የወባ ስርጭት በምዕራብ ወለጋ ቆንዳላ ወረዳ
ረቡዕ፣ ጳጉሜን 5 2017
በምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ ገጠራማ ስፍራዎች በወባ በሽታ ሶስት ህጻናት መሞታቸዉን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቋል፡፡ በቆንዳላ ወረዳ ጋራ አርባ በተባለ ስፍራ እና ሌሎች ገጠራማ ስፍራዎች የወባ በሽታ አሁንም በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት በበኩሉ የወባ ስርጭት በወረዳው ቢኖርም በሰው ላይ የሚያደረሰውን ጉዳት ግን ቀንሰዋል ሲል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞን ከዳቡስ ወንዝ ጋር በሚዋሰኑ አካባዎችዎች እንደ መንዲ፣ቤጊ፣እና በሚባሉ ቦታዎች ወባ ባለፈው ዓመት በወረርሽኝ መልክ ተሰራጭተው የቆየባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ በቆንዳላ ወረዳ ገጠራማ ቦታዎች እንደ ጋራአርባ፣ ወርባ እና ገሚጋባ በሚባሉ ቦታዎች የወባ ስርጭቶ በቅርቡ በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ እና የ3 ሰዎች ህይወት በበሽታው ማለፉን ያነጋገርናቸው አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ አመልክተዋል፡፡
በቆንዳላ ወረዳ በወባ በሽታ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ
‹‹ ገጠራማ ቦታዎች ላይ በሚገኙ ቀበሌዎች ስርጭቱ ይበዛል፡፡ ጋራ አርባ በሚባል ቦታ ሶስት ሰዎች ህይወት አልፍዋል፡፡ እነዚህ አካባቢዎች በቂ አገልግሎት የለለባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ ካዜ በሚባል ቦታም አንድ ነፍሰጡር እናት በወባ ታመው ወደ ህክምና ሳይሰርሱ ህይወታቸው ያለፈው፡፡ አምቡላንስ ርቀት ቦታዎች ላይ አይንቀሳቀሱም፡፡ የወባ መካላያ ኬሚካል ሪጭት አንድ አንድ ቦታዎች ላይ ለከተረጨ በኃላ ስርጭቱ ቀንሶ የቆየ ቢሆን አሁን በአዲስ መልክ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡››
በወረዳው የተወሰኑ ቦታዎች ከርጅም ጊዜ በኃላ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር መሰራጨቱን የተናገሩት ሌላው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ በገጠራማ ቦታዎች አሁንም ወባ በሽታ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በተለይም በዳቡስ ወንዝ በቅርበ ርቀት ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ስርጭቱ በስፋት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ በተወሰኑ ቦታዎቸ አጉበር ተሰራጭተዋል፡፡ ገጠራማ ቦታዎች ግን አልተዳረሰም፡፡ ገጠር ላይ አንድ የጸጥታ ስጋት አለ፣ ሁለተኛ ደግሞ መንገድ የለም፡፡ አጎበርም አላገኙም፡፡ጋራአርባና ጥሽሞ የተባለ ቦታ ዳቡስ ወንዝ ጋር አጎራባች የሆኑ ቦታዎች ናቸው፡፡ 3 ልጆችን በዚህው በሽታ ሞተዋል፡፡››
‹‹የወባ ስርጭት ቢኖርም በሰው ህይወት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቀንሰዋል››
የቆንዳላ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት በበኩሉ በወረዳው ወባ ስርጭት መኖሩን የገለጸ ሲሆን በሰው ህይወት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ደግሞ መቀነሱም አስታውቋም፡፡ በወረዳው ጤና ጽ/ቤት ዕቅድና በጀት ባለሙያ የሆኑት አቶ ግርማ አክሊሉ በወረዳው የወባ ስርጭት ባለፈው ዓመት ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከወረርሽኝ ደረጃ መቀነሱን አመልክተዋል፡፡
‹‹ ስርጭቱን በተመለከተ ባለፈው ዓመት 2016 እና 2017 ዓ.ም መጀመሪያዎች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ባለው ሁኔታ ግን ቀንሰዋል፡፡ አጎበርም ለሁሉም ባይዳረስም ተሰርጭተዋል፡፡ ወደ ጤና ተቋም ከሚመጡ ሰዎች መካከል 50 በመቶ በወባ ከተጠቃ ወባ በወረርሽኝ ደረጃ መኖሩን ያሳያል፡፡ አሁን ያለው ስርጭት ከዚህ ያነሰ ነው፡፡ ጋራአርባ በተባለ ቦታ ሰው ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባለው መረጃ ተቋማችንን የደረሰ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በአካባቢው ስርጭቱ በስፋት አለ፡፡ በወረዳ ደረጃ ባለፈው ሳምንት ወደ ጤና ተቋም ከመጡት 1750 ሰዎች መካከል ወባ የታየው 800 በሚደርሱ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ከስርጭት አንጻር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መቀነሱን ያሳል፡፡››
በምዕራብ ወለጋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ወባ በየዓመቱ በበርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱ በተለያዩ ወቅቶች ሲዘገብ ቆይተዋል፡፡ በ2016 ዓ.ም ምእራብ ወለጋን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ወባ በወረርሽኝ መልክ ተሰራጭቶ መቆየቱን የክልሉ ጤና ቢሮ መግለጹ ይታወሳል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ሥለሺ