1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወሲብ ንግድ በአውሮጳ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 26 2008

ከባድ ወንጀል እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚባለው« በሰዎች መነገድ» በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፋ በመሄድ ላይ መሆኑን በመስኩ ጥናት የሚያካሂዱ ባለሞያዎች ያስረዳሉ ። ባለሞያዎች እንደሚሉት በተለይ የወንጀሉ ሰለባ ከሚሆኑ ሴቶች አብዛኛዎቹ ዘመናዊ ባርነት እየተባለ በሚጠራው የወሲብ ንግድ እና የጉልበት ሥራ እንዲሰማሩ ይገደዳሉ ።

Prostituierte an einer Bar im Bordell Pascha in Köln Archiv 2006
ምስል picture-alliance/dpa/R. Vennenbernd

አሳሳቢው የወሲብ ንግድ በአውሮጳ

This browser does not support the audio element.

ናይጀሪያዊቷ ጆይ ኬ በልጅ ሞግዚትነት ሥራ እንደምታገኝ ቃል ተገብቶላት ነበር ወደ ኢጣልያ የሄደችው ። ኢጣልያ ስትደርስ ግን በውኗም በህልሟም ያልጠበቀችው ነገር ነበር የገጠማት ። ሞግዚትነቱ ተስፋ ሆኖ ቀርቶ መጨረሻዋ አንዲት መዳም የሚሏት ናይጀሪያዊት ቤት ሆኖ አረፈ ። ማዳም ከናይጀሪያ እንደ እንደ ጆይ ሁሉ ሥራ ታገኛላችሁ የሚል ተስፋ ተሰጥቶአቸው ወደ ኢጣልያ የሚመጡ ወጣት ናይጀሪያውያን ሴቶችን ለወሲብ ንግድ የሚያሰማሩ አንጋፋ ሴተኛ አዳሪዎች የተለምዶ መጠሪያ ነው ። ጆይ ኢጣልያ ሄዳ ሳትወድ በግድ በማዳም አሠሪነት በሴተኛ አዳሪነት ተሰማራች ። ማዳም መጀመሪያ እንደተቀበለቻት ፣ ባለ እዳ መሆንዋን ነበር ያረዳቻት ።እርስዋ እንደምትለው ኢጣልያ ከመጣችበት ጊዜ አንስቶ ገንዘብ እጇ ገብቶ አያውቅም ።
« ትልቅ ተስፋ ሰንቄ ነበር የመጣሁት ።ያኔ ወዲዚህ ስመጣ ስለ ጉዞዬ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም ። መጨረሻዬ ሴተኛ አዳሪነት ይሆናል ብዬም አልገመትኩም ነበር ።እሷ (ማዳም)ለጉዞዬ የወጣው 45 ሺህ ዩሮ እዳ እንዳለብኝ እና ሁሉንም ገንዘብ መክፈል እንደሚጠበቅብኝ ነገረችኝ ።»
የዓለም የሥራ ድርጅት በእንግሊዘኛው ምህፃር ILO እንደሚለው በዓለም ዙሪያ ለሴተኛ አዳሪነት እና ለልጅ ወታደርነት እንዲሁም ለተለያዩ የጉልበት ሥራዎች እንደ ባሪያ የሚታገቱ ፣ የሚሸጡ እና የሚለወጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 21 ሚሊዮን ይጠጋል ። ከመካከላቸው 11.4 ሚሊዮኑ ሴቶች እና ህጻናት ናቸው ። ባለፈው የካቲት ለአውሮጳ ህብረት ፓርላማ የቀረበ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ይህን መሰሉ ንግድ እንዲስፋፋ እገዛ ካደረጉት ውስጥ የሰዎች እንቅስቃሴ መጨመር እና አዳዳስ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሽ ናቸው ። በጥናቱ መሠረት የችግሩ ዋነኛ ተጠቂዎች ሴቶች እና ህፃናት ናቸው በተ.መ የአደንዛዥ እጾች እና የወንጀል ተከላካይ ቢሮ በእንግሊዘኛው ምህጻር UNODC «በሰዎች መነገድ» ላይ ያተኮረውን የመጀመሪያ ዘገባ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ካዘጋጁት አጥኝዎች አንዱ ፋብሪዞ ሳሪካ ናቸው ። ሳሪካ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት በዚህ ሥራ የተሰማሩት ደላሎች አይነት እና አደረጃጀት የተለያየ ነው ።
«በጣም የተለያዩ ህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች አሉ ። ሥራው የሚከናወነው በየአካባቢው ባሉ ግለሰቦች እንዲሁም አነስተኛ ቡድኖች አማካይነት ነው ።እነዚህ ሰዎች ምናልባት በጎረቤት ሃገራት ውስጥም ይህን ሥራ ያካሂዳሉ ።ከዚህ ሌላ ትላልቅ እና የተደራጁ በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ከአንዱ ሃገር ወደ ሌላው የሚያሸሹ በጉቦ እና በመሳሰሉት ወንጀሎች ውስጥ የተዘፈቁ ወንጀለኛ ቡድኖችም ይገኙበታል ።»
ሰዎችን እንደ እቃ የሚሸጡ እና የሚለውጡት እነዚህ ደላሎች ሴቶቹን የሚመለምሉት ከማታለል በተጨማሪ በማስፈራራት እና ኃይልን በመጠቀምም ጭምር ነው ። ከዚህ ወንጀል ተጠቂዎች አብዛኛዎቹም የተሻለ ህይወት ፍለጋ ከሃገራቸው ውጭ ለመሄድ የሚፈልጉ የድህነት ህይወት የሚገፉ ሰዎች ናቸው ። ከአፍሪቃ ሴቶች ለወሲብ ንግድ ወደ አውሮጳ ከሚሰደዱባቸው ሃገራት ግንባር ቀደሟ ናይጀሪያ ናት ። ማዳሞች እና ሌሎች ጉልበተኛ ቡድኖች በአውሮጳ የተከሰተውን የስደተኞች ቀውስ በመጠቀም በርካታ ልጃገረዶችን ወደ መንግሥት አልባዋ ሊቢያ እየላኩ ነው ። ሴቶቹ እድል ከቀናቸው በሜዲቴራንያን ባህር በኩል በህይወት ኢጣልያ ሊገቡ ይችላሉ ። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተለው «ዎክ ፍሪ» የተባለው ድርጅት እንደሚለው በጎርጎሮሳውያኑ 2015 ፣ከ5600 በላይ ሴት እና ልጃገረድ ናይጀሪያውያን አደገኛውን የባህር ጉዞ አልፈው ኢጣልያ ገብተዋል ። ባለፉት 7 ወራት በተመሳሳይ መንገድ ኢጣልያ የደረሱት ናይጀሪያውያን 1250 ደርሰዋል ። የዚህ ወንጀል ሰለባዎች አውሮጳ የሚመጡት በተጭበረበረ ሰነድ በአውሮፕላንም ጭምር መሆኑን የተመ የአደንዛዥ እጾች እና የወንጀል ተከላካይ ቢሮ በእንግሊዘኛው ምህጻር UNODC አስታውቋል ። አውሮጳ ከመጡት ከየአምስቱ ሴቶች ፣አራቱ በሴተኛ አዳሪነት ነው የሚሰማሩት ።ዩሮስታት የተባለው የአውሮጳ ስታስቲክስ ጽህፈት ቤት ከ28 የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ያሰባሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው ዘመናዊው የሰዎች ፍንገላ በዋነኛነት የሚካሄደው በአውሮጳ ህብረት ድንበር ውስጥ ነው ። ከዚህ ወንጀል ሰለባዎች 65 በመቶው የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ዜጎች ናቸው ። በተለይ በሸንገን አባል ሃገራት ሰዎቹን ለዚሁ ሥራ ከአገር ወደ አገር የማዛወሩ ሥራ የሚከናወነው በዋነኛነት ከምሥራቅ እና ከመካከለኛ አውሮጳ ወደ ምዕራብ አውሮጳ ነው ። ፍንገላው በዋነኛነት ከሮማንያ እና ከቡልጋርያ የሚካሄድ ሲሆን ከእስያ ከአፍሪቃ እና ከደቡብ አሜሪካም የሚመጡት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም ።ባለፉት 10 ዓመታት እየቀነሰ ቢሄድም ከሩስያ ፣ከዩክሬን እና ከሞልዶቫ ሰዎች እየተፈነገሉ ወደ ምዕራብ አውሮጳ መምጣታቸው አልቆመም ።ይህ ወንጀልለመከላከል የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ከወሲብ ንግድ ጋር የተያያዘን እንቅስቃሴ በሙሉ በወንጀል ድርጊትነት ከመፈረጅ አንስቶ ልዩ ልዩ ህጎችን አውጥተዋል ። በተመድ ደረጃም በጎርጎሮሳዊው በህዳር 2000 ዓም በተለይ የሴቶች እና ህጻናትን ፍንገላ ለመከላከል እና በወንጀሉ የተሰማሩ ሰዎችን ለመቅጣት የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ አንድ ደንብ አጽድቋል ።በዚሁ ደንብ መሠረት በሰዎች መነገድ ማለት ሰዎችን በማስፈራራት ፣ በኃይል ፣በማገት ፣በማጭበርበር (FRAUD)በማታለል፣ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም ፣ገንዘብ በመስጠት ወይም በመቀበል ሰዎችን ለመበዝበዝ በቁጥጥር ስር ለማድረግ መመልመል ፣ ማዘዋወር ማገት መያዝ እና ለሌላ ሰው አሳልፎ መስጠት የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል ። ሰዎችን በሴሴተኛ አዳሪነት አሰማርቶ መበዝበዝ ፣በኃይል በግዳጅ ሥራ ማሠማራት በባርነት ወይም ከባርነት ጋር በሚመሳል መንገድ ሰዎችን መያዝ እንዲሁም በኃይልና በግዳጅ ማሠራትን እና የሰዎችን የሰውነት አካላት ማውጣትንም ይጨምራል ።ከዚህ ደንብ በኋላ በሰዎች መነገድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል ።ዓለም ዓቀፉ የፖሊስ ድርጅት ኢንተርፖል እና የአውሮፓ አቻው ዩሮፖል ድንበር ተሻጋሪውን ይህን ወንጀል ለመከላከል በጋራ እየሰሩ ነው ። የፌደራል ጀርመን ወንጀል ጉዳዮች መሥሪያ ቤት በሰዎች የመነገድን ጉዳይ የሚመለከተው ክፍል ምክትል ሃላፊ ሄልጋ ጋየር ሁለቱ ድርጅቶች ተባብረው መሥራታቸው የሚደገፍ ነው ይላሉ ።በጋየር አስተያየት ችግሩን ለመከላከል ሰዎቹ የሚሸጋገሩባቸው ሃገራትም በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል ።
«ሁል ጊዜም ሰዎቹ ከሚመጡባቸው እና ከሚሸጋገሩባቸው ሃገራት ጋር አብረን መሥራት ይኖርብናል ። የሴተኛ አዳሪነቱን ሥራ ስናስብ ሴተኛ አዳሪዎቹ በጀርመን ብቻ ሳይሆን በኦስትሪያ በስዊትዘርላንድ በኔዘርላንድስ እንዲሁም በፈረንሳይ ወይም በቤልጂግ በዚሁ ሥራ ይሰማራሉ ። »
ጀርመንም ሰዎች በግዳጅ በሴተኛ አዳሪነት ከሚሰማሩባቸው የምዕራብ አውሮጳ ሃገራት አንዷ ናት ። የጋይለር መሥሪያ ቤት እንደሚለው በጎርጎሮሳዊው 2014 ለወሲብ ብዝበዛ የተዳረጉ የ392 ሰዎች ክሶች ተመዝግበዋል ። እንደ መሥሪያ ቤቱ በዚሁ ዓመት የተመዘገቡት የጉልበት ብዝበዛ ወንጀሎች 11 ብቻ ናቸው ።ይሁን እና ጋይለር በስታትስቲክስ የተያዘው ቁጥር እና እውነታው ግን ሊለያይ ይችላል ይላሉ።ከ 150 ሺህ እስከ 2 መቶሺህ የሚጠጉ ሴተኛ አዳሪዎች እንዳሉ በሚገመትባት በጀርመን በግዳጅ በዚህ ሥራ ተሰማሩ ተብለው የተመዘገቡት ቁጥር እጅግ አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል ።ሊያ አከርማን በሰዎች መነገድን የሚቃወም እና ለሴቶቹም አጋርነቱን የሚሳይ ዞልቮዲ የተባለው ድርጅት ውስጥ ሢሰሩ ከ30 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል ።ባለፈው ዓመት ብቻ 1700 ሰዎች የወሲብ ንግድ እና የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ለድርጅታቸው አስታውቀዋል ።አብዛኛዎቹም ከባልካን ሃገራት በተለይ ከሩማንያ ከቡልጋርያ ከአልባንያ የመጡ ሲሆን በርካታ ናይጀሪያውያንም ይገኙበታል ። ከነዚህ 1700 ሴቶች አንድ አራተኛው ወደ ዞልቮዲ የሄዱት የመኖሪያ ፈቃድ ችግር ስለገጠማቸው ነው ።አከርማን ሥጋቸውን እንዲሸጡ በሚገደዱ ሴቶች የሚገኘው ትርፍ የትየለሌ መሆኑን ነው የሚያስረዱት ።ለዚህም በምዕራብ ጀርመንዋ በኮሎኝ ከተማ ለዚሁ ተግባር ፣ ክፍል ብቻ የሚያከራይ የአንድ ትልቅ ቤት ባለቤት በቀን ሊያገኝ የሚችለውን ገቢ በምሳሌነት አቅርበዋል ።
«በቀን 135 ዩሮ የሚከፍሉት መቶ ያህል ሴቶች ካሉት በአንድ ቀን ውስጥ 13,500 ዩሮ ያገኛል ።ይህ ደግሞ በወር 405 ሺህ በዓመት ደግሞ ወደ 4,800,000 ዩሮ ይደርሳል ።እንግዲህ ይሄ የሚገኘው ክፍል በማከራየት ብቻ ነው ።»
ሆኖም ይህ ሰው አከራይ በመሆኑ ብቻ በወንጀል ሊጠየቅ አይችልም ። አከርማን በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ቤቶች ሌላ ስም እየተሰጣቸው መተዋወቅ መጀመራቸውንም ያስረዳሉ ።
« በአዲሱ ህግ ከጎርጎሮሳዊው 2002 ዓም አንስቶ በጀርመን ሴተኛ አዳሪነት እንደ ሌሎቹ ሙያዎች በህግ ተፈቅዷል ። አሁን ለዚህ ሥራ የሚያገለግሉ ቤቶች የሚተዋወቁት እንደ ሰውነት ማፍታቻ ገነት ሆኗል ።»
ለሴቶቹ ግን እነዚህ ቦታዎች ብዙውን ጊዜ ሲኦል ናቸው ። አክርማን በቅርቡ የግዳጅ የወሲብ ንግድን ለመከላከል የጸደቀው የጀርመን ህግም በሰዎች መነገድን ብዙም ሊለውጥ አይችልም ነው የሚሉት።
በአዲሱ ህግ እያወቀ በግዳጅ ሴተኛ አዳሪየሆኑ ሴቶችን የሚጠቀም አሠሪ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እሥራት ሊቀጣ ይችላል ። ሄልጋ ጋየር እንደሚሉት ደግሞ ህጉ ሌሎች አዳዲስ ጉዳዮችንም በግልፅ አካቷል ።
«በጀርመን የወንጀል ህግ በተለይ በልመና ማሠማራትን ፣ ወንጀሎችን መፈፀመን እና የሰውነት አካላትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ተጨምረዋል ። ይህ አዲስ ነው ።»
አዲሱ ህግ በጀርመን ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ውስጥ መግባት እና ተግባራዊ መሆን እንዳለበትም ጋየር ተናግረዋል ።በማየር ግምት ህጉ በዚህ ዓመት ሥራ ላይ ይውላል ።

ምስል Pascha
ምስል Pascha
ምስል picture-alliance / Ton Koene
ምስል AP
ምስል picture-alliance/dpa

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW