1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወባ በሽታ ስርጭት በአማራ ክልል

ማክሰኞ፣ ሰኔ 20 2015

የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አቶ ዳምጤ ላንክር የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ እንዳሉት በአማራ ክልል ሁሉም ወረዳዎች የወባ በሽታ ይታያል፡፡በክልሉ ባለፉት 11 ወራት ከአለፈው ዓመት ሲነፃፀርም በእጥፍ በመጨመር በበሽታው የሚያዙት ሰዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን መድረሱን አቶ ዳምጤ ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል፡፡

Amhara Public Health Institute office in Bahir Dar Äthiopien
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ወባ 24 ሰዉ ገደለ፣ከአንድ ሚሊዮን በላይ ያዘ

This browser does not support the audio element.

 

በአማራ ክልል ዘንድሮ በወባ በሽታ የተያዘዉ ሰዉ ቁጥር ከአምናዉ በእጥፍ መጨመሩን የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም አስታወቀ።ተቋሙ እንደሚለዉ በክልሉ ዘንድሮ በወባ በሽታ 24 ሰዎች ሞተዋል፤ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ ደግሞ በበሽታዉ ተይዛል።ተቋሙ በሽታዉ በጠናባቸዉ በ82 ወረዳዎች ለሚኖር 7 ሚሊዮን ሕዝብ የወባ መከላከያ መድሐኒትና ቁሳቁስ ማደሉን አስታዉቋል።የወባ በሽታ ከአምና ዘንድሮ የከፋበትን ምክንያት ግን ተቋሙ አልገለፀም።

እጅግ የከፋ የወባ ህመምም በበረታባቸው 6 የክልሉ ወረዳዎች ደግሞ የኬሚካል ስርጭት እየተከናወነ እንደሆነ ተቋሙ አመልክቷል፣ የጤና ተቋማትና ነዋሪዎችም የበሽታው ስርጭት ከአለፈው ዓመት ዘንድሮ መስፋፋቱን ይናገራሉ፡፡ ቀደም ባሉት ጊዚያት በሽታው የሚታወቀው በአብዛኛው በቆላማ  አካባቢዎች ቢሆነም አሁን አሁን ግን መጠኑ ቢለያይም በሁሉም የአማራ ክልል አካባቢዎች ወባ የጤና ጠንቅ እየሆነ መምጣቱን ነው የጤና ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አቶ ዳምጤ ላንክር  የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ እንዳሉት እንደ የአየር ሁኔታው የታማሚዎች ቁጥር የተለያየ ቢሆንም በአማራ ክልል ሁሉም ወረዳዎች የወባ በሽታ ይታያል፡፡በክልሉ ባለፉት 11 ወራት ከአለፈው ዓመት ሲነፃፀርም በእጥፍ በመጨመር  በበሽታው የሚያዙት ሰዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን መድረሱን አቶ ዳምጤ ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል፡፡
“አሁን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው ያው በወባ ተይዟል፣ ይህ ደግሞ እንደየዞኖቹ ስርጭቱ ልዩነት አለው፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ አዊ፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም የመሳሰሉ ዞኖች ከፍተኛ የበሽታው ስርጭት አለባቸው፡፡ ካለፈው ዓመት ጋር ስናነፃፅረው የዚህ ዓመቱ ከ56.5 % በላይ ነው ጭማሪው” ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አንድ የቆቦ ከተማ ነዋሪ በየጤና ተቋማት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የወባ ታማሚዎች እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
በአዊ ብሐረሰብ አስተዳደር የዚገም ወረዳ ነዋሪው አቶ መሐመድ ኢብራሂም ሁለት እህቶቻቸው በወባ እንደታመሙና እርሳቸውም በቅርቡ እንዳገገሙ ገልፀው፣ በጤና ተቋማቱ ህክምና እየተሰጠ ቢሆንም ከፍተኛ የታማሚ ቁጥር እንዳለ ገልፀዋል፡፡
“በጣም በጣም በርካታ ማህበረሰብ እየታመመ ነው፣ ሆስፒታል ሙሉ ነው፣ እኔ ራሱ አንዱ ታማሚ ነበርኩ አሁን አገግሜያለሁ፣ ሁለት ቤተሰቦቼ ታምመዋል፣ ገበሬው መስራት አልቻለም፣ አምና ሰላም ነበር፣ የዚህን፣ያክል አልከበደም ነበር፣ አምና አጎበር እጠቀም ነበር፣ በእርግጥ ዘንድሮም እጠቀማለሁ”
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በየቀኑ የወባ ታማሚዎች ወደ ህክምና ጣቢያ በከፍተኛ ቁጥር እየመጡ እንደሆነ  የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት  ኃላፊ አቶ ታምሩ ቢምረው ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪው አቶ ዳምጤ ላንክር እንዳሉት፣ ባለፉት 11 ወራት ከበሽታው ጋር በተያያዘ የ24 ሰዎች ህይወት አልፏል፣ በሽታውን የመከላከል፣ የመቆጣጠርና የህክምና ስራው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
“በወባ 24 ሰዎች ሞተዋል፣ ተጓዳኝ ችግርም የነበረባቸው ናቸው፣ የመድኃኒት እትረት ነበር፣ ለተወሰነ ሳምንትና ወር፣ ተመሳሳይ መድኃኒት ግን አገልግሎቱ ሲሰጥ ቆይቷል፣አሁን ግን ተሟልቷል፣ ህክምናው ግን አልተቋረጠም፣  የአልጋ አጎበር ለ82 ወረዳዎች 3 ሚሊዮን 800ሺህ ተሰራጭቷል፣ ከ6 እስከ 7 ሚሊዮን ለሚሆን ህዝብ ተደራሽ ተደርገዋል፣ የመኖሪያ ቤት የኬሚካል ስርጭት በ6 ወረዳዎች እየተካሄደ ነው፤  ደራ፣ ፎገራ፣ ጃዊና 3 የምዕራብ ጎንደር ወረዳዎች፣ እነኚህ ደግሞ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡”
ምንም እንኳ የወባ ስርጭቱ በበርካታ የክልሉ ወረዳዎችና ዞኖች ቢስፋፋም እስካሁን ግን በወረርሽኝ መልክ እንዳልተከሰተ ነው አቶ ዳምጤ የሚገልፁት፡፡
ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ሳያቋርጥ የአልጋ አጎበርን በአግባቡ እንዲጠቀም፣ ውሀ የአቆሩ ቦታዎችን እንዲያፋስስና እንዲደፍን፣ ለወባ ትንኝ መራባት አመቺ የሆኑ የግቢና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ፣ ሰዎች ሲታመሙ ደግሞ በአስቸኳይ ወደ ህክምና ጣቢያ እንዲሄዱ ባለሙያው መክረዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን

ምስል pzAxe/IMAGO

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW