1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወለጋ ግጭትና የፈጠረው ሥጋት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 27 2015

በምስራቅ ወለጋ ዞን ሰሞኑን የከፋ አለመረጋጋት ውስጥ ገብተው ከቆዩ አከባቢዎች አንዷ የሆነችው የጊዳ አያና ጉቲን ከተማ መጠነኛ መረጋጋት እንደሚስተዋልባት ነዋሪዎች ገለጹ። ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ድርጅቶችም ሰሞኑን በወለጋ የገጠመውን አለመረጋጋት አደገኛነቱነን በመግለጽ ለእልባቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።

Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

የወለጋው አለመረጋጋት አደገኛ ነው ተብሏል

This browser does not support the audio element.

በምስራቅ ወለጋ ዞን ሰሞኑን የከፋ አለመረጋጋት ውስጥ ገብተው ከቆዩ አከባቢዎች አንዷ የሆነችው የጊዳ አያና ጉቲን ከተማ መጠነኛ መረጋጋት እንደሚስተዋልባት ነዋሪዎች ገለጹ። ይሁንና በአከባቢው ለቀናት የዘለቀው አለመረጋጋት ወደ አጎራባች ወረዳዎች ጭምር እንዳይሻገርም በመንግስት አስቀድሞ ጥብቅ የፀጥታ አካላት ጥንቃቄ እንዲወሰድ ሲሉ ከአከባቢው የተፈናቀሉ ጠይቀዋል። ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ድርጅቶችም ሰሞኑን በወለጋ የገጠመውን አለመረጋጋት አደገኛነቱነን በመግለጽ ለእልባቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በቅዳሜው የጊዳ አያና ጉቲን ከተማው የታጣቂዎች ጥቃት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት ነዋሪ እንደሚሉት በግጭቱ ክፉኛ በተጎዳችው ጉቲን አሁን ቢያንስ የተኩስ ድምጽ አይሰማም፡፡ የአገር መከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማዋ ከገባ በኋላ ቢያንስ ግድያ ቆሟል ያሉት እኚው ነዋሪ በአከባቢው አሁንም ባጠላው የፀጥታ ስጋት ምክኒያት ነወሳሪዎች ከቤታቸው ወጥተው መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ግን አመልክተዋል፡፡ 
«የአገር መከላከያ ሰራዊት ከገባ በኋላ በጉቲን ከተማ አሁን ህብረተሰቡ መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡ ግን አዘናግቶ ማጥቃት ሊኖር ችላል በሚል አሁንም ትልቅ ስጋት አለ፡፡ አሁን በከተማው የገባው ሃይል ለሰላማዊ ዜጎች ከለላ ከመሆን ውጪ ምንም የወሰደ ርምጃ ባለመኖሩ ስጋቱ ቀጥሏል፡፡ ሰው የገደሉና ያፈናቀሉ ወንጀለኞች ብጠየቁ ለፍርድም ቢቀርቡ ማህበረሰቡ ተስፋ ይኖረዋል፡፡ ከአልጋ ቤት ሁሉ ተወስደው ቆስለው በጫካ የተጣሉ አሁን ላይ ተነስተው ወደ ህክምና እየተወሰዱ ነው፡፡ እነዚህ ቢጠየቁ ሁሉንም ነገር ያውቃሉና ፍትህ ብሰፍን የሰው ተስፋ ይለመልማል፡፡ እነዚህ በቂ ማስረጃ መሆን ብችሉም እስካሁን በመንግስት በኩል አልተጠየቁም» ብለዋል፡፡ 

ዘላቂ መፍትኄ የሚሻው የፀጥታ ስጋት በኦሮሚያ ክልል

እኚው ነዋሪ እንዳሉት አከባቢው አሁንም ፈጽሞ አልተረጋጋም፡፡ ለቀናት ቤታቸውን ዘግተው የቆዩት ነዋሪዎች ገና በራቸውን ብከፍቱም የደረሰው አዝመራቸውን እንኳ ወጥተው መሰብሰብ እንደማይችሉም አክለዋል፡፡ 

“ሰው እንደው መውጫ በሩን ነው እንጂ የከፈተው ራቅ ብሎ ከቀዬው መጓዝ የሚችል የለም፡፡ አምናም የደረሰ አዝመራ ነው የተቃጠለውና አሁንም ያ እንዳይደገም ነው ያለው ሌላው ስጋት፡፡ ያለው ሁኔታ እጅግ የተወሳሰበ በመሆኑ የነጻነት አየር የሚተነፍስ የለም፡፡ ከዚህ ቀደምም ከከተማው ወጣ ሲባል ግድያ እና አፈናዎች ይፈጸሙ ስለነበር አሁንም አከባቢው ከስጋት አልጸዳም፡፡ ቢያንስ ግን ከተማ ውስጥ የጥይት ድምጽ አይሰማም አሁን” በማለትም መጠነኛ የፀጥታ መረጋጋት መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ በሰሞነኛው የምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ግጭት ስጋት የገባቸው የአሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከሁለት ዓመታት ወዲህ አለመረጋጋት በፀናባት የአሙሩ ወረዳ በርካታ ቀበሌያት የተፈናቀሉ የውስጥ ተፈናቃዮች የሚበዙባት አገምሳ ቀጣይ የአለመረጋጋቱ ሰለባ እንዳትሆንም ነው ነዋሪው ስጋታቸውን የገለጹት፡፡ 
“ከዙሪያው ከ12-13 ቀበሌያት የተፈናቀሉ በዚህች ከተማ ውስጥ ተሸሽገዋል፡፡ ባለፈው ነሃሴ 23 እና 24 ይህቺ ከተማ የታጣቂዎች ሰለባ በመሆን ከ90 በላይ ሰዎች አልቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ ሰሞኑን በኪረሙ ወረዳ የጅምላ ጭፍጨፋ ነው እየተፈጸመ ያለው፡፡ አሁን በዚህ በተፈናቃይ በተጨናነቀች ከተማ በቂ የፀጥታ ሃይል ጥበቃ የለም፡፡ ሰሞኑን በኪረሙ እና ጉቲን የተከሰተ ደግሞ ለኛ ትልቅ ስጋት ነው ያጫረብን፡፡ እኛ እያልን ያለነው ስጋት የሚሆንብንን መንገድ መንግስት ይዝጋልን፣ ለሰላማችን ዋስትና ይስጠን ጭለማ ውስጥ ነን ይድረስልን ብንልም ሰሚ አጣን” ይላሉ፡፡  መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ጸጥታ እንዲያስከብር መጠየቁ
እኚህ የአገምሳ ከተማ ነዋሪ እንደሚሉት በ7 ኪ.ሜ. ርቀት የአጎራባች ኪረሙ ወረዳ ውስጥ ተኩስ እና ስጋት መንገሱ ከአገምሳ አቅም ያላቸው ወደ አሙሩ ወረዳ ዋና ከተማ ኦቦራ ከወዲሁ ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ በዚህች ከተማ ከነሃሴው ግጭት በኋላ ድጋፍም ሆነ መሰረታዊ አገልግሎት የማይደርስላት መሆኑም ሌላው የማህበረሰቡን ችግር አባብሷል ብለዋል፡፡ 
“ወላድ የምትሄድበት የህክምና ማዕከል የለነም፡፡ መብራት፣ ውሃ እና መንገድ የለንም፡፡ ወደ አሙሩ ወረዳ የአስተዳደር ከተማ እንዳናመራ እዚሁ ርገቴ በሚባል ስፍራ መንገድ ተዘግቶብናል፡፡ ሴቶች በእጅ እየፈጩ ነው ያለችውን እያበሉን ያሉት፡፡ መንግስት ለደህንነታችን ቀድሞ እንዲደርስልን አደራ ለማለት ነው፡፡”
ሰሞኑን በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ እና ጊዳ አያና በተባሉ ሁለት ወረዳዎች የፀጥታ መደፍረስ ጎልቶ መስተዋሉን ተከትሎ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የተለያዩ አስተያየት እየሰነዘሩ ነው፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግስት የመከላከያ ሰራዊትን በአከባቢው በማስፈር ዜጎችን ልታደግ ይገባል ሲል፤ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር ፖለቲከኛ ጃዋር መሃመድ በማህበራዊ ገጻቸው ላይ ባሰራጩት መረጃ መንግስት ምንም እንዳልተፈጠረ ማስመሰሉን በማቆም ግጭቱ በተስፋፋባቸው አከባቢዎቹ ማስቆም የሚገባው አሁን ነው ሲሉ በአጽእኖት ጠይቀዋል፡፡ አቶ ጃዋር በዛሬው እለትም በማህበራዊ ገጻቸው እንደጻፉት “ሙሉ በሙሉ አለመረጋጋት ውስጥ ትገኛለች” ባሉት ኦሮሚያ ክልል “በሳምንት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለው ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፤ በመሆኑም መንግስት አካሄዱን በማጤን ሳይረፍድ አሁን እርምጃ እንዲወስ ግፊት ማድረግ ይገባል” ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በበኩሉ በኦሮሚያ ይፈጸማል ላለው አሰቃቂ ግድያ መንግስት ማብቂያውን እንዲያበጅ ጠይቋል፡፡
ስለሰሞነኛው የምስራቅ ወለጋው አለመረጋጋት እስካሁን መንግስት በይፋ ወጥቶ አላብራራም፡፡ ዶቼ ቬለ የክልሉ እና የፌዴራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣናትን በስልክ ደውሎ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረትም አልሰመረም፡፡ ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ስለ የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አዋሳን አለመረጋጋት ተጠይቀው የነበሩት የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ ከአከባቢው አለመረጋጋት ጀርባ “ጽንፈኛ” ያሏቸው “ሸነ እና የአማራ ታጣቂ” የሚዘረጉት የፖለቲካ ደባ ነው ብለው ነበር፡፡ 

ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችምስል Alemenw Mekonnen/DW

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW