባለፈዉ ሕዳር ኢትዮጵያና ኬንያን ጨምሮ የአካባቢዉን ሐገራት ጎብኝተዋል።
ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ደግሞ ባለፈዉ ሮብና ሐሙስ ዩጋንዳና ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።የተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ከየአስተናጋጆቻቸዉ ጋር በድብቅ የመከሩ-የተስማሙትን የሚያዉቁት እነሱዉ ናቸዉ።በየጉብኝቱ ወቅት ከየርዕሰ ከተሞቹ በይፋ በወጡት መግለጫዎች መሠረት ግን ሁለቱም መሪዎች ከየሐገራቱ ባለስልጣናት ጋር የተነጋገሩት ጦርነቱን በድርድር ማስቆም ስለሚቻልበት ብልሐት ነዉ።

የሱድን ፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥ መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ሰሞኑን ኢትዮጵያና ዩጋንዳን ጎብኝተዋል።ምስል፦ Ashraf Shazly/AFP

 

ኢጋድ ባለፈዉ ሕዳር ባወጣዉ መግለጫዉ ሁለቱ የተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ስለተኩስ አቁም ለመነጋገር መስማማታቸዉን አስታዉቋል።የኢጋድን መግለጫ ሁለቱም አላረጋገጡም።አላስተባበሉምም። ትኩረት በአፍሪቃ የዛዉ አበቃ።

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW