1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበረታው የወባ በሽታ በደቡብ ኢትዮጵያ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 19 2017

“ብዙ ጊዜ በዕለታዊና በሳምንታዊ ተደምሮ የሚመጣው አሃዝ አይገናኝም ፡፡ ይሄ የውሸት ሪፖርት መታረም አለበት ፡፡ በተረፈ በሽታው የራስ ጥረትን ተጠቅመን በሽታውን ልንከላከለው እንችላለን“ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ

Malaria-Epidemie in Südäthiopien
ምስል Shewangizaw Wogayehu/DW

የበረታው የወባ በሽታ በደቡብ ኢትዮጵያ

This browser does not support the audio element.

ታረቀኝ ጎኣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ዳሞት ፉላሳ በተባለ ወረዳ በሚገኝ ጤና ጣቢያ ውስጥ በህክምና ሙያ በማገልገል ላይ ይገኛል ፡፡ “ በሙያው በቆየሁባቸው ባለፉት አሥር ዓመታት የወባ በሽታ እንደአሁኑ ሰፍቶ አላየሁም “ የሚለው ታረቀኝ “ እዚህ አኔ በምሠራበት ጤና ጣቢያ ብቻ በቀን እስከ ስምንት መቶ ህሙማንን ተቀብለን እያከምን እንገኛለን ፡፡ ወደ ጤና ጣቢያው ህክምና ፍለጋ ከሚመጡት ህሙማን መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የወባ ተጠቂዎች ናቸው ፡፡ የበሽታው ሁኔታ  ከባድ ፣ ሥርጭቱም  ከአቅም በላይ የሆነ ይመስላል “ ብሏል ፡፡
በዞኑ የሁምቦ ወረዳ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩ ሁለቱ  ነዋሪዎች በበኩላቸው በወረዳው በወባ በሽታ የተነሳ ሰዎች መታመማቸውንና ለሞት መዳረጋቸውን ተናግረዋል ፡፡ “ በርካቶች  ህመማቸው ወባ መሆኑ ከተነገራቸው በኋላ ተኝተው መታከማቸውን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ ሲታከሙ ከሞቱት መካከል የቅርብ ዘመዶቻቸው እንደሚገኙበት ገልጸዋል ፡፡
የሽታው ሥርጭት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ?
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወባ በሽታ ሥርጭት እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ጤና  ቢሮ አስታውቋል ፡፡  በክልሉ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ222 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችበወባ በሽታ መጠቃታቸውን የጠቀሰው ቢሮው ነገር ግን በበሽታው ህይወታቸው አልፏል ስለሚባሉ ሰዎች የቢሮው ሃላፊዎች በሪፖርታቸውም ሆነ በቃለ ምልልሶቻቸው ውስጥ በአሃዝ ሲጠቅሱ አይስተዋልም ፡፡  ያም ሆኖ አሁን ላይ የበሽታው ጫና ጎልቶ የታባቸው 21 ወረዳዎች መለየታቸውን ከቀናት በፊት ለዶቼ ቬለ የገለጹት በቢሮው የህብረተሰብ ጤና ተቋም ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምንተስኖት መልካ “ ለታማሚዎች ህክምና የማቅረብና የበሽታ መከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

በአሁኑ ወቅት በክልሉ የሚታየውን የወባ ሥርጭት መጠን እስከ ታህሳስ 2017 መጨረሻ በ 50 በመቶ ለመቀነስ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገምስል Shewangizaw Wogayehu/DW


በሽታውን የመከላከል ጥረት
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየጨመረ መጥቷል የተባለው የወባ በሽታ አሁን አሁን የከፍተኛ አመራሮችን ትኩረት እያገኘ የመጣ ይመስላል ፡፡ አመራሮች በክልሉ የተለያዩ ዞኖች በሽታው መከላከል በሚቻልበት ሥራዎች ላይ እየተወያዩ ፤ በየአካባቢው የወባ መከላከል ቅስቀሳዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ ፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በዎላይታ ሶዶ በተካሄደው መድረክ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ  ጥላሁን ከበደ በሽታውን “ በመከላከል ልንቆጣጠረው እንችላለን “ ብለዋል ፡፡ ነገር ግን በየደረጃው የሚገኙ አካላት የውሸት ሪፖርት ከማቅረብ መቆጠብ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ “ ቀውሱ አዙሪት ነው ፡፡ የፖለቲካዊ ፣ የኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጫና አለው ፡፡  ብዙ ጊዜ በዕለታዊና በሳምንታዊ  ተደምሮ የሚመጣው አሃዝ አይገናኝም ፡፡ ይሄ የውሸት ሪፖርት መታረም አለበት ፡፡ በተረፈ በሽታው የራስ ጥረትን ተጠቅመን በሽታውን ልንከላከለው እንችላለን “ ብለዋል ፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የሚታየውን የወባ ሥርጭት መጠን እስከ ታህሳስ 2017 መጨረሻ በ 50 በመቶ ለመቀነስ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳድሩ  ጠቅሰዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ነጋሽ መሐመድ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW