1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኾቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ በትግራይ

ሰኞ፣ ሐምሌ 4 2014

በተወሳሰበ የጤና ስርዓት ሰበብ ችግር ላይ ባለችው ትግራይ፥ የኮረና ቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራጨ መሆኑ ይገለፃል። የትግራይ ጤና ቢሮ ጥናት እንደሚያመለክተው በትግራይ በቅርቡ የኮረና ቫይረስ ምርመራ ከተደረገባቸው ዜጎች መካከል 30 በመቶዎቹ በቫይረሱ ተይዘዋል። ቫይረሱ ከሚገኝባቸው 100 ሰዎች መካከል ሶስቱ እንደሚሞቱ ጥናቱ ያስረዳል።

Äthiopien Mekelle | Tigray Region startet Corona Impfungen
ምስል Million Hailessilassie/DW

የኾቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ በትግራይ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ ለ1 ነጥብ 6 ሚልዮን ዜጎች የኮረና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ። በትግራይ የኮረና ቫይረስ  በከፍተኛ ደረጃ መሰራጨቱን የሚገልፀው የትግራይ ጤና ቢሮ በዓለም ጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ አቅራቢነት ዛሬ የተጀመረው የኮረና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ስርጭቱን ለመግታት ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል። በትግራይ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የኮረና ክትባት መስጠት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ተቋርጧል። በትግራይ ከ100 ሰዎች መካከል 30ዎቹ ቫይረሱ ያለባቸው ሲሆን ከመካከላቸው 3ቱ በቫይረሱ ሰበብ እንደሚሞቱ በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት ያመላክታል። ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ከመቀሌ ዝርዝሩን ልኮልናል።

ጦርነቱ ተከትሎ በተፈጠረው ሁኔታ በተወሳሰበ የጤና ስርዓት ችግር ላይ ባለችው ትግራይ፥ የኮረና ቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራጨ መሆኑ ይገለፃል። የትግራይ ጤና ቢሮ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው በትግራይ በቅርቡ የኮረና ቫይረስ ምርመራ ከተደረገባቸው ዜጎች መካከል 30 በመቶዎቹ በቫይረሱ ተይዘዋል። ቫይረሱ ከሚገኝባቸው አንድ መቶ ሰዎች መካከል ደግሞ ሶስቱ እንደሚሞቱ ጥናቱ ያስረዳል። ይህን ችግር ለመፍታት በዓለም ጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ አቅራቢነት ከዛሬ ሐምሌ 4 ቀን ጀምሮ፣ በትግራይ ለ1 ነጥብ 6 ሚልዮን ዜጎች የኮረና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ለመስጠት ዘመቻ ተጀምሯል። 

ምስል Million Hailessilassie/DW

የትግራይ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሓጎስ ጎደፋይ እንደሚሉት በትግራይ ወረርሽኙን ለመግታት የሚያስችል የጤና ስርዓት ባለመኖሩ፣ በቫይረሱ የተያዙትን በምርመራ ለመለየት በቂ ግብአት ባለመኖሩ፣ ኮረና የተገኘባቸው ዜጎችን ለይቶ ለማከም አቅም ስለሌለ ክትባት ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት ታቅዶ የክትባት ዘመቻው መጀመሩን ይገልፃሉ። ይህ በዓለም ጤና ድርጅት አቅራቢነት ወደ ትግራይ የደረሰው ክትባት ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተባለው መሆኑ የትግራይ ጤና ቢሮ አስታውቋል። 

በመቐለ ብቻ በሁለት ቀናት 300 ሺህ ዜጎች በተዘጋጁ 94 የኮረና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ማእከላት ለመከተብ መታቀዱ ተገልጿል።ክትባቱን ሲወስዱ አግኝተን ያነጋገርናቸው የመቐለ ነዋሪዎች የመከተብ እድል በማግኘታቸው  ደስተኞች ናቸው። ከመቐለ ውጭ  ክትባቱን የማሰራጨት ስራ በነዳጅ አቅርቦት ውሱንነት፣ ለክትባቱ በሚሆን ማቀዝቀዣ እጦት እና ሌሎች ምክንያቶች በሚፈለገው ደረጃ እየሄደ እንዳልሆነ የትግራይ ጤና ቢሮ ገልጿል። እስካሁን ወደ ትግራይ የገባው የኮረና መከላከያ ክትባት መጠን ከሚፈለገው 48 በመቶ ብቻ መሆኑን የገለፁት የትግራይ ጤና ቢሮ ሐላፊ ዶክተር ሓጎስ ጎደፋይ፥ የተቀረው እንዲመጣ፣ ሌሎች መድኃኒቶች እና የሕክምና ቁሳቁሶች ወደ ክልሉ እንዲደርሱ ጥረቱ መቀጠሉን ይገልፃሉ።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW