1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የወባ በሽታ በደቡብ ኢትዮጵያ

ሰኞ፣ መስከረም 6 2017

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ለጊዜው በኀሃዝ ለማስደገፍ ቢቸገሩም በክልል የበሽታው ሥርጭት በእጥፍ መጨመሩን አረጋግጠዋል ፡፡

China | Fossil einer Stechmücke in Bernstein
ምስል Xinhua/picture alliance

"ወባ ሰው እየገደለ ነው"

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተቀሰቀሰ የወባ በሽታ በርካቶችን ለህመም እና ለሞት እየዳረገ እንደሚገኝ ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገለጹ ፡፡ ነዋሪዎች እንዳሉት በበሽታው ተይዘው ወደ ጤና ተቋማት የሄዱ ህሙማን በቂ የህክምና ዕርዳት እያገኙ አይደለም ፡፡  በክልሉ የበሽታው ሥርጭት በእጥፍ መጨመሩን የገለጸው  የደቡብ ኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋም በበኩሉ በበሽታው ሰዎች ሥለመሞታቸው ግን በግምገማ እለመረጋገጡን አስታውቋል ፡፡

አሳሳቢው የወባ በሽታ በደቡብ ኢትዮጵያ
አቶ አለማየሁ ኢጃጆ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ የጥዮ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው  ፡፡  አቶ አለማየሁ ከባለፈው የሰኔ ወር ወዲህ በአካባቢው የተከሰተው የወባ በሽታ እየተባባሰ መምጣቱን ይናገራሉ ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በሽታው በርካታ የመንደሩን ነዋሪዎች ለአልጋ ቁራኛ ዳርጓል የሚሉት አስተያየት ሰጪው  በበሽታው ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉም እንደሚገኙበት ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል  ፡፡
ዶቼ ቬለ በክልሉ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል በተባለው የወባ በሽታ ዙሪያ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ምንተስኖት መልካን ጠይቋል ፡፡ ምክትል ዳይሬክተር ለጊዜው በኀሃዝ ለማስደገፍ ቢቸገሩም በክልል የበሽታው ሥርጭት በእጥፍ መጨመሩን  አረጋግጠዋል ፡፡  በክልሉ ከፍተኛ የወባ ጫና ያለባቸው 21 ወረዳዎችም መለየታቸውን የጠቀሱት ምንተስኖት “፡ በበሽታው የሰው ሕይወት እያለፈ ነው በተባለው ላይ ግን እስከአሁን በመረጃ የተገመገመ ነገር የለም “ ብለዋል ፡፡

የጸረ ወባ ትንኝ መድሃኒት ርጭት በደቡብ ኢትዮጵያምስል Shewangizaw Wogayehu/DW


የፈውስ መድሃኒት እጦት  
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየበረታ መጥቷል የተባለው የወባ በሽታ ከዎላይታ በተጨማሪ በጎፋና በደቡብ ኦሞ ዞኖች የነዋሪዎች ሥጋት እየሆነ መምጣቱን ዶቼ ቬለ ከየአካባቢው ያሰባሰባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡ በጎፋ  ዞን መሎኮዛ ወረዳ የሳላይሽ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ፎላ ሰዎች በበሽታው ምክንያት በየቤቱ ተኝተዋል ይላሉ ፡፡
የወባ በሽታ በታዩባቸው አካባቢዎች በቂ ባይሆንም የተወሰነ  የአጎበር ዕደላዎችና የፀረ ወባ ትንኝ መድሃኒት ርጭት መካሄዱን የጠቀሱት የቦሎሶ ሶሬ እና የሞሎኮዛ ወረዳ አስተያየት ሰጪዎች  “ ነገር ግን  ታመው ወደ ጤና ተቋማት የሄዱ ህሙማን መድሃኒት እያገኙ አይደለም ፡፡ ታመው በምርመራ ወባ እንዳለባቸው ቢነገራቸውም የፈውስ መድሃኒት ግን የለም ፡፡ የህክምና ባለሙያዎችም  ወደ ከተማ ሄደን እንድንገዛ ነው የሚነግሩን “ ብለዋል፡፡
የአቅርቦቱ መፍትሄ እና የቤት ለቤት ምርመራ 
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ምንተስኖት መልካ የወባ ታማሚዎች መድሃኒት እያገኙ አይደለም በሚለው አይስማሙም ፡፡ በዎላይታ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች የህክምና መድሃኒት አቅርቦት የመዘግየት ክፍተቶች እንደነበሩ የጠቀሱት ምክትል ዳይሬክተሩ “  አሁን ላይ አቅርቦቱን በመጨመር ግን እጥረቱን ሙሉ በሙሉ  ለመቅረፍ  ተችሏል “ ብለዋል  ፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተባባሰ የመጣውን የወባ በሽታ ለመከላከል  ካለፈው የሰኔ ወር ጀምሮ የቤት ለቤት የህክምና ምርመራ መጀመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ ቀደም ሲል ማስታወቁ አይዘነጋም  ፡፡ በክልሉ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ የህመም ስሜት ታይቶባቸው ምርመራ ከተደረገላቸው 30,807 ሰዎች መካከል 18,056 ሰዎች የወባ በሽታ እንደተገኘባቸው ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ፀሐይ ጫኔ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW